የገና ጨዋታ ደረሰ መጫወቻ ሜዳውስ?

ትውፊታዊው የገና ጨዋታ በወርኃ ታኅሣሥ ከእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጨዋታ ነው፡፡ ገጠር ከከተማ ወጣቶችና ጎልማሶች የሚያዘወትሩት ቢሆንም፣ አዛውንቶች መርቀው ከመክፈት ባሻገር አልፎ አልፎ የሚጫወቱ አይጠፉበትም፡፡

እንደ የአካባቢው ልማድ የገና ጨዋታ የታኅሣሥ ወር እንደገባ የሚጀመሩ ሲኖሩ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከወሩ አጋማሽ ይጀምሩታል፡፡

መንፈሳዊና ባህላዊ ክብረ በዓሉ በኢትዮጵያ ዓውድ ከገና ጨዋታ ጋር ተያይዞ  ከሚከበርባቸው ስፍራዎች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ጃንሜዳ ተብሎ የሚታወቀው ቦታ እጅግ ገናን ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከተቆረቆረችበት ዘመን አንስቶ የልደት በዓልን ተከትሎ በጃንሜዳ የገና ጨዋታ ሲካሄድ ኖሯል፡፡ የገና በዓል መዳረሻ ላይ የባህል ስፖርቶች ውድድር ማካሄድን ትኩረት ይሰጥ የነበረው የአዲስ አበባ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ዘንድሮ ድምፁ አልተሰማም፡፡

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለዓመት ያህል የአትክት ተራ መገበያያ ሥፍራ ሆኖ ያሳለፈውና በቅርቡ እንዲፀዳ የተደረገው ጃንሜዳ ለጥምቀት- ከተራ በዓል ማስተናገጃ እንደሚውል ከመገለጹ ባለፈ፣ የገና ጨዋታን ያስተናግድ አያስተናግድ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ዓምና አሥረኛው የባህላዊ ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል የገና ጨዋታ፣ ትግል፣  ቀስት፣ ገበጣ፣ ፈረስ ጉግስ፣ ፈረስ  ሸርጥና ኮርቦን ጨምሮ በ12  ባህላዊ  የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች ለአንድ ሳምንት በጃንሜዳ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡

የገና ጨዋታ ይዞታ

በዓሉ በሁለት ቡድኖች መካከል ሚና ለይተው በሚጫወቱበት ጊዜ ተጫዋቾቹም ሆኑ ታዳጊዎች በሆታና በዕልልታ ከሚያዜሟቸው መካከል፡

«አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡

ኦ! ኦ! አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡

ማታ ነው ድሌ፣

ይሄ ነው አመሌ፡፡›› ይጠቀሳል፡፡

ስለ ጃንሜዳ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያጠኑት አቶ አባይነህ ደስታ፣ ጃንሜዳ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብ ተሰብስቦ ከሚያከብራቸው የክርስቲያኖች በዓል ገና እና ጥምቀት ዋነኛ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የገናን ሀገር ባህላዊ ጨዋታን ስንመለከት አስቀድሞ የቡድን አባላት የሚሆኑ ሁለት ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ ሁለት ሁለት ተጫዋቾች ወደ አባቶች ይቀርቡና በምርጫው ወደ ቡድን ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሚያስፈልገው የተጫዋች ቁጥር ሲሞላ ወገን ወገናቸውን ይዘው በዱላ ቀልጣፋ የሆኑ ተጫዋቾች ጥንጓን ወደፊት እንድትቀጥል ይመቷታል ወይም ይመልሷታል፡፡ ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ በጨዋታው ስለሚሰጡ ጥንጓን ከእግር መካከል በገባች ጊዜ ከሰው እግር ጋር ደርበው ስለሚመቱ የእግር መሰበር በዚህም ሳቢያ ወገን ለይተው እስከመፈናከት ይደርሳሉ፡፡ የመኳንንቱም አሽከሮች፣ የንጉሡና የንግሥቲቷ አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም በጉብዝና የሚያስጠሩት በባህላዊው የገና ጨዋታ ነው፡፡  

ጨዋታው በመንደር ልዩነት ከሆነ የታች አምባ ቡድን ሀምሳ ተጫዋቾች ቢሆኑ የላይ አምባ ቡድን ሰባ ሆነው ቢጫወቱ የሚከለክል ደንብ አልነበረም፡፡ ጨዋታው በመጨረሻ ፀብ ስለሚያነሳ ብዙ ጊዜ ጉዳት ያጋጥማል፡፡ ጥንጓም ኃይለኛ ለጊ በመታት ጊዜ ዐይን እስከ ማጥፋት ትደርሳለች፡፡ ተጫዋቾች «በሚና» ብለው በሚጫወቱበት በቆልማማ ዱላ ቢደባደቡም የሚገላግል ዳኛ አልነበረም፤ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ ከመሳቅ በስተቀር ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አልተለመደም፡፡ «እግር ይብሳል፣ ያንከላውሳል፡፡» እያለ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት በገና ጨዋታ የተለመደ ነበር፡፡

የገና ጨዋታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች የታወቀውና በኦሊምፒክ የስፖርት በዓል ከሚደረጉ ውድድሮች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ጨዋታ ሆኪ በሚል ስም ይጠራል፡፡ ፈረንጆች የፊት አደጋን መከላከያ ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያገር ባህል ገና ጨዋታ በሚደርስ አደጋ ማንም ተጫዋች አይጠይቅም፡፡

በገና ጨዋታ አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፊሪዳና ጠጅ ተሰጥቷቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ሜዳውን የጦርነት ድል ያገኙበት ያስመስሉት ነበር፡፡ ከሚዘፍኑትና ግጥሞች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

«ማታ ነው ድሌ፣

ይሄ ነው አመሌ፡፡

አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡

ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡

ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው፣

የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው፡፡

የብብቱ ሽታ፣ የመንፈቅ በሽታ፡፡

የጀርባው መርሬ፣ ያውላል ጥድ በሬ፡፡

ካስር ጋን አተላ፣

አይተርፈው በአንኮላ፡፡

እግርህ የሸረሪት ሆድህ የእንቁራሪት፣

ቀን እንደጠላሁ ና እንዳትመጣ ሌሊት፡፡»

ስድብ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመኳንንቱና በነገሥታቱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል፡፡ በሚደርስባቸው ስድብ ግን ምንም ዓይነት ቁጣና ቅጣት አያደርጉም፡፡

«በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ

በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፡፡» የሚለው የዘፈን ግጥም ይህን ባህል ይገልፃል፡፡

የገና ጨዋታ ከክርስትና ሃይማኖት በፊት ይዘወተር እንደነበርና በኢትዮጵያ ከታኅሣሥ የመኸር ወቅት ጋር የተያያዘ ባህል እንደሆነ አቶ አባይነህ ያመለክታሉ፡፡ ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ብዙ የስነቃል ግጥሞችን ይገኛሉ፡፡

«ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣

እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡

ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣

ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና፡፡

ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣

ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ፡፡

በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣

እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ፡፡»

ምንጭ: ሪፖርተር

Advertisement