ደቡብ ኮርያ ውስጥ ወደ 500,000 ገደማ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ይወስዳሉ።
ፈተናው እጅግ አስጨናቂ እንደሆነ ይነገርለታል። የኮሮሮናቫይረስ ደግሞ የተማሪዎችን ጭንቅ አብሶታል።
ፈተናው ‘ኮሌጅ አቢሊቲ ቴስት’ ወይም በአጭሩ ሰንአግ ይባላል። ስምንት ሰዓታት ይወስዳል።
በስድስት ክፍሎች የኮርያኛ፣ የሒሳብ፣ የእንግሊዘኛ፣ የታሪክ እና የማኅበረሰብ ሳይንስ ፈተናዎችን ያካትታል።
ተማሪዎች የት ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ፣ በምን የሥራ ዘርፍ እንደሚሰማሩ የሚወሰነውም በፈተናው ውጤት አማካይነት ነው።
ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ወላጆቻቸውም ለፈተናው ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ።
ከሁለት ዓመት እድሜ ጀምሮ ዝግጅት የሚደረግለት ፈተና
ይህ ፈተና ሲጀመር መላው አገሪቱ በአንክሮ መከታተል ይጀምራል። በድምጽ የታገዘ ፈተና ሲሰጥ፤ ተማሪዎች እንዳይረበሹ በሚል የአካባቢ ጸጥታ የሚያስከብሩ ባለሙያዎች ይሰማራሉ።
ወላጆች ልጆቻቸውን ፈተና መስጫው ቦታ በጊዜ እንዲያደርሱ ሲባል መሥሪያ ቤቶች ዘግይተው ይከፈታሉ።
ወታደራዊ ስልጠና ይቆማል። የአክሲዎን ገበያም ከወትሮው ዘግይቶ ይጀመራል።
ወላጆች ልጆቻቸውን ለፈተናው የሚያዘጋጁት ከሕፃንነታቸው አንስቶ ነው። አብዛኞቹ ልጆች በአራት ዓመታቸው አንዳንዶች ደግሞ በሁለት ዓመታቸው መዘጋጀት ይጀምራሉ።
ኮቪድ-19 እና አስጨናቂው ፈተና
ደቡብ ኮርያ ከተቀረው ዓለም በተሻለ የኮቪድ-19 ተጽዕኖ አላረፈባትም። እስካሁን በቫይረሱ የተያዙት 35,000 ዜጎቿ ናቸው። የሞቱት ደግሞ ከ500 በላይ ይሆናሉ።
መንግሥት ተፈታኞችን ከወረርሽኑ ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎች አውጇል።
ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ወንበሮች በፕላስቲክ መጋረጃ እርስ በእስር እንዲለያዩም ይደረጋል። ተፈታኞቹ ምግብ እና ውሃ ይዘው መገኘት ይጠበቅባቸወል።
በእረፍት ሰዓት ማውራት ክልክል ነው። ወደ ፈተናው ከመግባታቸው በፊት ሙቀታቸው ተለክቶ ትኩሳት ያላቸው ተማሪዎች ለብቻቸው እንዲፈተኑ ይደረጋል።
ተማሪዎች እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች ውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለው ይሰጋሉ።
ጭምብል ማድረግ ትኩረታቸውን የሚሰርቃቸው የሚመስላቸው ተማሪዎች ብዙ ናቸው።
አንዲት ተማሪ ለቢቢሲ ኮርያ ጭምብሉ “የሚያፍነኝ ይመስለኛል” ብላለች። የ18 ዓመቷ ኦ ይዎን ጁ “በፈተናው ቀን ሙቀት እንደሚጨምር ሰምቻለሁ። እናም ጭምብሉ ምቾት ይነሳኛል” ስትል ስጋቷን ገልጻለች።
ወንበሮች እርስ በእርስ መለያየታቸውም ብዙ ተፈታኞችን አስፈርቷል።
“በፕላስቲክ መጋረጃ በተከፋፈሉ ወንበሮች የሙከራ ፈተና ወስደን ነበር። ወንበሩ ጠቦኝ ነበር። እንዲያውም ፕላስቲኩ ወድቆብኝ ነበር። በጣም ጨንቆኝ ነበር። ጓደኞቼም እንደኔው ጨንቋቸዋል” ያለችው የ18 ዓመቷ ሊ ሳንግ ዎን ናት።
ተፈታኟ ረዣዥም የፈተና ወረቀቶችን የምትገልጥበት በቂ ቦታ እንደማይኖራትም ትሰጋለች።
በወረርሽኝ ወቅት ፈተናውን መውሰድ የለብንም ሲሉ ቅሬታ ያሰሙም አሉ።
በሌላ በኩል ፈተናውን በማንኛውም ሁኔታ ተፈትነው መገላገል የሚመርጡም ጥቂት አይደሉም።
መንግሥት ምን አለ?
ፕሬዘዳንት ሙን ጄይኢን ተማሪዎች በወረርሽኝ ወቅት ፈተናውን ለመውሰድ በመገደዳቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።
ሆኖም ግን ግንቦት ላይ አገሪቱ ያለ መሰናክል ምርጫ ማከናወኗ አይዘነጋም። ስኬቱ በብሔራዊው ፈተናም ይደገማል ብለው ባለሥልጣኖች ያምናሉ።
ፈተናው የተማሪዎችን ሕይወት እስከወዲያኛው የሚቀይር እንደመሆኑ ማሸጋገር እንደማይቻልም ተመልክቷል።
ፕሬዘዳንቱ በዚህ ሳምንት ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
“መላው ዓለም ፈተናውን እየተከታተለ ነው” ያሉት ፕሬዘዳንቱ፤ አገራቸው ፈተናውን በስኬታማ መንገድ እንደምታከናውን ገልጸዋል።
ብዙ አገሮች በወረርሽኙ ሳቢያ ብሔራዊ ፈተና አሸጋግረዋል።
ደቡብ ኮርያ ፈተና ማካሄዷ ላይ ጥያቄ ያነሱ የጤና ባለሙያዎች አልታጡም።
በኮርያ ዩኒቨረርስቲ በተላላፊ በሽታዎች ዙርያ የሚሠሩት ፕ/ር ኪም ውጁ፤ “490,000 ተፈታኞች አሉ። 23,000 ሰዎች ፈተናውን ይቆጣጠራሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ወላጆች ልጆቻቸው ፈተናውን እንዲያልፉ ቤተ እምነት ሄደው ይጸልያሉ” ሲሉ ምን ያህል ሰው በፈተናው እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል።
ተማሪዎች በምሳ እረፍት ጭምብላቸውን እንደሚያወልቁና ምንም ያህል ጥንቃቄ ቢደረግ ስምንት ሰዓት በሚወስድ ፈተና ውስጥ ንክኪ ስለሚኖር ለወረርሽኙ የመጋለጥ እድል መኖሩንም አስምረውበታል።
ምንጭ: ቢቢሲ