ውበትና ጤና ከወይባ/ከቦለቀያ ጢስ – Buttered and Smoked, Ethiopian Beauty Treatment!

በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ከሚጋሯቸው ባህላዊ የሴቶች መዋቢያ መንገድ አንዱ ጭስ መሞቅ ነው፡፡ ቦለቅያ፣  ወይባ፣ እየተባለ በሚጠራው ጭስ በመሞቅ ለውበትም ሆነ ለጤንነት ክብካቤ ከሚያዘወትሩት አካባቢዎች አንዱ ራያ ነው፡፡ በራያ ድርሳን ላይ እንደተጻፈው፣ ‹‹የራያ ሴቶች ጭስን ለተለያዩ ጥቅሞች የሚሞቁት ሲሆን፣ በዋናነት ለውበትና ለጤናማ ሰውነት ይጠቀሙታል፡፡ የራያ ሴት ጭስን መሞቅ የራሷ፣ የግሏና ከእናቷ የወረሰችውን ባህላዊ ልብሷን ለብሳ ፀጉሯን ሹርባ ተሠርታ፣ ቅቤዋን ተቀብታ፣ ሽርጧን አሸርጣ፣ ጥርቅ ጫማዋን ተጫምታ፣ አሽኩቲና ናትራ ከጆሮዋ ሰክታ ብቅ ትላለች፡፡›› በዚህ ውበቷ የተማረከ የራያ ጉብል የቋጠረላት ስንኝ ነው የዚህ መጣጥፍ መክፈቻ የሆነው፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የፎክሎር ባለሙያዋ ቀለሟ መኮንን በመስክ ባደረጉት ጥናት እንደተመለከተው፣ ከባህላዊ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎች ዛሬ ላይ በዋና ዋና ከተሞች ሳይቀር እየተለመደና እየተስፋፋ የመጣው ባህላዊ የወይባ ጭስ የመሞቅ ሥነ ሥርዓት አንዱና ተጠቃሹ ነው፡፡ በባህላዊ መልኩ የወይባ ጭስ የመሞቅ ሥነ ሥርዓት በአማራ ብሔራዊ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንና አጎራባች ወረዳዎች በስፋት የሚከወንና የየአካባቢው መገለጫ እሴት ነው፡፡ በዞኑ በሚገኙት በባቲ፣ በከሚሴና ዙሪያዋ የሚከወነው ባህላዊ የወይባ ጭስ የመሞቅ ሥነ ሥርዓት በአካባቢው አጠራር ‹‹ቦለቀያ›› ይባላል፡፡

እንደ ባህል ባለሙያዋ አገላለጽ፣ ‹‹ቦለቀያ›› የሚለው ቃል መገኛው የኦሮምኛ ቃል ሲሆን፣ ‹‹ቦለ›› ማለት ጉድጓድ ሲሆን፣ ‹‹ቀያ›› ማለት ደግሞ የተቆራረጠ የወይባ እንጨትና ጭስ ነው፡፡ በሌላ በኩልም በራያ አካባቢ ቦሎቅያ የሚለው ስያሜ ከጉድጓድ ውስጥ ቆረጥ ቆረጥ እያለ የሚወጣውን ጭስ የአካባቢው ኅብረተሰብ ቡልቅ ብሎ ጭስ ወጣ ለማለት እንደሚጠቀሙበት ይነገራል፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በተለይም በባቲ ወረዳ ብሬንሳ፣ መለሆ የተባሉ የወይባ ዛፎች በስፋት ስለሚገኙ በአካባቢው ሴቶች በባህላዊ መልኩ የወይባ ጭስ የመሞቅ ሥነ ሥርዓት የቆየ ባህልና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የወይባ ጭስ የሚሞቁት ያገቡ ሴቶች፣ ልጅ የወለዱ አራስ ሴቶችና የልጆች እናት ሲሆኑ፣ በተለይ አንዲት አራስ በአራስነት ጊዜዋ የወይባ ጭስ መሞቅ የየዕለት ተግባሯ ነው ማለት ይችላል፡፡

 የወይባ ጭስ መሞቅ ባላገቡ ልጃገረዶች የተለመደ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የወይባ ጭስ ለመልካም ጠረን ሲባልም ስለሚሞቅ፡፡ ይህ ደግሞ ያላገቡ ልጃገረዶችንና ወጣቶችን ለጾታዊ ግንኙነት ይገፋፋል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ይህን ከጋብቻ በፊት ያለን ጾታዊ ግንኙነት ለመከላከል ሲባልና ባህሉም ስለማይፈቅድ ጭምር የተለመደ አለመሆኑንና እንደማይደረግ አስረጂዎች ይናገራሉ፡፡

በባህላዊ መልኩ የሚዘጋጀውን የወይባ ጭስ ለመሞቅ ከግብዓት አቅርቦት እስከ አገልግሎት ድረስ የራሱ የሆነ የቅድመ ዝግጅት ሥርዓት አለው፡፡ በዚህም ከግብዓት አኳያ የወይባ እንጨት፣ የምትሞቀዋ ሴት በምትሞቅበት ጊዜ ሙሉ አካላቷን እስከ አንገቷ ድረስ የምትሸፈንበት (የምትለብሰው) ከከብት ቆዳ የሚዘጋጀው በኦሮምኛ ‹‹ኢቲሌ›› ተብሎ የሚጠራው ጀንዴ፣ ጭሱን ከመሞቋ በፊት ሰውነቷን የምትቀባው ቀሉ (ለጋ ቅቤ)፣ የምትሞቀው ሴት አራስ ከሆነች አጥሚት፣ ገንፎ ወይም ሳቱ (ከማሽላ ወይም ከሽንብራ የሚዘጋጅ ንፍሮ) በማር ወይም በወተት ተዘጋጅቶ፣ ምግቦቹን ለማብሰያ እሳት፣ ጭሱን ሞቃ መጨረሻ ላይ ታጥባ ስትወጣ የምትሞቀው እንደ ሶርሳ፣ መስከቲ፣ ጃዊ፣ ወዘተ… የመሳሰሉ ጭሳጭሶች ያስፈልጋሉ፡፡

 ከግብዓቱ አቅርቦት በኋላ ለጭስ መሞቂያው ምቹ በሆነ መልኩ ጉድጓድ ይቆፈራል፡፡ የወይባ ጭስ የመሞቂያ ቦታ (ጉድጓድ) የሚዘጋጀው እንደ ሁኔታው በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ሆኖ፣ ከቤት ውጪ ከሆነ ሰው በማያየው የተከለለ ሥፍራ፣ በቤት ውስጥ ከሆነ ደግሞ አመቺ ቦታ ላይ ይዘጋጃል፡፡ ጉድጓዱ ከተዘጋጀ (ከተቆፈረ) በኋላ ጭቃ ይቦካል፡፡ ጭቃው ከተቦካ በኋላ በጭድ ይለወሳል፡፡ ከዚያ አንድ አንድ ክንድ የሚሆኑ እንጨቶች ተቆርጠው ይዘጋጁና ጉድጓዱ አፍ ላይ ዙሪያውን እንደ አጥር ይታጠራሉ፡፡ ከዚያ በተዘጋጀው ጭቃ ይመረጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተመረገው ጉድጓድ ለሦስት ቀናት ያህል ካደረ በኋላ በከብት እበት ይለቀለቃል፡፡ በዚህ መልኩ አንድ ጊዜ የመሞቂያ ቦታው ከተዘጋጀ በኋላ በተፈለገ ጊዜ መጠቀም ይቻላል፡፡

በዚህ መልኩ ጉድጓዱ ከተዘጋጀ በኋላ የወይባ ዛፉ ምቹ በሆነ መልኩ እስከ አንድ ስንዝር ድረስ ዘለግ ተደርጎ ይቆራረጥና ይፈለጣል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት አባወራዎች/ባሎች/ናቸው፡፡ ለቦለቀያ ያልደረቀው እርጥቡ የወይባ ዛፍ ቶሎ ተቀጣጥሎ የሚሞቁ ሴቶችን ለጉዳት የማይዳርግ በመሆኑ ይመረጣል፡፡ ከዚያም የተፈላለጠው የወይባ ዛፍ በመጠኑ ተደርጎ በጉድጓዱ ላይ እንዲጨስ እንዲቀጣጠል ይደረጋል፡፡ ከተቀጣጠለ በኋላ የወይባ ጭሱን ለመሞቅ የምትቀርበው ሴት የለበሰችውን ሙሉ ልብስ በማውለቅ ከጉድጓዱ ፊት ለፊት በተዘጋጀው መቀመጫ ላይ ትቀመጣለች፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ለመልበስ የተዘጋጀውን ቆዳ (ጀንዴ) በጓደኛዋ አማካይነት እስከ አንገቷ ድረስ ያለውን የሰውነት ክፍል ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ትለብሳለች፡፡

ከዚያም የወይባ ጭሱን ለመሞቅ በቦለቀያ ላይ የተቀመጠችው ሴት ሙሉ አካሏን ቀሉ (ለጋ ቅቤ) በስሱ ትቀባለች፡፡ ይህ የሚደረገው ሰውነቷ እንዲያምርና እንዲለሰልስ ለማድረግ ነው፡፡ የወይባ ጭሱን ለመቋቋምም በቅድሚያ በቂ ምግብ ትመገባለች፡፡ ሲያስፈልጋትም በመሀል ‹‹ሳቱ›› ተብሎ የሚጠራውን ንፍሮ ትመገባለች፡፡

የወይባ ጭሱን የምትሞቀዋ ሴት አራስ ከሆነች በቅድሚያ ገንፎ፣ አጥሚት፣ ሳቱ (ንፍሮ) ወይም ወተት ሊቀርብላት ይችላል፡፡ የወይባ ጭስ መሞቅ ለአራስ ሴቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ ከጠቀሜታዎቹ መካከል ሰውነታቸውን ለማጠንከር፣ ለመጠገን፣ ለጤንነትና ለውበትም ጭምር ያገለግላል፡፡ በአራስነት ወቅት ከሚመገቧቸው ምግቦች ለምሳሌ ሳቱ (ንፍሮ) ጡታቸው እንዲያግት (ወተት እንዲኖረው) በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በተጠቀሰው መልኩ ቅድመ ዝግጅቶቹ ተሟልተው የወይባ ጭሱን ለመሞቅ የገባችው ሴት እንደ ሁኔታው ለግማሽ ወይም ለአንድ ሰዓት ያህል ትቆይና ትወጣለች፡፡ ከዚያ የወጣውን ላብ ለማውረድ ገላዋን ትታጠባለች፡፡ ይህ የገላ መታጠቢያ የሚዘጋጀው ከወይባው ዛፍ ቅርፊትና ‹‹ጣጢሳ›› ተብሎ ከሚጠራ የዛፍ ቅጠል ሲሆን፣ አዘገጃጀቱ አንድ ላይ በማዋሀድ በቶፋ ወይም ከሸክላ በሚዘጋጅ መቀቀያ እንዲንፈቀፈቅ ተደርጎ ወይባዋን ሞቃ ስትጨርስ እንድትታጠብበት ይደረጋል፡፡ ሁለተኛ መግባት ከፈለገች ሰውነቷን አቀዝቅዛ እንደ አዲስ የወይባውን እንጨት በማያያዝ መሞቅ ትችላለች፡፡

ሁለተኛ ከተገባ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ገላዋን መታጠብ ላይኖርባት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ለመጀመርያ ዙር የሰውነቷን ላብ ስላወረደች ሁለተኛ የተሞቀውን ወይባ ሳይታጠቡ መተኛት የሚያስፈልጋቸው ወይባውን የሞቀችው አዲስ ሙሽራ ከሆነች ወይም የልጆች እናት ሆና ሞቃ ስትጨርስ በቀጥታ ወደ ባሏ ስለምትሄድ ነው፣ ወይም ሁለተኛውን ዙር ሞቃ ወይባው ገላዋ ላይ እንዳለ ጥሩ መዓዛ ስለሚኖረው በዚያው ሽንት ቤት ከሄደች በኋላ ስትመለስ በገል/በሸክላ ስባሪ እሳት በማድረግ ምጥን ጭስ ትሞቅና ወደ መኝታዋ ትሄዳለች፡፡

የወይባው ቅርፊትና የጣጢሳ ቅጠል ሲዋሀድ ውበት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የወይባው ቅርፊት ሲንፈቀፈቅ ቢጫ ቀለም ያለው ሲሆን፣ የምትታጠበው ሴት ቆዳዋ ቢጫ ቀለም ሲለብስ የቆዳ ጥራት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ጣጢሳ›› የሚባለው የዛፍ ቅጠል ጥሩ መዓዛ ያለው በመሆኑ የተሻለና ጥሩ መዓዛ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡

የወይባ ጭስን በተፈለገና በተመቸ ጊዜ መሞቅ የሚቻል ቢሆንም፣ ጠዋት ወይም ማታ ተመራጭ ጊዜያት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

ለምሳሌ አዲስ ሙሽራ ከሆነች ብዙም ሥራ እንደወላዶች ስለማይበዛባት ጠዋት ላይ ወይባዋን ባሏ አዘገጃጅቶላት ያስቀምጥላትና ከሰዓት በኋላ ላይ ሥራዋን ስትጨርስ ወደወይባዋ ትገባለች፡፡ ከዚያም እስከ ምሽት ድረስ ጥሩ መዓዛ ኖሯት ወደመኝታዋ ትሄዳለች፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከሰዓት በኋላ የሚሞቅ ወይባ በተለይ ለወጣት ሙሽራ ሴቶች ውበትንና ጥራትን ያጎናጽፋል ሲሉ አስረጂዎች ይናገራሉ፡፡ የልጆች እናት የሆኑና ሥራ የሚበዛባቸው እናቶች ደግሞ ወደማታ ላይ ሥራቸውን ሲያጠናቀቁ ወይባ ይገባሉ፡፡ ከዚያም በቀጥታ ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ፡፡

የወይባ ዛፍ መሞቅ ለቆዳ ጥራትና መልካም ውበትን ለመላበስ፣ ሰውነት ጥሩ ጠረንና መዓዛ እንዲኖረው ለማድረግና በተለይ ለወላድ ሴቶች የተከፈተ ሰውነትን በመጠገን፣ በመድፈን ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

ከዚሁ የወይባ ዛፍ ጋር እንደ ብሳና፣ አጋም፣ እሬት፣ ምስርችና ጉመሮ የተባሉ የዛፍ ዓይነቶች ከወይባ ዛፉ ጋር አብሮ መሞቅ ለበርካታ በሽታዎች ለአብነት ያህልም ለሰውነት ቁርጥማት፣ ለእግርና ለአጠቃላይ ሰውነት መተሳሰር፣ እንዲሁም ለወገብ በሽታና ድብርትን በመቅረፍ ረገድ ፈዋሽ መሆኑን መረጃ ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

የራያ ጉብል ከዘመኑ ሽቶ ይልቅ ከእናቷ የወረሰችውን ባህላዊ መዋቢያ እንደምትጠቀም ለመግለጽ ከባሌዎቹ የቋጠሩትን ስንኝ ድርሳነ ራያ እንዲህ ከትቦታል፡-  

‹‹ውብም አላየሁም እንዳንች ያማረ
       የቦሎ – ቅያው ጭስ ቆንጆ ልጅ ፈጠረ!››

Advertisement