ሽንኩርት ከተመገቡ በኋላ የሚፈጠር የአፍ ጠረን መቀየርን እንዴት መከላከል ይችላሉ?

                 

ነጭና ቀይ ሽንኩርት ካላቸው የጤና ጠቀሜታ አንጻር ከምግብ ጋርና ብቻቸውን በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

እነዚህን የአትክልት ዘሮች በተለይም ደግሞ በጥሬው ከተመገቧቸው በኋላ የአፍ ጠረንን ሊቀይሩ ይችላሉ።

ይህም በሁለቱ የአትክልት ዘሮች የሚገኙ ውህዶች ሳልፈርን በብዛት አምቀው ከመያዛቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። 

ሽንኩርቱ ተልጦ አየር በሚያገኘው ሰዓት በውስጡ ያለው አሊን የተባለው ውህድ ወደ አሊሲንነት ይቀየራል፤ ይህ ደግሞ በውስጡ ሳልፈርን አምቆ እንዲይዝ ስለሚያደርገው ለመጥፎ የአፍ ጠረን ይዳርጋል።

ከዚህ ባለፈም በሁለቱ አትክልቶች ውስጥ የሚገኘው አሊል ሜቲል ሰልፋይድ የተሰኘው ውህድ ሽንኩርቱን ሲመገቡ ወደ ደም በመግባት ወደ ሳንባና የቆዳ ቀዳዳዎች ይሰራጫል።

በዚህ ሳቢያም መጥፎ የአፍና ምናልባትም መጥፎ የሰውነት ጠረን ሊከሰት ይችላል።

ሲስቴይን ሳልፍ ኦክሳይድ ይህም በሽንኩርቱ ውስጥ የሚገኝ ውህድ ሲሆን ከተመገቡ በኋላ ለሚፈጠር መጥፎ የአፍና በሂደት ለሚመጣ የሰውነት ጠረን መቀየር ምክንያት ነው።

ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር ቀይና ነጭ ሽንኩርትን አለመመገብ ሳይሆን ይህን አጋጣሚ እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል መፍትሄ መፈለግ ነው።

ባለሙያዎችም ሽንኩርትን ከተመገቡ በኋላ ሊፈጠር የሚችልን መጥፎ የአፍና የሰውነት ጠረን ለመከላከል የሚከተሉትን መንገዶች እንዲጠቀሙ ይመክራሉ።

ውሃ መጠጣት፦ ይህን ሲያደርጉ የሽንኩርቱን ቅሪት ከአፍዎ ለማስወገድ ይረዳል፤ በተጨማሪም በአፍ ውስጥ በሚገኝ ባክቴሪያ ሳቢያ ሽንኩርት ሲመገቡ የሚፈጠርን መጥፎ ጠረን ለማስወገድ የሚረዳዎትን ምራቅ ማመንጨትም ያስችልዎታል።

መቦረሽና ምላስን ማጽዳት፦ በድድና በጥርስ መካከል ለመጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ የሆኑ የምግብ ቅሪቶች ይኖራሉ፤ ይህን ለማስወገድ ደግሞ ዘወትር አፍን በደንብ መጉመጥመጥ ከዚህ ባለፈም መቦረሽ።

በተጨማሪም በጥርስና በጥርስ መካከል ቀጭን ጠንካራ ክር በማስገባት ቅሪቶችን ማስወገድ (ፍሎስ ማድረግ) መጥፎ ጠረንን ለማስወገድ ይረዳል።

ከዚህ ባለፈምን ሽንኩርት ከተመገቡ በኋላ ምላስ ላይ ሊኖር የሚችልን ቅሪት ለማስወገድ ምላስንና የአፍን የላይኛው ክፍል ማጽዳት።

ለዚህም ለምላስ ማጽጃ ብሩሽ አልያም ምላስን ለማጽዳት የሚያገለግል ማጽጃ መጠቀም፤ እነዚህ ቦታዎች ለባክቴሪያ መከማቸት ትልቅ ድርሻ ስለሚኖራቸው ይህን ማድረጉ ይመከራል።

የአፍ ማጽጃዎችን መጠቀም፦ የናና ቃና ያላቸው አፍ ማጠቢያዎችን መጠቀም፥ አልያም ደግሞ ክሎሪን ዳይ ኦክሳይድ ያላቸውን የአፍ ማጽጃዎች መጠቀምም ለዚህ መፍትሄ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

እነዚህ የምግብ ቅሪቶችን፣ ባክቴሪያና በሽንኩርቱ ሳቢያ የሚፈጠርን የአፍ ጠረን መቀየርን ያስወግዳሉ።

አትክልትና ፍራፍሬ፦ ፍራፍሬና አትክልቶችን በተለይም እንደ አፕልና ሰላጣ ያሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ሽንኩርት ከተመገቡ በኋላ መውሰድ ሽታውን ለማጥፋት ይረዳል።

የምግብ ማጣፈጫ ተክልን ሽንኩርት ከተመገቡ በኋላ ማኘክም ለዚህ እንደሚረዳ ነው የሚነገረው።

ኮምጣጤ፦ ሽንኩርት ወይም ሽንኩርት የበዛበት ምግብ ከተመገቡ በኋላ አንድ የሻይ ማንኪያ ኮምጣጤን በውሃ ቀላቅሎ መጠጣት፤ ይሁን እንጅ ይህን የመፍትሄ ሃሳብ ከመጠቀምዎ በፊት ሃኪም ማማከርዎን አይዘንጉ።

አረንጓዴ ሻይ፦ ይህን መጠጣት የሽንኩርቱን ሽታ ለማጥፋት በእጅጉ ይረዳዎታል፤ ከዚህ ባለፈም ለመላው የአፍ ጤንነትም መልካም ነው።

ማስቲካ፦ ሌላውና በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚውለው መከላከያ መንገድ ማስቲካን ማኘክ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሜንት ቃና ያለው ማስቲካ እጅጉን ተመራጭ ነው።

ወተት፦ ወተት ሲጠጡ ሽንኩርት ከተመገቡ በኋላ በሳልፈር መታመቅ ምክንያት የሚፈጠረውን የአፍ ጠረን መቀየር ለማስወገድ ይረዳዎታል።

ሎሚ፦ አንድ የሾርባ ማንኪያ የሎሚ ውሃ በአንድ ብርጭቆ ውሃ ቀላቅሎ መጠጣትምን ሌላው መፍትሄ ነው።

ከዚህ ባለፈ ግን ነጭ ሽንኩርቱን ከላጡ በኋላ ከሽንኩርቱ በላይ በጣም በስሱና ምናልባትም ለመላጥ አስቸጋሪ የሆነውን ክፍል ማስወገድም

ከተመገቡት በኋላ ሊፈጠር የሚችልን የአፍ ጠረን መቀየር ለመከላከል ይረዳወታልና ይጠቀሙበት።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement