ታምሩ ዘገዬ፡ በክራንች ተገልብጦ በመሄድ የ100 ሜትር የክብረወሰን ባለቤት

ታምሩ ዘገዬ ተገልብጦ በክራንች በመሄድ 100 ሜትርን በ57 ሰከንድ በማጠናቀቅ ከአራት ዓመት በፊት በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሯል።

የአንደኛ ክፍል ተማሪ እያለ አንድ እንግዳ በቴሌቪዥን ቀርቦ ተመለከተ፤ቀልቡን ሳበው፤ ራሱን በእንግዳው ቦታ አድረጎ ደጋግሞ አሰበው። ሲነሳም ሲቀመጥም፤ ሲበላም ሲጠጣም ይህንኑ ማሰላሰል ያዘ። ጉዳዩን ከራሱ ጋር በሚያደርገው የሃሳብ ትግል ብቻ ሊተወው አልሻተም። በእግሩ እያዘገመ ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው አመራ።

ገና ሲቃረብ በር ላይ ለሚሰሩ ጥበቃዎች ምን እንደሚላቸው አላወቀም። ብቻ በውስጡ እንደ ደራሽ ጎርፍ የሚገፈትረው ህልም አለ። ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ውስጡ ነግሮታል።

በሩ ጋር ሲደርስ ያው ደንብና የስራ ኃላፊነት ነውና ጥያቄው አልቀረለትም። ማነህ? ከየት ነህ? ወዴት ነህ? የተለመዱ ጥያቄዎች፤

በጥያቄዎቹ አልፈራም፤ አልተደናገጠም። በጨዋ ደንብ አስረዳቸው፤ እንዲገባም ፈቀዱለት፤ ደስታው ወደር አልነበረውም።

ወደ ጣቢያው እንደገባ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ይተዋወቃል።

“ምን ሆነህ ነው የመጣኸው?” ሲሉ ይጠይቁታል።

” ችሎታየን ለማሳየት ፈልጌ ነው!”ሲል በጉጉት ይመልሳል።

“ምን ዓይነት ችሎታ ነው ያለህ?” በዝርዝር አስረዳቸው።

“አሳየና! ” ይሉታል። የት ላይ እንደሚያሳያቸው ቦታ ለመምረጥ ዙሪያውን ማማተር ጀመረ።

በርግጥ በቴሌቪዥን መስኮት ያየው ሰው በእጁ ተገልብጦ በመሄድ 21 የፎቅ ደረጃዎችን በመውረድ ነበር ተመልካቹን አጃኢብ ያሰኘው፤

ዙሪያውን ገልመጥ ገልመጥ ብሎ ተመለከተ በወቅቱ የነበረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሮ 12 ፎቅ ብቻ ነበረው።

ታምሩ ሰርከስ በማሳየት ላይImage copyrightTAMIRU ZEGEYE

‘ከሰውየው የበለጠ መስራት እችላለሁ’ እያለ ከቤቱ ቢወጣም ችሎታውን የሚሳይበት ቦታ አነሰበት፤ ግራ ተጋባ።

“ግድ የለም አሳየን” አሉት ግራ እንደተጋባ የተረዱት ጋዜጠኞቹ፤

በደስታ እየቦረቀ በወቅቱ ጣቢያው ያለውን 12 ፎቅ በእጁ ተገልብጦ ወረደ።

“ያኔ በቴሌቪዥን የተመለከትኩትና በድንቃ ድንቅ መዝገብ ስሙ የተጻፈው ግለሰብ 21 ፎቅ ነበር የወረደው፤ጣቢያው ከዚያ በላይ ፎቅ ቢኖረው እኔም ከ12 ፎቅ በላይ የመሄድ አቅሙ ነበረኝ” ሲል ያስታውሳል።

አሁን አሁን ብዙዎች በእግር ቀስ እያሉ ለመውረድ እንኳን ተስኗቸው አሳንሰር የሚያዙለትን ደረጃ ታምሩ ግን እግሮቹን ወደላይ አንጨፍርሮ በእጆቹ የእግር ያህል ተራመዳቸው።

ሲመለከቱት የነበሩት ጋዜጠኞችም መዳፋቸውን አፋቸው ላይ ጫኑ፤ ተደመሙ። ከዚያም እርሱን በጠራው የቴሌቪዥን መስኮት እሱም ከተመልካች ጋር ተዋወቀ፤ ህልሙን የማሳካት ፍላጎቱም እያየለ መጣ -ታምሩ ዘገዬ።

“በተፈጥሮዬ በእጄ በመሄድ የሚያክለኝ የለም”

ታምሩ ትውልዱ ሰሜን ወሎ ላሊበላ አካባቢ በሚገኝ ጋዝጊብላ ቀበሌ ሲሆን ከአካል ጉዳት ጋር ነው የተወለደው፤ ባጋጠመው ጉዳት ሳቢያ ሁለቱን እግሮቹን ያለ ክራንች መጠቀም አይችልም።

የተወለደበት አካባቢ ገጠር በመሆኑ በወቅቱ ማህበረሰቡ ስለ አካል ጉዳተኝነት ያን ያህል ግንዛቤው አልነበራቸውም። እንኳንስ ስለ ህክምናና ቴክኖሎጂ፤ መኪና እንኳን ማየት ብርቅ ነበር ይላል።

ይህም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አካል ጉዳተኛ መሆኑ ፈተናውን አባብሶበታል።

የገጠመውን ችግር ከባዕድ አምልኮና ከእርግማን ጋር ያያይዙታል።

ወላጆች በልጆቻቸው የሚያፍሩበትና የሚሳቀቁበትም አጋጣሚ ብዙ እንደሆነም ይናገራል። ይህም ልጅነቱን ፈታኝና ጎዶሎ አድርጎበታል።

ይሁን እንጂ ነገሮችን ወደ ቀልድና መዝናኛነት መለወጥ የሚቀናው ታምሩ ውሃ ለመቅዳት አልያም ከብት ለመጠበቅ ወደ መስክ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ ዳገቶችን ተገልብጦ በእጁ በመራመድ ጓደኞቹን ያስደምማቸው እንደነበር ያስታውሳል።

ፈተናዎቹን በሳቅ ለማለፍ ይሞክራል።

ታምሩ በክራንች ተገልብጦ በመራመድ ላይImage copyrightTAMIRU ZEGEYE

“በተፈጥሮዬ በእጄ በመሄድ የሚያክለኝ የለም፤ ተራራውን ለመውጣት ጤነኞች በእግራቸው ሲሄዱ፤ እኔ ግን በእጄ ተገልብጨ ተራራውን እወጣ ነበር” በማለት ያስታውሳል፡፡

የቄስ ትምህርቱን እስከ ቅኔ ድረስ ተከታትሏል። ከዘመናዊ ትምህርት ጋር የተዋወቀው ግን ዘግይቶ በ16 ዓመቱ ነበር። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታተለ።

በኢንፎርሚሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በቱሪስት በማስጎብኘት (tour guide) ዲፕሎማውን አገኘ።

አዲስ አበባ በሚኖርበት ጊዜም ከጉዳቱ ያገግም ዘንድ የእግር ቀዶ ጥገና አድርጎ ነበር።ቢሆንም ሙሉ በሙሉ እግሮቹን መጠቀም ባያስችለውም ክራንች ግን አልከለከለውም ።

ጥያቄ የወለደው ህልም

ይህ ሁሉ ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ በአእምሮው የሚያብሰለስለው ጉዳይ አልጠፋም፤ ይባስ ብሎ አቅጣጫውን ለወጠ። ጥያቄዎች እየተግተለተሉ በአዕምሮው ይመላለሱ ጀመር።

“ለምንድን ነው ሰዎች በክራንች እያነከሱ የሚሄዱት?” የሚል፤ ጥያቄውን ከቂላቂልነት የጣፉትም ነበሩ፤ እርሱ ግን የምሩን ነበር።

“ለምን በክራንቹ ላይ ተገልብጨ በእጄ አልሄድበትም? አልኩ” የሚለው ታምሩ ገጠር በሚኖርበት ጊዜ ተገልብጦ በእጁ የሚሄደውን ልምዱን ማዳበር ፈለገ።

ውሳኔው ራሱን ለማዝናናት፣ ለመቀለድ፣ ፌስቡክ ላይ ፎቶውን ለመለጠፍ ሲል እንጂ በዚህ መልክ ለዚህ ደረጃ እበቃለሁ ብሎ ግን አላሰበም።

እግሩን ቢያመውም ሙከራውን አጠናክሮ ቀጠለ፤ እየወደቀ ተነሳ ፤ ደጋግሞ ሞከረው ከዚያም እግሮቹን ወደላይ ዘርግቶ ክራንች ላይ ተገልብጦ በእጁ መቆም ሆነለት።

እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል እንደሚባለው በክራንቹ ላይ መቆም ከቻለ የማይራመድበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ራሱን አሳመነ።

ልምምዱንም በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርፆ አስቀመጠ።

በቴሌቪዥን መስኮት ከተመለከተው እንግዳ የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ…የሚለው ቃል በአዕምሮው ይንሸራሸር ያዘ።

ታምሩ ዘገየ በክራንች ተገልብጦ ሲሄድImage copyrightTAMIRU ZEGEYE

በርሱ ችሎታ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ የሰፈሩ ሰዎች እንዳሉ ለማየት መዝገቡን አገላበጠ፤ በእርሱ ችሎታ የተመዘገበ አለመኖሩንም አረጋገጠ።

ይህንኑ ለማድረግ ተግቶ መስራቱን ቀጠለ። በእጁ ተገልብጦ ደረጃዎችን በመውረድና በመውጣትም ብዙዎችን አስደነቀ። በክራንች ተገልብጦ ወደ 70 ሜትር በመሄድ ችሎታውን አሳደገ።

በስራ አጋጣሚ ያገኛቸው ሰዎችም እርሱን በማስተዋወቅ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ይናገራል።

የስኬት ጎህ ሲቀድ

በወቅቱ የነበሩት የሰርከስ ደብረብርሃን አሰልጣኝ ስራውን ስለወደዱለትና አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ በሚለው መርህ የሰርከስ ቡድኑን መቀላቀል ቻለ። በዚያ ቆይታውም የተለያዩ ትዕይንቶችን ከቡድኑ ጋር ያቀርብ ነበር።

14 ከሚሆኑትና የተለያየ ችሎታ ካላቸው የሰርከስ ቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ‘ካርጎ’ በሚል የሰርከስ ትርኢት ለሶስት ወር ያህል ለማሳየት ወደ ስዊድን ተጓዙ።

” ካርጎ ያልነው ብዙ አፍሪካውያኖች በኮንቴነር ተጭነው ወደ አውሮፓና ሌሎች አረብ አገራት ይሄዳሉ፤ ይሁን እንጂ በኮንቴነር ውስጥ ታሽገው እንደ ዋዛ የሚሄዱት ስደተኞች የራሳቸው ችሎታና ብቃት እንዳላቸው ለማሳየት ያለመ በመሆኑ ነው ” ይላል።

በስዊድን በነበራቸው ቆይታም ብዙ አድናቆትን እንደተቸራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታው ነው።

ይሁን እንጂ “በተለያየ ችግር ምክንያት ከአሰልጣኜ ጋር አልተስማማሁም ነበር” የሚለው ታምሩ ወደ ጀርመን አቅንቶ ጥገኝነት ጠየቀ።

በጀርመን ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ አግኝቶ ኑሮውን መሰረተ።

በስራው ምክንያት ብዙ አገራት እንደተጓዘ የሚናገረው ታምሩ ጀርመን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይህም ህልሙን ዳር ለማድረስ ሁኔታዎችን ምቹ እንዳደረገለት ይናገራል።

የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ አድረሻ ፈልጎ የተቀረፀውን ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላከላቸው፤ እነርሱም ወደዱት።

ጥረቱና ህልሙ ተሳክቶለት ከአራት ዓመታት በፊት በክራንች ተገልብጦ 100 ሜትርን በ57 ሰከንድ በመሄድ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙን አሰፈረ።

ታምሩ ዘገየ የተቀበላቸውን የምስክር ወረቀቶችን ይዞImage copyrightTAMIRU ZEGEYE

ወደፊት ትዝ ሲል

ታምሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝቷል። ከሽልማቶቹ መካከልም ወርልድ ሪከርድ አሲስታንስ (ASSIST WORLD RECORDS)ና ወርልድ ሪከርድ አካዳሚ (world record academy) ይጠቀሳሉ።

በራሱ ተይዞ የቆየውን የራሱን ሰዓት ለማሻሻል ተግቶ እየሰራ ይገኛል። አሁን ባለው ብቃቱም 100 ሜትሩን ከ45- 50 ባሉት ሰከንዶች መጓዝ እንደሚችል ይናገራል።

ከዚህ ባሻገርም ሌሎች ያልተለመዱ ስራዎችን ለማስመዝገብ በልምምድ ላይ ይገኛል። በእጆቹ ተገልብጦ 50 ፑሽ አፕ በመስራት ልምምዱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ታምሩ በአሁኑ ሰዓት ጀርመን ባየር ኑረምበርግ የሰርከስ አርቲስት በመሆን ሕይወቱን እየመራ ነው።

ያለፈበት የሕይወት መንገድ አስተምሮታልና የአካል ጉዳተኛ ማህበር የመመስረት እቅድ አለው፤ በተለይ ከ 5- 18 ያሉና ትምህርት ያላገኙ አካል ጉዳተኛ ህጻናትን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ማህበር የመመስረት ዕቅድ ይዟል። ከሚኖርበት ጀርመን ሆኖ የአካል ጉዳትን የሚረዳ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ ሃሳብ አለው።

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.