የአዕምሮ በሽታ ብቸኛ በሆኑ ሰዎች ላይ እንደሚበረታ ተገለፀ

ብቻቸውን የሚኖሩ ሰዎች ለጭንቀት፣ ውጥረት እና ለተለያዩ የአዕምሮ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በብሪታኒያ የሚገኙ ተመራማሪዎች በፕሎስ ዋን ጆርናል ባሳተሙት አዲስ ጥናት መሰረት ለሁለት አስርት ዓመታት ሶስት ምርምሮችን በማድረግ ከዚህ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ ባካሄዱት የክትትል ስራ ብቸኛ የሆኑ ሰዎች ብቻቸውን ከማይኖሩት አንጻር ለአዕምሮ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጥናት በፈረንጆቹ 1993፣ 2000 እና 2007 ባሉት ጊዜያት በብሪታኒያ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ ጎልማሳዎች የተሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጥናት ውጤት መሰረትም ከ1993 እስከ 2007 መካከል ባሉት ጊዜያት ብቻቸውን ሲኖሩ የነበሩት ከ8 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 10 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፥ የአዕምሮ በሽታም ከ14 ነጥብ 1 ወደ 16 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

ብቸኛ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰተው የአዕምሮ በሽታ ያለ እድሜ ልዩነት በማንኛውም አካል ሊከሰት የሚችል መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

አንዳንድ ጊዜም ብቻቸውን በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚከሰተው የአዕምሮ በሽታ ከሰው ጋር ከሚኖሩት ጋር ሲነጻፀር የሁለት እጥፍ ብልጫ እንደሚኖረው ነው የተነገረው፡፡

በፊንላንድ በተመሳሳይ በተካሄደ ጥናት ብቻቸውን የሚኖሩ 5 ሺህ ሰዎች ከባለትዳሮች አንጻር ለጭንቀት እና ውጥረት የነበራቸው ተገላጭነት ከፍ ብሎ እንደተገኘ ነው የተመለከተው፡፡

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

9 Comments

Comments are closed.