የሙት መንፈሱ ነገር…

                                                                               
(ኤፍሬም እንዳለ)

ሚኒባስ ታክሲ ላይ ነው … ሾፌርና ረዳት ብሶት ብቻ ነበር የሚያወሩት፡፡ ነዳጅ ውድ እንደሆነ፣ የታክሲ ታሪፉ ትንሽ እንደሆነ፣ ተራ አስከባሪዎች ጉልበተኞች እንደሆኑባቸው፣ ትራፊኮች በየመንገዱ እያስቆሙ አላሠራ እንዳሏቸው … ብቻ የማይኮንኑት የለም፡፡ እናም ሾፌር፣ 
“ይሄን ሁሉ የሚያደርገን እኮ መንግሥት ነው፣” ይላል፡፡

ረዳቱም፣ “እነሱ እኮ ታክሲ እንዲጠፋ ነው የሚፈልጉት” አይነት ነገር ይላል፡፡ ይሄኔ አንዱ ጎልማሳ ተሳፋሪ፣ “እናንተ አሁን ምን ሆንን ብላችሁ ነው መንግሥት ላይ የምታማርሩት? እኛ ነን እንጂ በስንቱ ነገር የምንሰቃየው” ይላል፡፡

ሌላ ተሳፋሪም፣ “ተዋቸው እባክህ … ምን እንዳያመጡ ነው፣ ወሬ ብቻ!” ይላል፡፡

ይሄኔ ሾፌር ሆዬ “የንጉሡን መንግሥት የገለበጡት እኮ ታክሲ ነጂዎች ናቸው” ይላል፡፡ መጀመሪያ የተናገረው ሰው ምን ቢመልስለት ጥሩ ነው፣
“አዎ፣ እነሱ መንግሥት ገልብጠዋል፡፡ እናንተ ደግሞ የሰዉን ኪስ ትገለብጣላችሁ” አላቸው፡፡

ለጠቅላላ እውቀት ያህል … 1966 የታክሲዎች ኩዴታ ነበር እንዴ!.. እየጠራ ይሂድ ብለን ነው፡፡ ምናልባት እንደ ዘንድሮ አያያዛችን ከጥቂት ዓመታት በኋላ “የ66ቱ የታክሲዎች አብዮት” ነገር ማለት ይጀምር ይሆናል፡፡ ቃልና ታሪክ ለመለወጥ ሁሉም ሰው ሊቼንሳ ያለው የሚመስልባት አገር የእኛዋ ብቻ ሳትሆን ትቀራለች…

አንድ ነገር አለ፣ ባለፈው ታሪካችን እንኮራለን፡፡ ለምን አንኮራም … በበጎው ታሪካችን ሁሉ አሳምረን እንኮራለን ! ታሪክ የሌለው አገር ሁሉ እየፈጠረ ‘ግነን በሉኝ’ ሲል እኛ … ለሌላ በሚተርፍ ታሪካችን ብንኮራ ምንም የሚገርም ነገር አለው ! ትልልቆቹ አገሮች ሚጢጢ የምታክለውን ነገር ሁሉ ልክ እንደ ተአምራዊ ታሪከ ለማድረግ ሲሯሯጡ እኛ ማጋነንም፣ ማሳበጥም ሳያስፈልገን የምንኮራባቸው በርካታ ታሪኮች አሉን…

ግን ያለፍውን በጎ ታሪክ ክሬዲት ወይም ባለቤትነት ከሠሪዎቹ ወደእኛ ሲዞር አንገት ማስደፋት አለበት፡፡ ጥያቄው የቀደሞዎቹ በጣሉት መሰረት ላይ የኋለኞቹ ምን ጨመርንበት ነው ! እንዲህ ብለን የምንጠይቅ ብዙ አይደለንም እንጂ…

የሆነ መንደርተኛ በሆነ ነገር ከጎረቤቶቹ ተጋጨ እንበል፣ “እናንተማ ምን ታደርጉ፣ ይሄን እልም ያለ ጫካ ሰፈር ያደረጉትና ያቀኑት እኮ የእኔ ወላጆች ናቸው፡፡ አዳሜ ከየትም፣ ከየትም ጨርቅሽን ጠቅልለሽ መጥተሽ…” ምናምን አይነት ደረቱን ይነፋል፡፡ እናስ ! እነሱ መንደሩን አቀኑ፣ እሱ የየጎረቤቶቹን አጥር እየነቀነቀ አይደል እንዴ ! በወር አምስት ቀን ቀበሌ እየተጓተተ አይደል እንዴ ! እሱ መንደር እያመሰ፣ መንደር ያቀኑ ወላጆቹን ክሬዲት መመንተፍ ይፈልጋል፡፡

ለምሳሌ የሆነ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪ “አብዮቱን ያመጣው እኮ የተማሪ ንቅናቄ ነው፣” ምናምን ይል ይሆናል፡፡ እና የእዛ ዘመን ተማሪዎች የረገጡትን ካምፓስ ስለረገጠ በኩራት አየር ላይ ይንሳፈፍ ይሆናል፡፡ እሺ ይሁን…ግን ልዩነቱ ለአብዮቱ አንዱ ምክንያት ነው የሚባለው የተማሪ ንቅናቄ ጥያቄው ‘መሬት ላራሹ’ የመሳሰሉት ህዝባዊ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረው ደግሞ “የዳቦው መጠን ቀነሰብን፣” አይነት ለየት ያለ ሪቮሉሽን ነው፡፡ ጦሙን እየዋለ “የእኛ ምግብ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖቻችን ይሂድልን” በሚልና “ይቺን ዳቦ በልተን ነው የምንውል!” በማለት መካከል ሦስት ውቅያኖሶች ያህል ርቀት አለ፡፡

ዘንድሮ ክሬዲት በቆረጣ ከመውሰድ ይልቅ የባሰበትና አልለቅ ያለን ነገር ያለፈውን መርገም ነው፡፡ ከአርባ፣ ከሰባ፣ ከመቶ ምናምን ዓመት በፊት የተሠሩትን፣ ወይም ባይሠሩም በድፍረት ተሠሩ የምንላቸውን አያነሳን እርግማ ! እርግማን! እርግማን! ብቻ ሆኗል፡፡

ግራ የሚገባ ነገር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይሄ እንደ ንጉሥ ሀምሌት የሙት መንፈስ አይነት፣ ያለፈው ስርአት የሙት መንፈስም መቃብር እየገለበጠ ብቅ ይላል እንዴ ለማስባል ምንም አልቀረውም! የወዲያኛው ካበቃለት ብዙ፣ በጣም ብዙ ክረምቶች አለፉ አይደል እንዴ! ላይመለስ ሄደ ከተባለ እኮ ልጅ ተረግዞ፣ ተወልዶ፣ አድጎ፣ አግብቶ፣ ወልዶ ባለቤቱ ሁለተኛውን ልጅ ጸንሳ የለም እንዴ!

እስከመቼ ነው በተለይ በፖለቲካው አካባቢ በትንሽ ትልቁ “ያለፈው ስርአት የጣለብን፣” “የአጼዎቹ ስርአት ትቶብን የሄደው፣” እየተባለ የሚዘለቀው! ጠረጴዛችን ላይ ቁራጭ ዳቦ መች ጨመረልን! ሁላችንም በቀን ሦስቴ እንድንበላ መች አደረገን! ለሚቆርጠን፣ ለሚፈልጠን፣ ለሚያንዘፈዝፈን ደዌ ሁሉ መች ፈውስ ሆነን! ስንት ሚሊዮናችን መች ውለን ስንገባ የምንጠለልበት የራሳችን የምንለው ጣራና ግድግዳ ሰጠን! መች በየአገልግሎት መስጫው ከመጉላላት አዳነን!

እውነት ለመናገር ‘ያለፈው ስርአት ጥሎብን የሄደው’ የሚባሉትን ነገሮች ሁሉ በአነኚህ ሁሉ አስርት ዓመታት ከትከሻችን ማሽቀንጠር ካልቻልን ችግሩ የእኛው ነው የሚሆነው፡፡ አሸክሞን የሄደውማ ጭኖብን ሄደ፡፡ እኛ ተሸክመን ለመቆየታችን ግን በምክንያትነት ምንም የሐምሌትን የሙት መንፈስ መጎትት አያስፈልገንም፡፡

ያለፈውም ቀድሞ የነበረውን ሲያወግዝ፣ የተከተለውም እሱን ሲያወግዝ ሁሉም አልፎን እየሄደ…ቀድሞ የወጣውን ጆሮ ኋላ የወጣው ቀንድ እየበለጠው ነው፡፡ ከሀምሳ ዓመት በፊት ኮሪያ የእኛ ቢጤ ነበረች እንደሚባለው ማለት ነው፡፡

አይገርምም፣ ሊገርምም አይችልም፡፡ አንድ ግልጽ ልዩነት አለን…እኛ ዲስኩር ስናሳምር እነሱ ሥራ እያሳመሩ ነው፡፡ ጊዜ የላቸውም፡፡ በዛሬ ወሬ የትናንቱን ጨለማ ጎትተው ማምጣትማ ፍላጎቱም፣ ሀሳቡም የላቸውም!

ብዙ ጊዜ “ከዚህኛው አገር የወሰድነው፣” “ከዛኛው አገር የቀሰምነው” የሚባሉ ነገሮች እንሰማለን፡፡ ከጠቀመን፣ እሺ ይሁን፡፡ ሁሉም አገር እየኮረጀ ነው ያደገው፡፡ ግን እኮ ከእነሱ ልንቀስማቸው የሚገቡ ሌሎችም ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጀርመኖቹ “ሂትለር አገሪቷን እንደዛ አፈራርሶ ሄዶ፣” እያሉ ሲደሰኩሩ አይደለም እንዲህ አይነት ሀያል ኤኮኖሚ የገነቡት፡፡

ጃፓኖቹ አሁንም ስለሂሮሺማና ናጋሳኪ ጠዋት ማታ እየተራገሙ አይደለም የስልጣኔ ማማ ላይ የወጡት… ሥራ ላይ ሰለሆኑ ነው፡፡ መዘከር ያለበት ነገር በተቀመጠለት ጊዜ ይታወሳል፣ ይዘከራል…አራት ነጥብ፡፡ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እብደትን እያስታወሱ ጣት ሲቀሳሰሩ አንሰማም፡፡

በታሪካቸው መከራ ያልወረደባቸው፣ በእርስ በእርስ ግጭቶችና እልቂቶች ያላለፉ ሀገራት ጥቂት ናቸው፡፡ ግን አብዛኞቹ በትናንት አልተለከፉም፡፡ የሐምሌትን የሙት መንፈስ የግድ ቆፍረው ለማውጣት በመሞከር ውድ ጊዜያቸውን አያጠፉም፡፡ ፈረንጆቹ ‘ቢቲንግ ኤ ዴድ ሆርስ’ እንደሚሉት ዘላለማቸውን የሞተውን ፈረስ ሲደበድቡ አይኖሩም፡፡ የሞተ ፈረስማ ሞቷል፣ ይልቅ የትናንቱን ፈረስ ዛሬ በምን የተሻለ ነገር እንተካው ብሎ መሥራቱ ይሻላል፡፡

ዓለም እየተለወጠች ነው፣ አስተሰሳቦች እየተለወጡ ነው፡፡ ከትናንት፣ ከትናንት ወዲያ ጋር ጥርስ በመናከስ የትም እንድማይደረስ የታወቀበት ዘመን ነው፡፡ የዘንድሮ ለውጥ የየአምስት ዓመት፣ ወይም የየዓመት አይደለም፣ የየቀንና የየሰዓት እንጂ፡፡ የትናንት ነገሮች ለታሪከ መጽሐፍት እየሆኑ ዛሬ ላይ ነገ ታሪክ የሚሆኑ ነገሮች እየተሠሩ ነው፡፡ እናማ … ብዙ ሐገራት ያለፈ ስርአትን የሙት መንፈስ እየጎተቱ ስላለሆኑ አእምሯችውን ለበጎ አውለውታል፡፡

አንዱ ስርአት በርካታ የህግ ጥሰቶችን ይፈጽማል፡፡ የሚከተለው ስርአት ያኛው የፈጸማቸውን የህግ ጥሰቶች ባለመድገሙ ብቻ የመንግሥተ ሰማያትን ቪ.አይ.ፒ. ስፍራ አያሰጠውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ “ምን ትፈልጋላችሁ ይኸው ኮንዲሚኒየም ተሰጣችሁ አይደል እንዴ! ያለፈው ስርአት እንዲህ አድርጓል?” አይነት ነገር አለ፡፡

በነገራችን ላይ፣ እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ ምልልስ ከመጣ ማለቂያ የሌለው ንትርክ ይሆናል…የጤፍን ዋጋ ለሁሉም አቅም የሚመጥን የማያደርግ ንትርክ፣ የደረቀውን የብዙ ህዝባችንን ከንፈር የማያወዛ ንትርክ፡፡ ከየት ባመጣነው ጉልበት ነው የምንነታረከው! በትንሽ ትልቁ “ያለፈው ስርአት፣” “የእነእከሌ አገዛዝ” እያልን በቃላት መተናነቃችንን ካልተውን ምናልባትም የሐምሌት ትያትሩ የሙት መንፈስ ነገር አልቀቀንም ማለት ነው፡፡

እና ነገርን ለታሪክና ለራሱ ትተን ዛሬ ላይ ማተኮሩ ብልህነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ይሆናል፡፡

ይገርማል…ነገሮች ከተለዋወጡ ሠላሳው ሊደፍን ሦስትና አራት ፈሪ ብቻ ሆኖ አሁንም ለምንም ነገር በየመድረኩ ላይ “ያለፈው ስርአት ጥሎብን የሄደው…” ምንምን ማለት አልቀረም…

“እኔ አሁንስ መሮኛል፡፡ የት አባቴ ልሂድ!”
“መረረሽ!…”
“አዎ፣ በጣም ነው የመረረኝ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ተቀምጬ መጠበቅ አለብኝ እንዴ! ለምን በጊዜ አትገባም?”
“ዝም በይ፣ ውለታ ቢስ! የመጀመሪያው ባልሽ በመጥረጊያ መንደር ለመንደር እየሯሯጠ አልነበር እንዴ የሚደበድብሽ!”

እና!…እንዴት አይነት ማመሳከሪያ ነው! የመጀመሪያ ባሏ ይፈጽም የነበረውን አይነት ወንጀል ስላልፈጸመ የመልአከ ክንፎች ልንቀጥልልት ነው! በየቀኑ መጠጡን እየተጋተ በውድቅት ሌሊት የሚመጣው እኮ ህመሙ የዱላውን ያህል ነው፡፡ ዘለዓለም የቀድሞውን ባሏን መጥፎነት እየቆፈሩ ከማውጣት ይልቅ የእሱን መልካም ባልነት በተግባር ማሳየት አይሻልም!
ዘለዓለም የዛኛውን ስርአት መጥፎነት ከመስበክ ይልቅ የተተኪውን መልካምነት በተግባር ማሳየት አይሻልም!

ትውልድ እኮ ተለውጧል፡፡ ለብዙ ነገሮች፣ ለበርካታ እውቀቶች፣ ለበርካታ ክስተቶች የተጋለጠ ትውልድ እኮ ቦታውን እየተረከበው ነው፡፡ በእርግጥ ስለትናንት ማወቅ ይፈልጋል፣ ማወቅም ይገባዋል፡፡ የነገው ጉዞ የሚሰምረው እኮ የትናንቱ ታውቆ መልካሙ ሲወሰድ፣ መጥፎው ሲራገፍ ነው፡፡ ከአዎንታዊውም ሆነ፣ ከአሉታዊው ተሞክሮ መማር ማለት ግን እርግማን በቁናና በኩንታል ማራገፍ ማለት አይደለም፡፡

ይህ ማለት ግን ቴሌቪዥኑን በከፈቱ ቁጥር፣ ጋዜጣውን በገለጡ ቁጥር ደግሞ፣ ደጋግሞ ከምክናያታዊነት ይልቅ ጥላቻ የተጫናቸው ትረካዎች ማየት አለበት ማለትም አይደለም፡፡ 
ሰዉ በአሁኑ ሰዓት የሚፈልገው ስለ ዛሬ ነው፣ መወያየት የሚፈልገው ስለ ነገ ነው፡፡ ምክንያቱም የሦስት ሺህ ዘመን እንቅልፍ የሚባለው በእሱ ዘመን መራዘመ የለበትምና ነው፡፡ ኖረበትም፣ አልኖረበትም ያለፈውን ዘመን ተረክ ጠዋትና ማታ በእርግማንና በኩነና መልክ መስማት አይፈልግም፡፡

“ያኔ እኮ መብራት የሚያገኘው ትንሽ ሰው ነበር፣ አሁን ብዙ ነው፡፡”
“ያኔ እኮ ውሀ የሚያገኘው ሰው በጣም ትንሽ ነበር፣ አሁን ስንትና ስንት ሚለዮን እያገኘ ነው፡፡”
እናስ!…የስርአት ለውጥ ያስፈለገው እኮ ለዚህ፣ ለዚህ ነው!

በነገራችን ላይ በየቦታው ያሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮዎች አለቆቻቸው በአደባባይ በሚናገሯቸው ንግግሮች፣ በሚሰጧቸው የፕሬስ መግለጫዎች ላይ የራሳቸው አስተዋጽኦ የላቸውም እንዴ! 
“ጌታዬ፣ ይሄ ያለፈውን የሚኮንነው አንቀጽ ቢወጣ የተሻለ ይመስልኛል፡፡”
“ለምን!”
“ህዝቡ ብዙ ዘመን ሲሰማው ሰለነበር በጣም ሰልችቶታል፡፡ ይልቅ ስለ ድርጅታችን ሥራና የወደፊት እቅድ ሰፋ አድርገን ብንናገር…”

ምናልባት ይህን የሚል ባለሙያ በማግሰቱ ወደ ንብረት ክፍል ዝውውር ደብዳቤ ሊደርሰው ይችላል፡፡ ያለፈውን መኮነን ማለት የበላይ አካልን ማስደሰት ማለት ነዋ!

እና የትናንት፣ የትናንት ወዲያ ስርአቶች የሙት መንፈስ እየተጎተተ ነገሩ ሁሉ የቁርሾና የማይለቅ ቂም አይነት ሲመስል ለማንም አይበጅም … በተለይ ደግሞ ለዚች ችግሮቿና የቤት ሥራዎቿ ለበዙባት አገር፡፡

እረፍት የለሽ ሥራ እንጂ፣ እረፍት የለሽ እርግማን ያበጠውን ማጉደል፣ የቆሰለውን ማሻር አይችልም፡፡ ሌላውን እንደ መርገምና መኮነን የቀለለ ነገር የለም፡፡ የብቃት ማረገጋጫ አያስፈልገውም፡፡ ጣትን እዛኛው ወገን ላይ ቀስሮ ስለ ጉድለቶቹ መንገር ቀላል ነው፡፡ ሃጢአቶቹን እየደረደሩ ውጉዝ ከመአርዮስ እንደማለት የጨርቅ መንገድ የሆነ ነገር የለም፡፡ 
ከባዱ ነገር፣ የናፈቀን ነገር በተግባር “ይኸው ይሄን ሠርቻለሁ፣” የሚል ዜማ ነው፡፡ ጣትን ወደራስ አዙሮ “ይኸው እኛ ሃላፊነታችንን አየተወጣን ነው፣” የሚል እፎይ ብሎ የሚያሰኝ ዜማ ነው፡፡

ይሄ ሁሉንም ነገር ሌሎቹ ዘመናት ላይ በኋላ ማርሽ እየሄዱ መኮነን፣ መርገም፣ “የበፊት ባልሽ በመጥረጊያ ያሯሯጥሽ አልነበረም ወይ!” “ያለፈው ስርአት እንዲህ፣ እንዲህ ሲያደርጋችሁ አልነበረም ወይ!”…” ብዙም አያራምደንም፡፡ የሙት መንፈስ ለቲያትር ሲሆን ተመልካች ይስብ ይሆናል፣ አገርና ህዝብን ግን እንዲት ስንዝር አያራምድም፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement