10 የአለማችን አስገራሚ ሰዎች – 10 Amazing People Of The World

ሁላችንም ከሌላው ሰው ጋር ለየት የሚያደርገን በህሪያትና ችሎታዎች የታደልን ነን፡፡ ይሁንና የአንዳንድ ሰዎች የተሰጣችው ልዩ ችሎታ በጣም የሚገርምና ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል በአለማችን በጣም አስገራሚ የሆኑ  ሰዎችን ተፈጥሮ ካደለቻቸው ልዩ ብቃታቸው ጋር እናያለን፣

 

  1. ወገበ-ቀጭ እመቤት

 

                                                      

የ26 አመቷ ጀርመናዊት ሚሸል ኮብከ በአለማችን ወገበ-ቀጭኗ እመቤት ስትሆን፤ የወገቧ መጠነ-ዙሪያ 40.64 ሳንቲ ማትር ወይም 16 ኢንች ነው፡፡ ሚሸል የወገቧን መጠነ-ዙሪያ ከዚህም በታች ወደ 35.56 ሳንቲ ማትር ወይም 14 ኢንች  የማሳነስ ዕቅድ እንዳላት ትናገራለች፡፡ “ችቦ አይሞላም ወገቧ ማር እሸት ነው ቀለቧ” የተባለው ለዚች አይነቷ ቆንጆ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 

  1. ብረት-በሉ ሰው

                                                                               

ይህ ግለሰብ ሚቸል ሎቲቶ ይባላል የፈረንሳይ ዜግነት ያለው ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሠኔ 15 ቀን 1950 ነበር የተወለደው፡፡ ሚቸል ሎቲቶ  አንድን አውሮፕላን በሁለት አመታት ውስጥ አጣጥሞ እንደበላ ይነገርለታል፡፡ በ40 አመት ጊዜ ውስጥ ሚቸል ሎቲቶ ከዘጠኝ ቶን በላይ ክብደት የሚመዝን ብረት ተመግቧል፡፡ መቸም ሰው በጤናው ብረትን አይመገብምና “ይህ ሚቸል የተባለ ግለሰብ ግን ጤነኛ ነው?” ብለው ሳይጠይቁ አይቀሩም:: ሚሸል ፒካ የተባለ የአእምሮ ህመም ተጠቂ ሲሆን፣ የህመሙ ዋነኛ ባህሪይ ሰዎች በተለምዶ የማይመገቧቸውን ነገሮች (ብረትና ፕላስቲክ የመሳሰሉትን) እንድንመገብ የሚያደርግ ነው፡፡

 

  1. ፂመ-ረጅሙ ሰው

                                                                           

ራም ሲንግ ቹዋሃን ይባላል ህንዳዊ ነው በአለማችን ፂመ-ረጅሙ ሰው ለመባል በቅቷል፡፡ የራም ፂም 4.29 ሜትር የሚረዝም ሲሆን በቀን ውስጥ አንድ ሰዓት የሚሆነውን ጊዜ ፂሙን በማጽዳትና በማበጠር ያሳልፋል፡፡ አሪፍ ጊዜ ማሳለፊያ ያገኘ ይመስላል፡፡

 

  1. እድሜ-ጠገቡ ፓይለት

                                                                        

አቶ ፒተር ዌበር ጁኒየር የተባሉት አሜሪካዊ በአለማችን እድሜ ጠገቡ አውሮፕላን አብራሪ መሆናውን አለምአቀፋዊው የክበረ ወሰን መዝገብ ያስረዳል፡፡ አቶ ፒተር የ96 አመት ወጣት ሲሆኑ ላለፉት 72 አመታት አውሮፕላን ሲያበሩ ቆይተዋቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በወር ቢያንስ ለሁለት ጊዜ የሰማይ ላይ ጉዟቸውን እንደሚያከናውኑ አቶ ፒተር ይናገራሉ፡፡

 

  1. እድሜ-ጠገቧ የዮጋ መምህርት

                                                                       

አሁን ደግሞ ከእድሜ ጠገቡ አውሮፕላን አብራሪ ወደ እድሜ-ጠገቧ የዮጋ መምህርት እንሸጋገር፡፡ ወይዘሮ ታኦ ፖርቸን-ሊንች የ96 አመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ለ70 አመታት የዮጋ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ዘወትር ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ ወይዘሮዋ ተማሪዎቻቸውን ሰብስበው እንዴት ሰውነታቸውን ማጠፍና መዘርጋት እንደሚችሉና ሌሎችን የዮጋ ዘዴዎች ያስተምራሉ፡፡

 

  1. አፈ-ሰፊው ሰው

 

                                                                     

ፍራንሲስኮ ዶሚነጎ ጃኩይም ይባላል በአለማችን ትልቅ የሆነውን አፍ በመያዝ ክብረ ወሰኑን ሰብሮ ይገኛል:: የጃኩይም አፍ ከዳር እስከዳር 17ሳንቲ ማትር ወይም 6.69 ኢንች ያህል ይሰፋል፡፡

 

  1. ብረ ንግስት

                                                                      

አሻ ራኒ የሁለት የአለም ክበረ-ወሰኖች ባለቤት ነች፤ ከባድ ነገሮችን በጸጉሯና በጆሮዋ በመጎተት ብቃቷ፡፡ የ23 አመቷ አሻ በዚህ ለዩ ችሎታዋ ብረቷ ንግስት የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷታል፡፡

 

  1. ቀንዳሟ ወይዘሮ

                                                                        

ይህ ደግሞ ከወደ ቻይና የተገኘ አስገራሚ ዜና ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2010 ዣንግ ሩይፋንግ የተባሉ ወይዘሮ ግንባራቸው ላይ ቀንድ በማብቀል አለምን አስደምመዋል፡፡ ወይ ጉድ!!

 

  1. የብርቱ ሳንባ ባለቤት

 

                                                                    

እርስዎ ምን ያህል መጠን ያለውን ፊኛ መንፋት ይችላሉ? ማንጂት ሲንግ የተባለው ግለሰብ ግን 2.5 ሜትር መጠነ-ዙሪያ ያለውን ፊኛ በ42 ድቂቃ ውስጥ በመንፋት በአለማችን የጠንካራ ሳነባ ባለቤት መሆኑን አስመስክሯል፡፡

 

  1. እጁን እንዳነሳ የቀረው ሰው

                                                                     

ይህ ሰው የሂንዱ እምነት ተከታይ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1973 ሳደሁ አማር ባራቲ የተባለ ግለሰብ የሂንዱ አምላክ ክብር ሲል ቀኝ እጁን አነሳ፤ ከዛን ቀን ጀምሮ ለአምላኩ ክብር ያነሳውን እጁን አላወረደም፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

 

 

Advertisement