የማህፀን ዕጢ የምንለው የካንሰርነት ባሕርይ የሌለው የማሕፀን ውስጥ ዕባጭ ሲሆን በአብዛኛው የሚከሰተው በወጣትነት ዕድሜ ላይ ነው፡፡ የማህፀን ውስጥ ዕጢ ወደ ማኅፀን ካንሰርነት የመለወጥ ዕድሉ እጅግ በጣም አናሳ ነው፡፡
የማሕፀን ዕጢ ከማሕፀን ግድግዳ ጡንቻዎች የሚነሳ ሲሆን የሴሎች ጤናማ ባልሆነ ሆኑታ ሲከፈሉ የሚመጣ ሆኔታ ነው፡፡ ይህ የማሕፀን ዕጢ በፍጥነት የሚያድግ ወይንም በዝግታ የሚያድግ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ተመልሶ በራሱ ሊጠፈም ይችላል፡፡
የማሕፀን ዕጢ ምልክቶች
የማኅፀን ዕጢ በአብዛኛው ምንም ዓይነት ምልክት የማያሳይ ቢሆንም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚከሰቱ ምልክቶች እንዚህ ናቸው፡፡
• ከፍተኛ የሆነ የወር አበባ መብዛት
• ከሰባት ቀናት በላይ የሚቆይ የወር አበባ ማየት
• ማሕፀን አካባቢ ግፊት መሰማት ወይንም ሕመም
• ቶሎ ቶሎ የውሃ ሽንት መምጣት
• የሆድ ድርቀት
• የጀርባ እና የዕግር ሕመም ስሜት
• አልፎ አልፎ ከፍተኛ የሆነ ሕመም (አጣዳፊ) የሚያስከትል ሲሆን ይህም የሚሆነው የደም ዝውውር በሚቀንስ ጊዜ/በሚቋረጥ ጊዜ ነው፡፡
ለማሕፀን ዕጢ ተጋላጭነት የሚጨምሩ ሁኔታዎች
• ከዘር፡- እናት ወይንም እህት የማሕፀን ዕጢ ወደ ዘር ካላቸው ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡
• ጥቁር ዘር፡- ጥቁር ሴቶች በአብዛኘው ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፡፡
• በልጅነት የወር አበባን ያዩ ከሆነ እና አመጋገብ ናቸው፡፡
የማኅፀን ዕጢ ለከፋ የጤና ችግር የሚዳርግ ባይሆንም የደም ማነስ እና ምቾት ማጣትን ግን ሊያስከትል ይችላል፡፡
የማሕፀን ዕጢ እና እርግዝና
የማሕፀን ዕጢ በአብዛኛው እርግዝናን የማይቃረን ቢሆንም አንዳንዴ ዕጢው በሚገኝበት ቦታ ምክንያት በጥቂት ሰዎች ላይ እርግዝናን እንዳይፈጠር መንስዔ ይሆናል፡፡ ይህ በመሆን ጊዜ ሐኪምን በማማከር ከእርግዝና በፊት መደረግ ያለባቸውን ቅድመ ሆኔታዎች ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ሐኪምዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነው?
• የማያቋርጥ የማሕፀን አካባቢ ሕመም ካለ
• ከፍተኛ ሕመም ያላቸውና በብዛት የሚያስቸግሩ የወር አበባ ጊዜያት
• ከወር አበባ ፅዳት ውጪ የደም መፍሰስ
• በግብረ ስጋ ግኝኑነት ጊዜ የሕመም ስሜት ከተሰማዎት
• የሆድ ዕብጠት ካለ
• የውኃ ሽንትን ማስወገድ መቸገር
እጅግ ከፍተኛ የሆነ ድንገተኛ የማኅፀን አካባቢ ሕመም ካለዎትና ከፍተኛ የደም መፍሰስ የሚኖር ከሆነ በአፋጣኝ ወደ ሐኪም እንዲሄዱ ይመከራል፡፡
ምንጭ:- ጤናችን