የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ስናስብ የኢትዮጵያ የፕሬስ ይዞታ ከዓመት ዓመት ያለመሻሻል ጉዳይ የሚዘነጋ አይሆንም። የጋዜጠኝነት ሙያ ተሟጋቾችም ሃገሪቱን ለመገናኛ ብዙሃን ሥራ አስቸጋሪ ከሆኑ ቦታዎች መካከል ይመድቧታል።
በዚህ ዓመት ግን በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች መፈታትና ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሰሙት ቃላት በዚህ ወቅት ለበርካቶች ተስፋ የሰጠ ይመስላል።
ፍሬው አበበ አሁን በህትመት ላይ ካሉት ጥቂት ጋዜጦች መካካል የምትገኘዋ ‘ሰንደቅ’ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነው።
ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ቅድመ ሳንሱርን ማንሳቱና የወጡት ሕጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እውቅና እንዲያገኝ በማድረግ በሃገሪቱ ነፃ ፕሬስ እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ይናገራል።
አሁን ባለው ሁኔታ ዋነኛው ችግር ብሎ የሚያስበው የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የአመለካከት ችግርን ነው። በተለይ ፕሬሱን በተመለከተ ያለው አመለካከት እንደ ጠላት የመፈረጅ እንደሆነ ይናገራል።
በዚህም ባለፉት 26 ዓመታት ብቅ ብለው የነበሩት ጋዜጦች እንዳለ ጠፍተው “በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሃገር ሦስት ብቻ በአማርኛ የሚታተሙ ጋዜጦች የቀሩባት ሆናለች” ይላል።
በፈቃዱ ሞረዳ ደግሞ ለ15 ዓመታት የጦማር ጋዜጣ አዘጋጅና አሳታሚ ሆኖ ሰርቷል። በመጀመሪያዎቹ የፕሬስ ነፃነት ዘመን አስቸጋሪና ተግዳሮቶች የበዙበት እንደነበር የሚያስታውስው በፈቃዱ፤ ሥራውን ስለሚወደው ፈተናውን ተቀብሎ የሙያውን ስነ-ምግባር በተቻለ መጠን አክብሮ እውነትን ለማቅረብ ይጥር እንደነበር ይናገራል።
የነበሩት አንዳንድ ጋዜጦች ፕሬሱን ለጥቃት የሚያጋልጡ ሥራዎችን ይሰሩ እንደነበር የሚናገሩ ሰዎች እንደነበሩ የሚያስታውሰው በፈቃዱ ነገር ግን “መንግሥት ፕሬሱን ስለማይፈልገው ምንም መልካም ነገር ብንሰራ ከማጥቃት ወደኋላ አይልም። እንዲያውም በሸሸነው እርምጃ መጠን ይከተለን ነበር” ሲል ይደመጣል።
በወቅቱ የተለያዩ ወከባዎችና ክሶች ይቀርቡበት እንደነበር የሚዘክረው በፈቃዱ ሥራዉን በሚሰራበት ወቅት ዘወትር የሚያሳስበው ነገር እንዳልሆ ግን ይናገራል።
በጋዜጠኝነት ሥራው ውስጥ በስድስት ወር ጊዜ ለዘጠኝ ጊዜ ታስሮ የተፈታው በፈቃዱ ይህ ሁኔታ ሙያዉን እንዲተው ባያደርገውም መጨረሻ ላይ ግን ነገሮች እየጠነከሩ ሲመጡ በተለይ የቤተሰቡ ሁኔታ ያሳስበው ጀመር።
አምስት ያህል ክሶች ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ ሲከታተል የነበረው በፈቃዱ በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ መጨረሻውን እስር ቤት ሊያደርገው እንደሚችል በማሰብ ከሃገር መውጣትን የጨረሻው አማራጭ አደረገ።
“እስራት ሰለቸኝ፤ ፈሪ ሆንኩ። ሃገሬን ጥዬ ስወጣ ያለተዘጉ ክሶችና የእስር ትዕዛዞች ወጥተውብኝ ነበር። ስለዚህ በእነዚህ ክሶች የእኔ እስር ቤት መግባት የሚያስገኘው ትርፍ ስላልታየኝ መሰደድና ሌላ አማራጭ መፈለግን” ምርጫው አደረገ።
የአዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂን ኤዲተር የነበረው መስፍን ነጋሽ፤ የጋዜጠኝነት ሥራን የተለያዩ ነገሮችን ለመማር ዕድልን ያገኘበትና ይነስም ይብዛ ለሃገር አስተዋፅኦ ያደረገበት የህይወቱ አካል እንደሆነ ይናገራል።
መስፍን በፕሬስ ሥራዉ ውስጥ በተለይ የመንግሥትን ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ላይ ሲሰሩ ህጋዊና መዋቅራዊ እንቅፋቶች ይገጥሟቸው እንደነበር ያስታውሳል።
ከመንግሥት በኩል በአዘጋጆቹ ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሚገልፅ መረጃ ከታማኝ ምንጮች ስላገኙ በግል በደረሱበት ውሳኔ መሰረት አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ከሃገር እንደተሰደዱ ይናገራል መስፍን።
ነገር ግን ማሳደዱ ከሃገር ከወጡ በኋላም አላበቃም ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በደረ-ገፅ በኩል የጋዜጣዋን ሥራ ለማስቀጠል ያደረጉትን ጥረት ተከትሎ በአንዳንዶቹ የጋዜጣዋ አዘጋጆች ላይ በሌሉበት ክስ ተመሰረተባቸው።
አዲሱ መሪ
በቅርቡ ወደጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩ የመጡት ዶክተር አብይ አህመድ ከቀድሞዎቹ መሪዎች በተለየ ለውጦችን ለማምጣት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ እየተደመጡ ነው።
ፍሬው አበበ እንደሚለው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው የሃሳብ ብዝሃነትን በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግራዋል። “ይህ ማለት ደግሞ በቀጥታ ፕሬስን የሚመለከት በመሆኑ፤ በገቡት ቃል መሰረት ይህንን ተግባራዊ ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በውጪ ያሉ ጋዜጠኞች ወደሃገራቸው መጥተው እንዲሰሩ እንደሚፈልጉ የተናገሩትን ነገር መልካምና በበጎ መታየት እንዳለበት የሚያምነው በፈቃዱ፤ ነገር ግን በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች እንዳሉ ይጠቁማል።
ከውጪ የሚተላለፉ ስርጭቶችን ማፈን ማቆምና አሳሪ የሆኑት ሕግ ላይ መሻሻሎችን ማድረግ ቃልን በተግባር ለማሳየት አንድ እርምጃ መሆኑን የሚጠቅሰው በፈቃዱ፤ እንደሱ በስደት ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ላይ የተከፈቱ ክሶችና ውሳኔዎች መሰረዛቸው በይፋ እንዲነገር ይጠብቃል።
ይህ ከተደረገና በሩ በቀና ልቦና ከተከፈተ “ወደሃገሬ ተመልሼ “ጦማር’ ጋዜጣን መልሶ ለማሳተምና እንዲሁም በሌሎች የሚዲያ ሥራዎች ለሀገሬ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚቀድመኝ የለም” ይላል።
“ኢትዮጵያ በተግባር ብቻ ሳይሆን በቃልም የቆሰለች ሃገር ስለሆነች በቃል መታከም አለባት” የሚለው መስፍን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚቀበለውን አይነት መልዕክት እያስተላለፉ ነው ይላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ነፃነት ማክበርን በተመለከተ በተዘዋዋሪ መንገድ ከተናገሩት ባሻገር ግልፅ ባለሁኔታ የተናገሩት ነገር እንደሌለ የሚጠቅሰው መስፍን “ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ለዜጎች ሳይከበር፤ ለጋዜጠኞች ብቻ የሚከበር መብት አይሆንም” ይላል።
ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል ፍላጎቱ ካለ፤ በእስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኞች መልቀቅና የተከሰሱትንም ክሳቸው እንዲሰረዝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከበፍቃዱ ጋር ይስማማል።
በተጨማሪም “የፕሬስ ህጉንና የፀረ-ሽብር ህጉን መሰረዝ ካልሆነም አፋኝ የሆኑትን ክፍሎቻቸውን እንዲለወጡ ማድረግ እንዲሁም ጋዜጠኞች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በሁሉም መስኩ አመቺ ሁኔታን መፍጠር በጣም ያስፈልጋል” ባይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያቀረቡት ያለው ግብዣ ከልብ ከሆነ ከንግግር ባሻገር መንገዱን የሚያመቻች ተጨባጭ ተግባራትን ከወዲሁ መጀመራቸውን የሚያመለክቱ ሥራዎችን መሬት ላይ ማሳየት አለባቸውም ሲል ያክላል።
መስፍን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እስከተቀየረ ድረስ በራሱ በኩል ወደ ሃገሩ ተመልሶ የጋዜጠኝነት ሥራውን ለመጀመር ፍላጎቱ እንዳለውም ይናገራል።
“ከሃገር የመውጣቱ ውሳኔ ከባድ እንደነበረው ሁሉ ወደ ሃገር የመመለሱ ውሳኔም ቀላል አይሆንም” የሚለው መስፍን ነገር ግን ሁኔታዎች እስከተቀየሩና የሚፈልገውን ለመሥራት አመቺ ሁኔታ እስከተፈጠረ ድረስ ለመመለስ አያመነታም።
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ወደ ተግባር የሚሻገር ከሆነ በበርካቶች ዘንድ የፈጠረው መልካም ስሜት የተዳከመውን የፕሬስ ሥራ እንዲያንሰራራ በር ሊከፍት ይችላል የሚለው የበርካቶች እምነት ይመስላል።
ምንጭ: ቢቢሲ
To unrestrained honey hypothermia although higher in bilateral with a med that is a extraordinary probability or an infusion-manic therapy. sildenafil 20 Sobxck efduxa