የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች አንዳሉት ይታወቃል፤ በቅርቡ የወጣ ጥናት ደግሞ የአካል ብቃት አንቅስቃሴ ከድብርት ለመላቀቅ ፍቱን ነው ይላል።
ተመራማሪዎች ለ30 ዓመታት ተካሄደ ባሉት ጥናታቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ድብርትን በማስወገዱ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል።
በአውስትራሊያ ተመራማሪዎች የተመራው እና በአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ሳይካትሪ ላይ በታተመው የጥናት ውጤት እንደተገለጸው፥ በጥናቱ በ22 ሺህ 500 ኖርዌያውያን ላይ ክተትል ተደርጓል።
በዚህም በሰዎች ላይ ከሚከሰቱ አዳዲስ ድብርቶች ወስጥ 12 በመቶ ያክሉ በሳምንት ለ1 ሰዓት ብቻ በሚሰራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መከላከል እንደሚቻል ተለይቷል።
በኤን.ኤስ.ደብሊው ዩኒቨርሲቲ ብላክ ዶግ ኢኒስቲቲዩት ሳይካትሪስት እና ኢፒዲሞሎጂስት የሆኑት የጥናት ቡድኑ መሪ ሳም ሀርቬይ፥ የምንሰራው የአካል ብቃት መጠን እና አይነት ምንም ችገር የለውም ይላሉ።
ዋናው ጥቅም የሚገኘው ሰዎች በሳምን ውስጥ ምንም ካለመስራት ወደ የአንድ እና የሁለት ሰዓት አካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሰሩ በማሸጋገር ነው ብለዋል።
በጥናቱም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትረው የሚሰሩ ሰዎች ለድብርት የመጋለጥ አድላቸው በ41 በመቶ የቀነሰ መሆኑም ተለይቷል ብለዋል።
ይህም በዓመት 100 ሺህ የሚደርሱ የድብርት ህክምናዎችን ሊያስቀር ይችላል የተባለ ሲሆን፥ ለጤና የሚወጣን በቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚቆጠሩ ገንዘቦችንም ለመቆጠብ ያስችላል ነው የተባለው።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)