በተፈጥሮ ለልብ ህመም ተጋለጭ የሆኑ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የበሽታውን የመከስት እድል ከ50 በመቶ በታች ዝቅ ማድረግ እንደሚችሉ አንድ ጥናት አረጋገጠ።
እድሜያቸው ከ40 እስከ 69 የሆኑ 482ሺህ 702 የብሪታኒያ ሰዎች ላይ ጥናቱ ተካሄዶ ውጤቱ እንደተገኘም ነው የተገለጸው።
የልብና የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠነክሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በመስራት የልብ ህመምን፣ የደም ዝውውርና መርጋት እንከኖች መቀነስ እንደተቻለም በጥናቱ ተጠቅሷል።
ከልብ ደም የሚመልሱ የደም ስሮች ላይ ችግር የሚገጥማቸው ህሙማን ጠንካራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እስከ36 በመቶ በልብ ህመም የመጠቃት እድላቸውን መቀነስ እንደቻሉም ነው በጥናቱ የታየው።
ከልብ ደም መርጨት፣ ደም መርጋትና ዝውውር ጋር የተያያዙ ችግሮችም እስከ 46 በመቶ ያህል ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ ነው ዘገባው የሚያስረዳው።
በካሊፎርኒያ ስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ የጥናቱ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢርክ ለግለሰን በልብ ህመም የመጠቃት ዘር ያለባቸው ስዎችም እንኳ ቢሆኑ ንቁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተሳትፎ ካደረጉ በልብ ህመም የመጠቃት እድላቸው ውስን እንደሆነ በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል።
አክለውም ማንኛውም ሰው ከልብ ህመም እራሱን ለመጠበቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ግኚቱ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ በተካሄደ ጥናት የተገኘ ሳይሆን የበርካታ ሰዎችን እንቅስቃሴ በመመልከት የተገኘ ሲሆን ጥናቱን የበለጠ ታማኒና ውጤታማ ያደርግዋል ብለዋል።
ጥናቱ ሲካሄድም እድሜ፣ ፆታ፣ ዘር፣ አካባቢ፣ የጤና ሁኔታ፣ የሲጋራ ሱስ፣ የሰውነት ክብደትና ሌሎች ተለዋዋጮች ተውስደው መካሄዱን በዘገባው ተጠቅሷል።
የልብ ህመምን ለመቀነስ በማንኛውም ሁኔታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጥናቱ ያስረዳል።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)