ወደ ኳታር መጓዝ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ካሁን በኋላ ቪዛ አያስፈልጋቸውም፤
እስኪ ለወደፊቶቹ ጎብኚዎች 5 ጠቃሚ ነጥቦችን እናካፍላችሁ።
1. የዓለማችን ሃብታም ሀገር ናት
ምንም እንኳ የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ ቢመጣም ኳታር ግን በሚያስገርም ሁኔታ እያደገች ነው።
በሀገር ውስጥ ምርት በሚገኝ የነፍሰ ወከፍ ገቢ ዓለምን እየመራች ነው። ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ያወጣው አሃዝ እንደሚያሳየው እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ በዓመት 129,726 ዶላር ገቢ ያገኛል።
ይህ ደግሞ በሁለተኝነት ከምትከተላት ሉክዘምበርግ እንኳን በ30, 000 ዶላር ይልቃል። ከአሜሪካ ደግሞ ከእጥፍ በላይ ይበልጣል።
2. የበርካታ ስደተኞች መኖሪያ ናት
በኳታር 2.6 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ይኖርባታል። ከእነዚህ መካከል 300,000 የሚሆኑት ብቻ ናቸው ዜጎቿ። ይሄ ማለት ከአጠቃላይ ነዋሪዎቿ የሀገሪቱ ዜጋ ከ7 ሰዎች አንዱ ብቻ ነው ማለት ነው።
ከእነዚህ ደግሞ ብዙዎቹ ከደቡብ እሲያ ፣ ከህንድ ፣ከኔፓልና ከባንግላዴሽ የመጡ ናቸው።
በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ለ80 ሃገራት ያለቪዛ የመግባት ፈቃድ በመስጠቷ ወደሃገሪቱ የመሄዱን ሂደት አቅለዋለች።
3. የወንዶች ቁጥር ከሴቶች በእጅጉ ይበልጣል
በእርግጥ ኳታር ሚስት ለማግኘት ተመራጭ ሀገር አይደለችም ምክንያቱም ከህዝብ ብዛቷ ሴቶች 25 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ። ከስደተኞቹ ብዙዎች ወንዶች መሆናቸው ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
4. ነጻ ሃሳብን ትደግፋለች(ገደብ ቢኖረውም)
በርካታ የአረብ ሀገራት በመንግሥታቸው ላይ ትችቶችን ስለሚዘግብ በአልጀዚራ ደስተኞች አይደሉም። ይህም በአንዳንድ የአረብ ሀገራትና በኳታር መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረትን ፈጥሯል። ሆኖም የኳታሩ ኤሚር ራሳቸውን በተመለከተ ምንም አይነት ትችት አይቀበሉም፤ ይህን ተላልፎ እርሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚያሳጣ ነገር ያሳተመ ከፍተኛ ቅጣትና የእስር ጊዜ ይጠብቀዋል።
5. የዓለም ዋንጫን ልታስተናግድ ነው
በአምስት ዓመታት ውስጥ የዓለማችን ታልቁ የስፖርት ክስተት በኳታር አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በእርግጥ እስካሁን የዓለም ዋንጫን ለማዘገጃት የሚያስችላትን ውድድር ለማሸነፍ ጉቦ ሰጥታለች በሚል በመወንጀሏ መቶ በመቶ አልተረጋገጠም።
ይህ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ ዕድሉ ለሌላ ሀገር ሊሰጥ ይችላል።ካስተናገደች ደግሞ የኳታርን ከፍተኛ ሙቀት ለመከላከል በክረምት የሚካሄድ የሚጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ይሆናል።
ምንም እንኳ የዓለማችን ሃታም ሀገር ብትሆንም ጫወታው የሚካሄድባቸውን ስታዲየሞች በሚገነቡት ስደተኞች ላይ ያለፈቃዳቸው በጉልበት የማሰራትና የሰብአዓዊ መብት ጥሰት ትፈጽማለች በሚል በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተወንጅላለች።
ምንጭ: ቢቢሲ