በከምባታ ጠምባሮ ዞን የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ሥፍራዎች የሀምባሪቾ ተራራ፣ የአጆራ ፏፏቴና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ ሆኖም እነዚህን መስህቦች ለገብኚዎች አመቺ አድርጎ ሕዝቡንና አገርን አብዝቶ ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም፡፡
በመሆኑም ዞኑ የሕዝቡን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ለማፋጠንና ተጠቃሚ ለማድረግ ‹‹ታሪክ ለዋጭ›› ያላቸውን 13 ፕሮጀክቶች ነድፎ እየሠራ ይገኛል፡፡
ከነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ የሀምባሪቾ ቱሪዝምና ግሬን ዲቨሎፕመንት ፕሮግራም ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም የሀምባሪቾ ተራራን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
የተራራውን ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ በውስጡ የያዛቸውን ታሪካዊ ክስተቶችና ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ከሚከናውኑት የልማት ሥራዎች የተለያዩ የመዝናኛ ሎጆች፣ የመንገድ መሠረተ ልማቶችና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
የባለሀብቶችን ትኩረትና የጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ እየለማ ካለው የሀምባሪቾ ተራራ ሥራዎች ውስጥ 777 ደረጃ ያለው የተራራው መወጣጫ ተጠናቆ ተመርቋል፡፡
ከዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ 777 የተራራ መወጣጫ ደረጃ በዞኑ የቱሪዝም ልማቱን ለማሳደግና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
የሀምባሪቾ ተራራ መወጣጫ 777 ደረጃ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ሰሞኑን ሲመረቅ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ መሄዶ፣ በዞኑ የቱሪዝም ልማት የታቀዱ ፕሮጀክቶችን በመተግበር የዞኑንና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሀምባሪቾ ተራራ ላይ በሰኔ 2012 ዓ.ም. መከናወኑ ይታወሳል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን ተግባራዊ ለማድረግ በክልሉ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡
ለከምባታ ጠምባሮ ዞን አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የውሃ ማማ የሆነውን የሀምባሪቾ ተራራን ማልማት ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ ለሌሎች አጎራባች ዞኖችም የውሀ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡
ከባህር ጠለል በላይ 3ሺ 38 ሜትር ላይ የሚገኘው የሀምባሪቾ ተራራ ለቱሪዝም ዘርፉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ሀምባሪቾ ቱሪዝም እና ግሪን ዲቨሎፕመንት ፕሮግራም በአራት ወረዳዎች የሚገኙ 21 ቀበሌዎችን የሚያቅፍና 650 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ፕሮጀክት ነው፡፡
የሀምበሪቾ ቱሪዝም እና ግሪን ዲቨሎፕመንት ፕሮግራም አካል በሆኑ 21 ቀበሌዎች ለሚገኙ 1538 አርሶ አደሮች ከ8000 በላይ የተከተበ የአቮካዶ እና የማንጎ ችግኞች ማሰራጨትም ተችሏል፡፡
የሀምባሪቾ ቱሪዝም እና ግሪን ዲቨሎፕመንት ፕሮግራም የሀምባሪቾ ተራራ እና ተፋሰሱ ያለበትን ስነ ምህዳር የዕጽዋት፣ የዱር እንስሳት፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በጥልቀት በመለየት እና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትን እውን ለማድረግ ትኩረት የተሰጠው ነው ተብሏል፡፡
የሀምባሪቾ ተራራን ወደ ቀድሞ ይዞታው በመመለስ የምርምር ማዕከል እንዲሆን ከማስቻል ባለፈ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር የስራ እድል ፈጠራ ላይ በማተኮር፣ ተራራውን በማልማት የአካባቢውን ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ምንጭ: ሪፖርተር