የቆዳ መሸብሸብን ለመከላከል

                 

የሰውነት ቆዳ ሁለት ተደራራቢ ክፍሎች ሲኖሩት፥ የላይኛውና የታችኛው በመባል ይታወቃሉ፤ የቆዳ መሸብሸብ ደግሞ በታችኛው የቆዳ ክፍል ላይ የሚከሰት ነው።

የታችኛው ክፍል ኮለጅን እና ሌሎች የፕሮቲን አይነቶች በአብዛኛው ሲኖሩት፥ ኮለጅን ቆዳ እንዲለጠጥና እንዲለሰልስ ያደርገዋል።

እድሜ እየገፋ ሲሄድ ሰውነትም ከእርጅና ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ መጠን ያለው ኮለጅን ያመርታል ይህ ደግሞ ቆዳን እንዲደርቅና እንዲሸበሸብ ያደርገዋል።

ከዚህ ባለፈም በበዛ መልኩ ለፀሃይ ብርሃን መጋለጥ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የፈሳሽ እጥረት፣ ያልተመጣጠነ አመጋገብ፣ ሲስቁ አልያም ከስሜት መለዋወጥ ጋር የሚያሳይዋቸው የፊት ገጽታዎች፣ ብክለትና መመረዝ፣ በጎን በኩል መተኛት እና እድሜ ለዚህ ችግር ይዳርጋሉ።

ባለሙያዎች ደግሞ ይህን ችግር ለመከላከል የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ይጠቁማሉ፤

ሲጋራ አለማጨስ፦ ሲጋራ ሲያጨሱ ሰውነት ለፈሳሽ እጥረት ይዳረጋል፤ ሲጋራ ሲያጨሱም ጉንጭና ግንባር አካባቢ መስመሮች እንዲወጡ በማድረግ ለቆዳ መሸብሸብ ያጋልጣል።

ውሃ መጠጣት፦ ውሃ ማብዛቱ በተለያየ አጋጣሚ ወደ ሰውነት ውስጥ የገቡ አደገኛና መርዛማ ውህዶች ጠራርጎ ለማስወጣትና ለማስወገድ ይረዳል።

በዚህ ሳቢያ ሊከሰት የሚችልን የቆዳ መሸብሸብ መከላከል ያስችላል።

አመጋገብ፦ በብክለትና መመረዝ ሳቢያ ቆዳ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ለዚህ ቫይታሚን ኤ፣ ሲ እና ኢ አስፈላጊ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፤ እነዚህ ቫይታሚኖች የሚገኙባቸውን ምግቦች አዘውትሮ መመገብም ለዚህ ይረዳል።

እንጆሪ፣ ሎሚ፣ ሰላጣ፣ ባቄላ እና በአብዛኛው አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ።

ከዚህ ባለፈም በኦሜጋ ፋቲ 3 የበለጸጉ እንደ አሳ አይነት ምግቦችን መመገብም ይመከራል።

አኩሪ አተርን በመፍጨት ዱቄቱን በውሃ አርሶ ቆዳ ላይ መቀባት፤ ወይም ደግሞ የአኩሪ አተሩን ዘይት ሰውነትን ከታጠቡ በኋላ መቀባት።

በፀሃይ ጨረር የተጎዳን የሰውነት ቆዳ እንዲያገግም ያደርጋል፣ የቆዳን ተፈጥሯዊ ወዝና ገጽታ በመመለስም ማራኪ ገጽታን ለመላበስ ይረዳል።

የቆዳ ማለስለሻዎችን መጠቀም፦ ሃኪም በማማከርና የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትሉ የቆዳ ማለስለሻዎችን መጠቀም ለዚህ ይረዳል።

ከዚህ ባለፈም ከመኝታ በፊት ፊትዎን ከታጠቡ በኋላ ጥቂት የወይራ ዘይት ጠብታን በመጠቀም ፊትዎን መቀባትና ወደ መኝታ ማምራት።

የፀሃይ ብርሃን ተጋላጭነትን መቀነስ፦ በአብዛኛው ከቤት ሲወጡ አልያም ወደ አንድ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በተቻለ መጠን በበዛ መልኩ ለፀሃይ ብርሃን አይጋለጡ።

ምናልባት በዚህ መልኩ ለፀሃይ ብርሃን የሚጋለጡ ከሆነም የህክምና ባለሙያወችን በማማከር የፊት ቆዳን ከፀሃይ ብርሃን ለመታደግ የሚረዱ ቅባቶችን መጠቀም።

በቂ እንቅልፍ፦ እንቅልፍ በአግባቡ አለማግኘት ሰውነት ኮርቲሶል የተሰኘውን ሆርሞን በብዛት እንዲያመነጭ ያደርገዋል።

ይህ ደግሞ ሰውነት ራሱን ለማደስ የሚያደርገው ጥረት ላይ እክል ስለሚፈጥር ለቆዳ መድረቅና መሰል አጋጣሚዎች ይዳርጋል፤ ይህም የቆዳ መሸብሸብን ያስከትላል።

በጀርባ መተኛት፦ ባለሙያዎች ይህን በተመለከተ እስካሁን ትክክለኛ ማረጋገጫ አገኘን ባይሉም በፊት ተደፍቶ መተኛት ግን አንድ ቦታ ላይ ለሚከሰት መስመርና የቆዳ መሸብሸብ ይዳርጋል።

ከዚህ አንጻርም በተቻለ መጠን በጀርባ መተኛት መሰል አጋጣሚዎችን ለመቀነስ ይረዳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement