የልብ ድካም ህክምና ካደረጉ ሰዎች 20 በመቶ የሚሆኑትን ታካሚዎች ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለሌላ የልብ ሕመም እንደሚጋለጡ ጥናቶች ይገልፃሉ።
ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የሰውነት ክፍሎች መዳከም እና የሕዋሳት (tissue) ያለመጎልበት ችግር ነው ተብሏል።
በዚህም በብሪታኒያ ውስጥ በየዓመቱ ከሰባት ወንዶች አንዱ እና ከ11 ሴቶች መካከል አንዷ በድንገተኛ ልብ ሕመም እንደሚሞቱ ጥናቱ አሳይቷል።
ተመራማሪዎች ሰዎች በዚህ ምክንያት እንዳይሞቱ ከልብ ድካም እንዲድኑ እና ጡንቻዎቻቸው እንዴት እንደሚያድጉ የሚረዳ አዲስ ጥናት አካሂደዋል።
በዚህም በአላባማ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝ አንድ የጥናት ቡድን በደከሙ የልብ ጡንቻዎች (cardiomyocytes) ላይ ህክምና በማድረግ አዳዲስ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።
ሙከራው የሚያሳየው የበራሒ (genes) ከፍተኛ ግፊት (cell-cycle activator gene CCND2)፥ በከፍተኛ ሁኔታ በድንገት የተዳከመውን የልብ ጡንቻ እንደገና ስራውን እንዲጀምር አድርጓል ።
ይህም የሆነው ህዋሳቶችን የበለጠ በማሳደግ እና በመከፋፈል ነው ተብሏል።
ይህ የህዋሳት የዕድገት መጨመር እና መከፋፈል ደግሞ የልብ ጡንቻ እንዲበረታ እና የሞቱ ህዋሳት መጠን እንዲቀንስ አስችሏል።
በተጨማሪም ጡንቻን እንደገና እንዲበረታ በማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ በተጎዳው ክፍል አዲስ የደም ቧንቧዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ይህ ሙከራ ሰው ሰራሽ በሆኑ ግንደ ሕዋስን(stem cells) በመጠቀም በአይጦች የተካሄደ ሲሆን፥ ወደፊት ይህ ህክምና የልብ ህመም ታካሚዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል::
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)