በሥራ ቃለ መጠይቅ ወቅት ልንላቸው የማይገቡ 7 ነጥቦች

በሥራ ቃለ-መጠይቅ ወቅት ያልተጠበቁ ነገሮች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ መቼ እረፍት እንደሚወጡ የሚጠይቁ፣ ስልክ የሚያናግሩ፣ ስለቀድሞ አለቃቸው መጥፎ ነገር የሚያወሩ እና ሌሎችም. . . እነዚህ ነገሮች ብዙ ሲሆኑ የማይገባ ነገር በመናገርም ሥራውን የማጣት ዕጣም ይገጥማል።

በሥራ ቃለ-መጠይቅ ወቅት ልንናገሯቸው የማይገቡ ነገሮችን ከቅጥር ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር እንደሚከተለው ቀርበዋል።

1. “አለቃዬ ብቁ አይደለም”

ባለሙያዎች በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

“የቀድሞ አለቃዎትን የሚያጣጥል ነገር የሚያወሩ ከሆነ ቀጣይ አለቃዎን ስላለማጣጣልዎ ምንም ማረጋገጫ አይገኝም” ይላሉ የቢቢሲ ሙንዶው ሠራተኞች ዳይሬክተር ሉዊስ ሪቫስ።

ስለዚህ ከቀድሞ አለቃችን ጋር አለመግባባት ካለ ብንተወዉ ይመረጣል።

2. “የአሁኑን ሥራዬን አልወደውም”

ይህ ትክክል ቢሆንም ማለቱ ግን ተገቢ አይደለም።

አሉታዊ ስሜት ያለውን አስተያየት ወደጎን መተው አስፈላጊ መሆኑን እና እንደ “አዲስ ፈተና ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” የሚሉ አይነት አስተያየቶችን እንድንጠቀም ባለሙያዎች ይመክራሉ።

3. “ምንም ደካማ ጎን የለኝም”

ይህ ቃለ መጠይቅ የሚደረገውን ሰው እብሪት ከማሳቱም በላይ እራስን መለስ ብሎ ለመመልከት የማይፈልግ ሰው እንደሆንና በበጎ መልኩ የሚሰጡ አስተያየቶችንም ለመቀበል አለመፈለግ እንዳለ የሚያሳይ ነው።

“ብቸኛው ችግሬ ሁሉም ነገር ፍጹም እንዲሆን መጠበቄ ነው” የሚል አይነት የተለመዱ አገላለጾችን ማስወገድ እንደሚገባም ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

4. “ይህ ሥራ ምን ያህል የዕረፍት ቀናት አሉት?”

የመጀመሪያ የሥራ ቃለ መጠይቅ ከሆነ ሥራውንም እንዳገኘን ስላልተረጋገጠ እና የሚከፈለው የደሞዝ መጠንና ጥቅማጥቅሞችን ጨምሮ ሌሎች ነጥቦች ስለማይታወቁ በጥልቀት ወደ ጉዳዮች መግባት አያስፈልግም።

“ለዕረፍት የሚሆን ትኬቶች አገኛለሁ?” ተብሎ የሚጠየቀው ሥራውን እንዳገኘን ሲነገረን ወይም ሥራው ቢሰጠን ምን ያህል ጊዜ ውስት እንደምንጀምር ስንጠየቅ ብቻ ነው።

ስለደሞዝ ቀድመው አይጠይቁImage copyrightISTOCK

5. “ድርጅትዎ ምን ይሠራል”

ይህንን በፍጹም ልንጠይቅ አይገባም።

“ብዙ ጊዜ ስለድርጅቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ አለብዎት” ሲሉ በሠራተኞች ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት አሊሰን ዶይል ለቢቢሲ ዎርልድ ገልጸዋል።

“ቀጣሪዎችዎ እነማን እንደሆኑ ያጥኑ፣ ድረ ገጻቸውን ይጎብኙ፣ የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን እና ስለድርጅቱ የሚያትቱ ዜናዎችን መከታትል አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ስለድርጅቱ በይፋ የማይታወቁ ነገር ግን በምናውቃቸው ሠዎች በኩል የሚገኙ መረጃዎች ካሉ መፈለግ ጥሩ መሆኑን ዶይል ያብራራሉ።

6. “ደሞዙ ምን ያህል ነው?”

ስለደሞዝ ጉዳይ ቀደመን አናንሳ። ቃለ መጠይቅ የሚያደርገን ሠው እስኪያነሳው ድረስ እንጠብቅ።

“ቀደም ብለው ስለደሞዝ ጥያቄ ማቅረብ የለብዎትም። ምክንያቱም ለሥራው ብቁ ተብለው ለቅጥር አልታሰቡ ይሆናል” ይላሉ ዶይል።

“ጥሩ የሚሆነው የሚጠይቅዎት ሠው ስለደሞዝ ካነሳ ነው። ይህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በስፋት ለማውራት ዕድል የሚፈጥር ይሆናል” ሲሉም ይመክራሉ።

7. “ይህን ሥራ በጣም እፈልገዋለሁ”

ሥራውን በጣም የምንፈልገው መሆኑን መሳየት ተገቢ አይደለም። ሊናገሩ የሚገባዎት በሥራው ላይ ጥሩ ፍላጎት እንዳለንና እና ለዚህም የሚሆን ብቃት እንዳለን ብቻ ነው።

ቃለ መጠይቅ አድራጊዉን ለማማለል አይሞከሩ። ስለፖለቲካ ወይንም በራስ መተማመን ማሳየት በሚገባዎት ቦታ እየማሉ አይናገሩ።

በመጨረሻው ባለሙያዎችን የማያስማማው ነጥብ

“ከማንም በላይ ለዚህ ሥራ የምመጥነው እኔ ነኝ” በሚለው በዚህ አባባል ላይ በባለሙያዎች ዘንድ መግባባት የለም።

አንዳንዶች ይህ ያለንን ጥንካሬ እና በራስ መተማመን ያሳያል ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ተፎካካሪዎቻችንን በማናውቁበት ሁኔታ ራስን ይህን ያህል ከፍ ማድረግ ተገቢ አይደለም በሚል ይሞግታሉ።

በሌላ ጥግ ደግሞ “ለዚህ ሥራ በጣም ብቁ ነኝ ብዬ ባላስብም እማራለሁ . . .” ማለትም አይመከርም።

በአጠቃላይ ለሥራ ቃለ መጠይቅ በምንቀርብበት ወቅት ያለንን ደካማ ጎን ከማሳየት ይልቅ ያለንን ተግባራዊ ልምድ መግለጽ ተገቢ ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.