ጥንዶች እርስ በእርስ የሚናናቁ ከሆነ የመፋታት እድላቸው ሰፊ ነው | Couples Who Disrespect Each Other Are Likely To Break Up

ማንኛውም የፍቅር እና የትዳር ግንኙነት የራሱ የሆነ የህይወት ውጣ ውረዶች አሉት።

42 በመቶ ጋብቻዎች በፍቺ እንደሚለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ።

ሆኖም የፍቺው ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ለመመለስ የተለያዩ ችግሮች ቢቀርቡም፥ ዋነኛው እርስ በእርስ ከመናናቅ የሚመነጭ መሆኑን የስነ ልቦና ፕሮፌሰሩ ጆን ጎትማን ይናገራሉ።

ፍቺ ከፈፀሙ የትዳር አጋሮች መካከል 90 በመቶዎቹ በትዳር ህይወታቸው ትኩረት አለመስጠት፣ እንክብካቤ ካለማድረግ እና ከመናናቅ የሚመጣ ነው ብለዋል።

በተለይም ስህተትን ላለማረም ግትር መሆን እና እኔ ጥፋተኛ አይደለሁም የሚሉት ባህርያትም የመናናቅ መገለጫዎች ናቸው።

ለትዳር አጋር ክብር አለመስጠት፣ ማንቋሸሽ፣ በምፀት መመልከት፣ ቁመነገር እና ቀልዱን ሳይለዩ ዋዛና ፈዛዛ መሆን፣ የስም አጠራር፣ ተገቢ ያልሁኑ አካላዊ መግባቢያዎች ለምሳሌ በግልምጫ መተያየት እና አፍን አጣሞ መናገር መገለጫዎቹ ናቸው።

መናናቅ ሲጀመር የትዳር አጋሮች አንዳቸው የሌላቸውን አወነታዊ እና መልካም ነገሮች በመርሳት፣ መጥፎ መጥፎ ነገሮችን ማሳደድ እንደሚጀምር ፕሮፌሰሩ “Why Marriages Succeed or Fai” በሚለው መፅሃፋቸው አስፍረዋል።

ፕሮፌሰር ጎትማን በትዳር ህይወት ውስጥ እንቅፋት የሚሆነውን መናናቅን ለማስወገድ መፍትሄዎችም አሉ ብለዋል።

ፍቅርን ለማጎልበት መጣር፣ አንዳቸው ሌላቸውን ማድነቅ፣ መከባበር እና ስላሳለፏቸው ደስተኛ የህይወት ገጠመኞች መጫወት ትዳራቸውን ለማጎልበት እና መናናቅን ለማስወገድ እንደሚጠቅም የስነ ልቦና ምሁሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በዚህም በመካከላቸው ቅራኔ ወይም ችግር በሚፈጠር ጊዜ ችግሮቻቸውን በጋራ መፍታትን ይለማመዳሉ፤ ጥፋትን ይቅር ይባባላሉ ነው ያሉት።

በመሆኑም የትዳር አጋሮች የፍቅር ህይወታቸውን ሲጀምሩ ቀጣይ ህይወታቸውን በሚያጠናክሩ አዎንታዊና መልካም ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ ነው የመከሩት።

ከዚህ ባለፈ ግን የትዳር ህይወት ላይ ጥንዶችን የሚያማክሩ ባለሙያዎችን መጠየቅም ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement