ለልብ ጤንነት የሚመከሩ አመጋገቦች – Heart-Healthy Foods to Work into Your Diet

                                            

ልብ ጤንነትን ለመጠበቅ ቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ጀምሮ አመጋገብን መቆጣጠር እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከአመጋገብ ጋር ተያይዞም ቅባት ያልባዛባቸውና ያልተቀነባበሩ ምግቦችን መመገብ እንደሚገባም ይመክራሉ።

ባለሙያዎቹ የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ ይረዳል ያሉትን አመጋገብ ደግሞ ከዚህ በታች መመልከት ይችላሉ፤

አጃና ገብስ፦ አጃ በውስጡ ቤታ ግሉካን የሚባልና የሚሟሟ አሰር (ፋይበር) ይዟል፤ ይህ አሰር ደግሞ ለሰው ልጅ ጤንነት እጅግ ወሳኝ ነው።

በሰውነት ውስጥ የሚገኝን የስኳር መጠን ማመጣጠን፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ማሳደግ፣ በህክምናም ሆነ በሌላ አጋጣሚ በጨረር ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መቀነስና

ለሰውነት አላስፈላጊ የሆነን ኮሊስትሮል መጠን ለመቀነስና ለማስወገድ ይረዳል።

በየቀኑ በጥቂቱ አጃና ገብስ ቢመገቡ አላስፈላጊ ኮሊስትሮልን በ10 በመቶ ለመቀነስ ይረዳዎታል፤ የገብስም ሆነ የአጃ አጥሚት በቀን አንድ ብርጭቆ ቢጠጡ እጅጉን ያተርፋሉ።

አሳ፦ በተለይም በቱና መልክ የሚዘጋጁ በጣም ያልበሰለ አሳ መመገብ ለልብ ጤንነት እጅጉን ይረዳል፤ ልብ የተስተካከለ ስራውን እንዲሰራ ከማገዙም በላይ የደም መርጋት እንዳይከሰትም ያደርጋል።

የደም ግፊትን መቀነስ፣ የደም ቧንቧዎች እንዳይጠቡ በማድረግ የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ ይመከራሉ፤ ለዚህም አሳና የአሳ ተዋጽኦዎችን መመገብ።

በተቻለ መጠንም በሳምንት ሁለት ቀን አሳ ወይም የአሳ ተዋጽኦ መመገብ፤ ይህን ሲያደርጉ ግን ትኩስ ወይም በጣም ያልበሰሉ አሳዎችን ለነብሰ ጡርና ለህጻናት አብዝቶ መስጠቱ አይመከርም።

አትክልቶች፦ ጠቆር ያሉ አረንጓዴ አትክትልቶችን በተለይም እንደ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ጎመን ያሉ አትክልቶችን መመገብ።

በቫይታሚን ኤ ሲ፣ ኢ እና ኬ የበለጸጉ በመሆናቸው ለልብ ጤንነት እጅጉን ተፈላጊዎች ናቸው፤ ከዚህ ባለፈም በውስጣቸው ፖታሺየም እንደመያዛቸው መጠን የደም ቧምቧዎችና የልብ ግድግዳ አካባቢ እንዳይጨናነቅ ያደርጋሉ።

ዝቅተኛ የካሎሪ መጠንና የሚሟሟ አሰርን በመያዛቸውም ለደም ዝውውርና አላስፈላጊ ኮሊስትሮልን ለማስወገድም ይረዳሉ።

ጥራጥሬና ለውዝ፦ ለውዝን ጨምሮ እንደ ሰሊጥ ያሉ የቅባት እህሎችና ሌሎች ጥራጥሬዎችን መመገብም ለልብ ጤንነት ይረዳል ነው የሚሉት የህክምና ባለሙያዎች።

እንደ ባቄላ፣ አተርና ሽንብራ ያሉ ጥራጥሬዎችን መመገብም የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ እንደሚያስችልም ነው የሚገልጹት።

እነዚህ ጥራጥሬዎች በውስጣቸው የሚሟሟ አሰር እንደመያዛቸው መጠን አላስፈላጊ ኮሊስትሮልን በማስወገድ የተስተካከለ የደም ዝውውር እንዲኖር ያደርጋሉ።

ማንጋነዝ፣ ቫይታሚን ቢ፣ ማግኒዢየም፣ ዚንክ፣ ፎስፎረስና መዳብን በውስጣቸው የያዙ በመሆናቸው በደም ውስጥ በሚገኝ የስኳር መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አይኖራቸውም።

ለደም ቧምቧዎች መስፋት፣ ኮሊስትሮልን ለመቀነስ፣ ለውዝ ማብዛት አይመከርም የካሎሪ መጠናቸው ከፍ ያለ በመሆኑ በበዛ ቁጥር ችግር ሊያስከትል ይችላልና።

ስኳር ድንች፦ በናይትሪክ ኦክሳይድ የበለጸገ ሲሆን የደም ቧምቧን በደምብ በመክፈት የደም ግፊትን ለመቀነስ ይረዳል።

የስኳር ድንች ጭማቂ ከልብ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ማስቻሉንም በአውስትራሊያ በተደጋጋሚ የተደረጉ የጥናት ውጤቶችን ጠቅሰው ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻርም መገጣጠሚያ አካባቢ፣ ካንሰርና የልብ ስራ መቆም ችግርን ለመከላከል ይረዳሉም ነው የሚሉት።

አቮካዶ፦ በቀን አድን አቮካዶን መመገብ የደም ግፊትን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ያስችልዎታል፤ አላስፈላጊ ኮሊስትሮልን ለመቀነስም ይረዳሉ።

የወይራ ዘይት፦ የደም ግፊትና አላስፈላጊ ኮሊስትሮልን ከሰውነት በማስወገድ የተስተካከለ የደም ዝውውር እንዲኖር ያስችላል።

የወተት ተዋጽኦዎች፦ የወተት ተዋጽኦ ከልብ ጋር ተያይዞ ያልተለመደ ቢሆንም እርጎ፣ ወተትና አይብ የደም ግፊትን ለመቀነስ ይረዳሉ ነው ያሉት ባለሙያዎቹ።

በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናትም እርጎን አብዝተው የሚጠጡ ከማይጠጡት በተሻለ መልኩ የደም ግፊትን ተጋላጭነትን 20 በመቶ መቀነሳቸው ተነግሯል።

የወተት ተዋጽኦዎች ካልሺየም፣ ፖታሺየም እና ማግኒዢየምን የያዙ በመሆናቸው የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ይረዳሉም ነው ያሉት።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን እነዚህ ምግቦች የበዛ ቅባት ስላላቸው ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ ባለሙያ ማማከሩም የተሻለ ይሆናል።

ከዚህ ባለፈ ግን ሃኪምን በማማከር ለልብ ጤንነት የሚረዱ ምግቦችን መመገብና መከታተል አስፈላጊ ነው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement