የአሜሪካ ክሊኒካል ኦንኮሎጂ ማህበር ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የአልኮል መጠጥ ከካንሰር ጋር ግንኙነት እንዳለው አስታውቋል።
አልኮል መጠጣት ለሰባት የካንሰር አይነቶች እንድንጋለጥ ያደርጋል ያለው ማህበሩ፥ ከእነዚህም ውስጥ የአፍ፣ የጉሮሮ እና የጡት ካንሰር እንደሚገኙበት አስታውቋል።
የአሜሪካ ክሊኒካል ኦንኮሎጂ ማህበር ሪፖርቱን ያወጣው አልኮል የሚጠጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ነው ተብሏል።
አልኮል በዓለማችን ላይ ለሚከሰቱ ካንሰር እና የካንሰር ህመም ሞቶች ውስጥ 5 በመቶውን እንደሚይዝም ሪፖርቱ አመልክቷል።
ሪፖርቱ በቀን ውስጥ ለሴቶች ከአንድ እና ከዚያ በታች የአልኮል መጠጣት እንዲሁም ለወንዶች ሁለት እና ከዚያ በታች አልኮል መጠጣት ለእነዚህ የካንሰር አይነት ተጋላጭነተን እንደሚቀንስም አመልክቷል።
ነገር ግን አልኮልን አብዝተን በጠጣን ቁጥር ለሰባት የካንሰር አይነቶች ያለን ተጋላጭነት እየጨመረ ይሄዳል ነው የሚሉት የማህበሩ ኦንኮሎጂስት።
አልኮል በመጠጣት የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶችም፦
- የአፍ ካንሰር
- የጉሮሮ ካንሰር
- የአፍና ሆድን የሚያገናኝ ትቦ (Esophageal) ካንሰር
- የድምፅ ሳጥን (Larynx) ካንሰር
- የጉበት ካንሰር
- የሴት ጡት ካንሰር
- የአንጀት ካንሰር
የአሜሪካ ክሊኒካል ኦንኮሎጂ ማህበር ባወጣው ሪፖርት አነስተኛ የአልኮል መጠን ያለውን እንደ ቢራ እና ወይን ያሉ መጠጦችን አብዝተው የመሚጠጡ ሴቶች ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድላቸው በ5 በመቶ ከፍ እንደሚል ያሳያል።
“መጠጥ የማትጠጡ ከሆነ አትጀምሩ” የሚሉት የማህበሩ ዶክተር ሎ ኮንቴ፥ “አልኮል የምትጠጡ ከሆነ ደግሞ በቀን ውስጥ ሴቶች በቀን ውስጥ 1 እና ከዚያ በታች ወንዶች ደግሞ ሁለት እና ከዚያ በታች አልኮል ቢጠጡ መልካም ነው” ሲሉ ይመክራሉ።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)