ብዙ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ረሀብ፣ ቁር ሳይበግራቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ለቀናት ይባስ ሲልም ለወራት በእግራቸው ተጉዘው ወደ ሌላ አገር ይሻገራሉ።
በዚህ እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ጉዞም በአሰቃቂ ሁኔታ ብዙዎች ባህር ውስጥ ሰምጠዋል፤ የሰውነት አካላቸው ተሽጧል፤ ተስፋቸው ሳይሞላ ሞተዋል፤ ሌሎችም ለማይሽር አካላዊና ህሊናዊ ጠባሳ ተዳርገዋል።
እዛም ከደረሱ በኋላ የከፋ ህይወት የሚያጋጥማቸው ብዙ ናቸው። በተለይም ወደ አረብ አገር የሚሄዱት በአሰሪዎች መደብደብ፣ መደፈር፣የጉልበት ብዝበዛ ፣ክፍያ መከልከልና ሌሎችም አስከፊ ስቃዮች የበርካታ ኢትዮጵያዊያን እጣ ነው።
የአንዱ ምርቃን ለአንዱ እርግማን ነው እንዲሉ ብዙዎች ባለው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሁኔታ ተማረው ህይወታቸውን አደጋ ጥለው ከኢትዮጵያ እየተገፉ ሚሊዮኖች ወደ ተለያዩ ሀገሮች ይሰደዳሉ ፤ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ ወደ ሃያ የሚሆኑ ሀገራት ስደተኞች መጠጊያ ናት።
ስደተኞቹ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የህክምና ችግር ፣ በተለያዩ ጦርነቶች አልፈው ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለአዕምሮ ህመም የተጋለጡ እንዲሁም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውም በከተማ ስደተኝነት ተመዝግበው አዲስ አበባ ይኖራሉ።
የከተማ ስደተኛ ማን ሊሆን ይችላል የሚለውን የሚወስነው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሲሆን በስደተኞች ዙሪያም ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር አብረው ይሰራሉ።
አስረሳሽ ስራው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ልማትና ተራድኦ ኮሚሽን የስደተኞችና ተመላሾች መምሪያ የማህበራዊ አገልግሎትና የፆታዊ ጥቃት መከላከል ኃላፊ ስትሆን በሙያዋም ነርስና የሳይኮሎጂም ባለሙያ ናት።
በዚህ መምሪያ የሚረዱ ወደ 4500 ስደተኞች ሲኖሩ ከህክምና ድጋፍ በተጨማሪ ገንዘብም በቤተሰባቸው መጠን መሰረት በየወሩ እንደሚሰጣቸውም ትናገራለች።
ብዙዎች በጦርነት ከፈራረሱ ኃገሮች ከመምጣታቸው አንፃር ስደተኞቹ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እንዲሁም አዕምሯዊ ጉዳት ደርሶባቸው እንደሚመጡ አስረሳሽ ትናገራለች።
አንዳንድ ታሪኮች ለመስማት የሚዘገንኑና ሰብዓዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ናቸው።
ከነዚህም ውስጥ የሲናይ በረሃን ስታቋርጥ በወታደሮች ተይዛ ለስድስት ወራት ያህል በእሳት መጠበስ፣ በኤሌክትሪክ መቃጠልና መደፈር የደረሰባት 18 ዓመት ያልሆናት ልጅ በደረሰባት በደልና ስቃይ የአዕምሮ ችግር እንዲሁም አካላዊ መናጋቶች እንደደረሱባት አስረሳሽ ትናገራለች።
ባዕድ ነገር ማህፀኗ ውስጥ ተጨምሮባት ማህፀኗ በቀዶ ጥገና የወጣላት ሴት፤ ሌላኛው ህፃን ወንድ ደግሞ አባቱን፣ እናቱንና ወንድሙን ከገደሉ በኋላ እሱን ወታደሮች ደፍረውት ለማያገግም የአካል እንዲሁም የአእምሮ ጠባሳ ጥሎበት እንዳለፈ አስረሳሽ ትናገራለች።
“አንዳንዴ ይህንን የሚያደርጉት ሰዎች ናቸው ወይስ አውሬ ናቸው?” በማለት ትጠይቃለች።
ልማትና ተራድኦ ኮሚሽን የስደተኞችና ተመላሾች መምሪያ ግቢ ውስጥ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳና ከየመንና ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞች በየጥጉ ተቀምጠዋል።
ከነዚህም ውስጥ ከኮንጎ ማሲሲ ከተባለች አካባቢ የመጣችው የ32ዓመት ዕድሜ ያላት ፌይዛ ባይንጋና ሳይመን አንዷ ናት።
ከነበረችበት መንደርና ከሞቀ ቤቷ የአማፅያን ቡድን ከባሏ ጋር እንደወሰዷትና ጫካ ውስጥ እንደደፈሯት ትናገራለች።
በተሰባበረ እንግሊዝኛዋም ልጇ እንዴት እንዳለቀሰ፣ እንዴት እንደደቡት ትናገራለች። “ባየውም ስቃይ ለስድስት ወራት መናገር አልቻለም ነበር” ትላለች።
አሁንም ከአንዳንድ ቃላት በላይ መናገር እንደማይችል የምትገልፀው ፌይዛ ራሱንም መቆጣጠር አይችልም።
የደረሰባት ጉዳት ሳያገግም ከሁለት ዓመታት በኋላ አባቷ፣ ወንድሟና ሌሎች ቤተሰቦቿ እንደተገደሉ የሷም ሆነ አካባቢው የነበሩ ቤቶችም እንደተቃጠሉ ትተርካለች።
ህይወቷንም ለማትረፍ ሾፌሮችን በመለመን ወደ ዩጋንዳ ተሰደደች። ስደቷ በዚህ አላበቃም፤ አቆራርጣም ወደ ኬንያ ከዚያም በአውቶብስ ተሳፍራ ወደ ኢትዮጵያ ገብታለች
ይህ ሁሉ ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ጥሩ ህይወት ትኖር እንደነበር የምትናገው ፌይዛ ኢትዮጵያ እስከምትደርስ ድረስ የደረሰባት ግፍ ተነግሮ እንደማያልቅ ትገልፃለች።
መጀመሪያ ኢትዮጵያ ስትደርስ አሶሳ አካባቢ የሚገኘውና ሸንኮሌ ተብሎ የሚጠራው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ከቆየች በኋላ ህመሟ ሲጠና ወደ አዲስ አበባ እንደተላከች ትናገራለች።
የከተማ ስደተኛ በመሆኗ 3ሺብር በወር የሚሰጣት ሲሆን ባለው ኑሮ ውድነት አንፃር ምንም በቂ እንዳልሆነ ትናገራለች።
” የቤት ኪራይ አዲስ አበባ አይቀመስም፣ ለትራንስፖርት መክፈል አለብኝ። በዚያ ላይ ልጆች አሉኝ እንዲሁም ከፍተኛ ህመም አለብኝ” ትላለች።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የኤድስም በሽተኛ ስትሆን በመደፈሯ ጊዜ የደረሰባት ኢንፌከክሽን ወደ ካንሰር እንደተቀየረም ተነግሯታል።
ሌላኛዋ ከኮንጎ የመጣችው ስደተኛ ኩዊን መለስም ታሪክ ተመሳሳይ ነው። ከኮንጎ ከመጣች አስር ዓመት የሆናት ኩዊን የተወለደችው ኢትዮጵያ ነው።
ኮንጎ ያደገቸው ኩዊን አባቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ለስራ ለጥቂት አመታት በመኖራቸው ኢትዮጵያ የመወለዷ ምክንያት ሆነ።
በተለያዩ ታጣቂዎች የተከፋፈለችውን ኮንጎን አምልጣ አዲስ አበባ የመምጣቷን ታሪክ የምታወራው በለቅሶና በምሬት ነው።
“ሰው አልነበርኩም፤ አሁንም በደረሰብኝ ነገር ሰው የሆንኩ አይመስለኝም። ቤተሰቦቼ ተገድለዋል፤ በሚያሳዝን መልኩ ሲገደሉ አይቻለሁ። በሰውነቴ ላይ ያደረሱትን ነገር ዘርዝሬ አልገልፀውም” ትላለች
ታጣቂዎች ቤተሰቦቿን ከገደሉ በኋላ እሷንም ደፍረዋት ሞታለች ብለው ጥለዋት እንደሄዱ ትናገራለች።
በጊዜው የሜዲሲን ተማሪ የነበረቸው ኩዊን ንግግሯ በሳግና በለቅሶ ይቆራረጣል። “በህይወቴ ማንም የለኝም፤ መንገድ ላይ ወንድሜን የሚመስል ሰው ሳይ መፈጠሬን እጠላለሁ” የምትለው ኩዊን
“ኮንጎን ማየት የምፈልገው ካርታ ላይ ብቻ ነው። የኮንጎ መሪ የነበረው ሞቡቱ ሴሴኮ አምባገነን ነው ይላሉ፤ ግን ሰላም ነበርን። ማንም ሊገድለን አይመጣም ነበር” ትላለች።
በጉዞዋ ላይ የደረሰባት መከራና ስቃይ ተዘርዝሮ እንደማያልቅ የምትናገረው ኩዊን እሷም በመጀመሪያ የደረሰችው አሶሳ የሚገኘው የቸርኮሌ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ነው።
የደም ግፊት፣ አስም እንዲሁም የአዕምሮ መረበሽ ያለባት ኩዊን አብዛኛውን ጊዜ በህይወት የመኖር ተስፋዋ ይሟጠጣል።
“አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ጥናታዊ ፊልሞችን ሳይና የኔን ሚመሰል ታሪክ ሳገኝ ብቻየን እንዳልሆንኩ ስረዳ ትንሽ እረጋጋለሁ” ትላለች።
በሰው ልጅ ያላት ተስፋ በከፍተኛ ሁኔታ የተሸረሸረ ሲሆን ነገን በጥርጣሬ ብታይም ከ10 ዓመት በኋላ እንደገና ህልሟን ለመኖር የትምህርት እድል አግኝታ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የነርሲንግ ትምህርቷን እየተማረች ነው።
ስቃዩ ቢዘረዘር ተወርቶ አያልቅም የምትለው አስረሳሽ ምንም እንኳን ችግሩ የጠለቀና አለም አቀፍ ችግር ቢሆንም ሰዎች ስለ ሰብዓዊነት ቢያስቡ ችግሩን መቀነስ ይቻላል ብላ ታምናለች።
ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ ሴቶች ተስፋቸው አንሰራርቶ የመኖር ተስፋቸው እንዲፈነጥቁ ብዙ ስራ እንደሚያስፈልገውም ትገልፃለች። “ጠንክረው ራሳቸውን ከዚያ ሁኔታ የሚያወጡበትን መንገድ እንሰራለን። የተለያዩ ማማከሮችን ስለሚያገኙ የጤናቸው ሁኔታ ይሻሻላል”ትላለች።
ከተለያዩ ድርጅቶችም ጋር በመተባበር የፀጉር ስራ፣ የልብስ ስፌት እንዲሁም የኮምፒውተር ስልጠና በመስጠት ህይወታቸውን ዳግም የሚያስቀጥሉበትን መንገድ እንደሚመቻችም አስረሳሽ ትናገራለች።
“ሁሌም የምፀልየው ጥንካሬ እንዲሰጠኝ ነው። ለልጆቼ ትንሽ ጊዜ እንኳን በህይወት ብቆይላቸው ደስ ይለኛል። ሁልጊዜም ቢሆን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ” የምትለው ፌይዛህይወቷ አሁን የተረጋጋ እንደሆነም ትገልፃለች።
“ኢትዮጵያ የአዕምሮ ዕረፍት አግኝቻለሁ፤ የመሳሪያ ተኩስ አልሰማም፤” ትላለች ፌይዛ
ለኩዊንም ከምሬትም ጋር ቢሆን ኢትዮጵያ የመኖር ተስፋን የምታልመው ቦታ ሆኖላታል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ