በሳምንት የ3 ሰዓት የእግር ጉዞ ማድረግ የአዕምሮ መሳትን ያስቀራል

በሳምንት ውስጥ ለሶስት ሰዓት ያህል በእግር መጓዝ የአንጎል ተግባርን በማሻሻል የአዕምሮ መሳትን እንደሚያስቀር አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡

የካናዳ ተመራማሪዎች በሰሩት ጥናት በአንድ ሳምንት ውስጥ በትንሹ የሶስት ሰዓት የእግር ጉዞ ማድረግ፥ በጭንቅላት ውስጥ በሚፈጠር የደም መፍሰስ ምክንያት ከሚመጣ የአዕምሮ መሳት ህመም እንደሚከላከል ይፋ አድረገዋል፡፡

በ38 አዛውንቶች ላይ በተሰራው ጥናትም ለስድስት ወር ያህል በሳምንት ውስጥ ለሶስት ሰዓታት በእግራቸው ጉዞ ያደረጉት የአዕምሯዊ ተግባራቸው መሻሻል አሳይቷል፡፡

በሳምንት ውስጥ የተቀመጠውን ጊዜ ያህል የእግር ጉዞ ያደረጉት አዛውንቶች የማስታወስ አቅማቸውም ጨምሮ ተግኝቷል፡፡

በእግር የሚደረገው ጉዞ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች የደም ዝውውር ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ስለሚያግዛቸው የአዕምሮን ተግባር የሚያውክ የደም መፍሰስ እንዳያጋጥም ያደርጋል፡፡

በጥናቱ ውስጥ የተሳተፉት አዛውንቶች በአንጎል ውስጥ በሚከሰት የደም መፍሰስ የአዕምሮ መሳት የሚያጋጥማቸው እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ ባደረጉት እንቅስቃሴም ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸውን በብሪቲሽ ጆርናል ኦፍ ስፖርትስ ሜዲስን ላይ የሰፈረው ጥናት ያሳያል፡፡

ተመራማሪዎቹ ማንኛውም ሰው በሳምንት ውስጥ ቢያንስ የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ በማድረግ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማዘውተር በአንጎል ውስጥ የሚገኝ የደም ዝውውርን የተሻለ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በተለይም አዛውንቶች በእድሜ መግፋት ምክንያት ብዙ ጊዜ በቤት ውስጥ ስለሚያሳልፉ፥ ከቤት ወጣ እያሉ በእግራቸው መጓዝን መልመድ እንደሚገባቸውም ተመክሯል፡፡

ምንጭ፡-ደይሊ ሜይል

Advertisement