ኢትዮጵያ፡ ያለ ባሕር በር የባሕር ኃይል ?

ጎልማሳው የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ባልደረባ ትዝታ፣ ቁጭት እና ናፍቆቱን የሚወጣው በሙዚቃ ነው፡፡ የኪቦርዱን ቁልፍ እየጠቃቀሰ የሚያንጎራጉራቸውን ሙዚቃዎች ሌሎችም ይጠለሉባቸው ዘንድ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይጭናቸዋል፡፡

ከእነዚያ ሙዚቃዎች መካከል አንዱ ‹መልህቅ አርማዬ› የተሰኘው በጌታቸው በርሄ ተጽፎ በባህር ሃይል የሙዚቃ ቡድን የተዘጋጀው ለስላሳ መዝሙር ነው፡፡

ፒቲ ኦፊሰር ፍሬሰናይ ከበደ ስለ ድሮ ባህር ሃይል ሲነሳ ግን የሙዚቃውን ተቃራኒ በእልህና በቁጭት ይሞላል ፣‹‹የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ከዓለም ተደናቂ ሃይሎች አንዱ የነበረ፣ ሰባቱንም ውቅያኖሶች ያቋረጠ ትልቅ የባህር ሃይል ነበር፡፡ ከወደብ ጠባቂ(ኮስት ጋርድ) ጀምሮ እስከ ትልቁ የጦር ሚሳኤል ድረስ ታጥቆ ይንቀሳቀስ የነበረ ሃይል ነው፣›› ብሎ እማኝነቱን ይሰጣል፡፡

ፒቲ ኦፊሰር ከሙዚቃ በተጨማሪ ባሰናዳው ድረ-ገፅ ሰርክ የሚዘክረው የባህር ሃይል ዛሬ የለም፡፡ ጃንሆይ በ1947 አቋቁመውት በደርግ ዘመን እስከ 3ሺ ጦር ድረስ የነበረው ሃይል በ1983 ምጽዋ በኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር ከተያዘበት ጀምሮ ህልውናው ይስለመለም ገባ፡፡

ነባር መርከቦቹ ከየመን እና ዙሪያው ተሰብስበው፣ገሚሶቹ የጂቡቲን ዕዳ ለመክፈል ዋሉ፣ ገሚሶቹ የኤርትራ አዲስ መንግስትና ኢትዮጵያ ተከፋፈሏቸው፡፡ በ1988 ዛሬ የምስራቅ አፍሪቃ ተጠባባቂ ጦር ቅጥር ግቢ የሆነው የአዲስ አበባ ቢሮው ሲዘጋ የባህር በር ታሪክ የተደመደመ መሰለ፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ከሰሞኑ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በነበራቸው ምክክር የኢትዮጵያን ባህር ላይ የማደራጀት አላማ እንዳላቸው ስለማሳወቃቸው ተዘገበ፡፡

ዘገባውን ተከትሎ ተስፋ እና ጥያቄ ተከተለ፡፡ ከጠያቂዎቹ መካከል የቀድሞ የባህር ሃይል ባልደረባ ፒቲ ኦፊሰር ፍሬሰናይ ከበደ ይገኝበታል፡፡

‹‹ካለ ባህር በር እና ባህር እንዴት ነው የባህር ሃይል የሚቋቋመው? ይሄ በእውነቱ ፌዝ ነው፡፡የባህር ሃይል ውስጥ የነበረ ሰው ይቅርና ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚቀበለው አይሆንም ፡፡›› ሲል ያሳስባል፡፡

የቀድሞ የባሕር ሃይል ባሕር -ጠለቅ ኮማንዶ አባልImage copyrightFRESENAY KEBEDE
አጭር የምስል መግለጫየቀድሞ የባሕር ሃይል ባሕር -ጠለቅ ኮማንዶ አባል

ከጎረቤታዊ ባህር ሃይል -እስከ ቦሊቪያዊ ተሞክሮ

የቀድሞው የባህር ሃይል አባል በተቃራኒ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ፣ የወታደራዊ እና ደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ ሜጀር ጀኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር ሃይልን ጉዳይ ሲያነሱ በተለያዩ መንገዶች ሊያሳኩት አስበው እንደሆነ ሀሳባቸውን ያጋራሉ፡፡

‹‹አንደኛ ኢትዮጵያዊያን (ሲጠይቁት) የነበረውን የባህር መብት ለማስከበር አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ እኔም በሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ፅሁፌ ላይ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህግን ተጠቅማ የባህር በር ባለቤት የምትሆንበትን መንገድ ጠቁሜያለሁ፡፡ ምናልባት በሂደት የዚህ አካል የሚሆን የባህር ሃይል ለማዘጋጀት አስበው ሊሆን ይችላል፣›› በማለት የሚያብራሩት ጀኔራሉ፣ በሁለተኛ መንገድነት የሚጠቅሱት የአዘርባጃን እና ካዛኪስታንን ተሞክሮ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ቢሆኑም በካስፒያን ባህር ላይ የሚንቀሳቀስ ጦር አላቸው፡፡ ይሄን ያሳኩት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባላቸው ስምምነት መሰረት ነው፡፡ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ከጂቡቲ ጋር ያላትን መልካም ጉርብትና በመጠቀም የባህር ሃይል ጣቢያ ብሎም የቀይ ባህር ላይ ተሳትፎ ልታደርግ እንደምትችል ያወሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደር ስር በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ብርሃነ መስቀል አበበ ሁለተኛው ሀሳብ ሊሳካ የሚችልበትን ዓለማቀፋዊ አሰራር ሲያስረዱ ‹‹ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ የውሃ አካላት ላይ አሰሳ ለማድረግ ያላትን መብት ለማሳካት የባህር ሃይል የጦር ሰፈር ይፈልጋል፡፡በቀጠናው የጦር ሰፈር እንዳላቸው ሀገራት ሁሉ በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ከጎረቤት ሀገር ባንዱ የባህር ጦሯን ልታሰፍር ትችላለች፡፡ የተሳሰሩ ህዝቦች አሉን›› ይላሉ፡፡

ወደ ሜ/ጄኔራል አበበ ስንመለስ ሶስተኛውን የቦሊቪያን መንገድ ያጋሩናል፡፡

‹‹የባህር በር የሌለው ቦሊቪያ የሚባል ሀገር አለ፡፡ ከጊዜያት ወዲህ የባህር በሩን ያጣ ሀገር ነው፡፡ ይሁንና አሁንም የባህር ሃይል አላቸው፡፡ የባህር ሃይላቸውን የሚጠቀሙበት ያጣነው ነገር የለም የሚለውን መንፈስ ለማሳየት እንደ (ሀገራዊ ክብር ማሳያ) ምልክትነት ነው፡፡››

በ1958 የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አባላት ከጦር መርከብ ኢትዮጵያ አባላት ጋርImage copyrightFRESENAY KEBEDE
አጭር የምስል መግለጫበ1958 የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አባላት ከጦር መርከብ ኢትዮጵያ አባላት ጋር

እስከመቼ ጎረቤት ታምኖ …

ለዓመታት ሳይታክቱ ‹‹ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት አላት›› በሚል ሲሟገቱ እናውቃቸዋለን-ዶ/ር ያቆብ ሃ/ማሪያምን፡፡ ከተለያዩ መድረኮች ሙግት እና ውይይቶች ባሻገር ‹አሰብ የማናት? ፣የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ›› የተሰኘ መጽሃፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ዶ/ር ያቆብ የሰሞነኛውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ንግግር በበበጎ እንደሚያዩት፣ ሆኖም የባህር በር በሌለበት ሁኔታ የሚሰምርበት ሁኔታ ላይ ጥርጣሬ አላቸው፡፡ የጎረቤት ሀገራትን ተማምኖ ጦር ማደረጀትም ያልተፈለገ ውጤት እንዳለው ይነሳሉ፡፡

‹‹ የጎረቤት ሀገራት ፍቅር እኮ ዘላለማዊ አይደለም፡፡ አንዳንዴ በመሃል ጥል፣ ግጭት ይኖራል፡፡ ይሄም የበለጠ ኢትዮጵያ በቋፍ ላይ እንድትሆን ያደርጋታል፣›› የሚሉት የዓለምአቀፍ ህግ ባለሙያ እና መምህሩ አስተማማኝ መፍትሄ የሚገኘው ኢትዮጵያ የባህር በር መብቷን ስታረጋግጥ እንደሆነ ዳግም ያሰምራሉ፡፡

ፒቲ አፊሰር ፍሬሰናይ ከበደ ግን ጣቶቹ በኪቦርዱ ላይ መመላለሳቸውን -እሱም መልህቅ አርማዬን መዘመር ቀጥለዋል፡፡

መልህቅ አርማዬ ቀይ ባህር ቤቴ፣

ጀግንነት ውርሴ የአያት የአባቴ፡፡

ቃልኪዳኔን ላድስ ዳግም ለእናት ሀገር፣

ተከብሮ በደሜ ለኖረው ባህርበር

የእምዬ ኢትዮጵያ መከታ ጋሻዎ

ጀግናው መርከበኛ የማህጸን ፍሬዎ፡፡

ለፍሬሰናይ ይሄ መዝሙር የብዙ ስሜቶች ማስታገሻ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ዳግም ተመስርቶ ይሄንን መዝሙር ለመዘመር ከቻለ ግን ውጤቱ የማይገመት የአዲስ ታሪክ ጅማሬ መሆኑ አይቀሬ ይመስላል፡፡

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.