‹‹ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የሚኖራቸዉ ግንኙነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡››

• ከሁለት አስርት ዓመታት እና ከዛ በፊት የነበሩ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የጠነከረ ግንኙነት ነበራቸዉ፡፡

ባሕር ዳር፡ነሀሴ 04/2010 ዓ.ም(አብመድ) በእንግሊዝ የተደረገ ጥናት ይፋ እንዳደረገዉ ከአስርት ዓመታት ወዲህ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት እና ለቤተሰቦቻቸዉ የሚኖራቸዉ ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀንሷል፡፡
ለትዉልድ አካባቢያቸዉ እና ለሚኖሩበት ማህበረሰብ እምብዛም ትኩረት አይሰጡምም ብሏል፡፡ ጥናቱ በ20ዎቹ የእድሜ ክልል በሚገኙ ወጣቶችን በማካተት ከፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 2005 እስከ 2015 ተደርጓል፡፡

ከሁለት በላይ ትዉልዶችንም በንጽጽር ተመልክቷል፡፡ 80 በመቶ በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ የዚህ ዘመን ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸዉ እና ዘመዶቻቸዉ ይልቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ ሚዲያ ከተዋወቋቸዉ ሰዎች ጋር የጠበቀ የእለት ተዕለት ግንኙነት ይመሰርታሉ፡፡ ችግሮች ሲያገጥሟቸዉ ለቤተሰብ አያማክሩም፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊም ሆነ ሌሎች ድጋፎችንም ከቤተሰብ አይጠይቁም ነዉ ያለዉ ጥናቱ፡፡

በአንጻሩ ከአስርት ዓመታት እና ከዚያ በፊት የነበረዉ ወጣት ትዉልድ ከቤተሰብ አባላት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አንደነበረዉ ተመልክቷል፡፡ ለአብነት ወጣቶች እስከ 30ዎቹ አጋማሽ አድሜያቸዉ ከቤተሰብ ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ ከቤተሰብም ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያገኙ ነበር፡፡ ከቅርብ ጓደኞቻቸዉ መካከል ቢያንስ አንድ የቤተሰብ አባል እንደሚኖርም ገልጿል፡፡

አዲሱ ወጣት ትዉልድ ትርፍ ጊዜዉን ከቤተሰብ ጋር የማሳለፍ እንዲሁም በማህበራዊ እና የበጎ ፈቃድ ተግባራት የመሳተፍ ልምዱ አነስተኛ ነዉ ይላል ጥናቱ፡፡ ይህም ከማህበራዊ መገናኛ መረቦች መስፋፋት እና የግለኝነት (individualism) ኑሮ ዘይቤ መለመድ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑ በዋና ምክንያትነት ቀርቧል፡፡

ወጣቶች ለመንፈስ ጭንቀት እና ሌሎች የስነ-አዕምሮ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸዉ ጨምሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለእድሜ ልክ በሽታዎች ይጋለጣሉ፤ ግፋ ሲልም ራስን አስከማጥፋት ይደርሳሉ፡፡ ችግሩ ሁሉንም ሰዉ የሚመለከት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ተብሏል፡፡

ማህበራዊ መገናኛዎችን በአግባቡ መጠቀም እና ከቤተሰብ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመስረት አዲሱ ትዉልድ መዘንጋት የሌለበት ጠቃሚ ጉዳዮች መሆናቸዉ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.