ህዋዌ በስማርት ሞባይል ስልክ የሚነዳ መኪና ሰራ

                    

የቻይናው ትልቁ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ድርጅት ህዋዌ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በስማርት ሞባይል ስልክ የሚነዳ መኪና መስራቱን በባርሴሎና እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የሞባይል ጉባዔ ላይ አስታወቀ።

“ሮድ ሪደር” ወይንም መንገድ ቃኚ የተባለው ይህ ቴክኖሎጂ የህዋዌ ምርት የሆነውን ሜት 10 ስልክን በመጠቀም መኪናን ይቆጣጠራል እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን መለየት ይችላል። 

መኪናው የሚያጋጥመውን ነገር የመረዳት፣ የመለየት እንዲሁም ትክክለኛውን ውሳኔ የመወሰን አቅም እንዳለውም ነው የተገለፀው።

ስልክ ላይ የተገጠመው ካሜራ መንገድ ላይ የሚያጋጥሙትን አካላት ምስልን በመያዝ የተገጠመለትን ዋይፋይ በመጠቀም መረጃውን ወደ መኪናው እንደሚልክ ገልጸዋል።

የህዋዌ ስራ አስኪያጅ መኪናው 1 ሺህ የተለያዩ አካላትን የመለየት ብቃት እንዳለው በጉባኤው ላይ የገለጹ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ድመት፣ ውሻ፣ ኳስ፣ ብስክሌት እና ሌሎች ነገሮችን የማስታወስ ብቃት አለው ነው ያሉት። 

በተጨማሪም ሰው ሰራሽ የማሰብ አቅም ያለው መሳሪያ አስፈላጊነት ላይም በጉባዔ ላይ አንስተው ተወያይተዋል።

በባርሴሎናው ጉባኤ ላይ ከ108 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ይታደማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከ2 ሺህ 300 በላይ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን ማቅረባቸው ተገልጿል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement