ሰዎች ብቻቸውን የሚመገቡ ከሆነ ለጤናቸው መልካም አይደለም

                                                

ሰዎች ብቻቸውን የሚመገቡ ከሆነ ለጤናቸው መልካም እንዳልሆነ አንድ ጥናት አመላከተ።

የደቡብ ኮሪያ ተመራማሪዎች የሴቶች እና የወንዶችን የአብሮነት እና የብቻ የአመጋገብ ሁኔታን በማጥናት የሁለቱን ልዩነትም አነፃፅረዋል።

በዶንጉክ ዩኒቨርሲቲ የኢልሳን ሆስፒታል ተመራማሪዎች፥ ምግብ ብቻቸውን በሚመገቡ በ7 ሺህ 725 ጎልማሳዎች ላይ ጥናት አድርግዋል።

የጥናቱ መሰረታዊ ዓላማም ሰዎች ብቻቸውን መመገባቸው በጤናቸው ላይ ጉዳት ያደርሳል ወይስ አያደርስም የሚለውን ማሳወቅና ጥንቃቄ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ መስጠት ነበር።

በዚህም በቀን ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻቸውን የሚመገቡ ሴቶች 29 በመቶ ለኮሌስትሮል ችግር እና ለደም ግፊት ከፍ ማለት የመጋለጥ እድል እንዳላቸው ተጠቁሟል።

ተመራማሪዎቹ በአጠቃላይ ሰዎች ብቻቸውን መመገባቸው ለጤናቸው መልካም እንዳልሆነ ደርሰንብታል ያሉ ሲሆን፥ ችግሩ ደግሞ በወንዶች ላይ ሊበረታ ይችላል ብለዋል።

ወንዶች ብቻቸውን የሚመገቡ ከሆነ 45 በመቶ ከመጠን በላይ የመወፈር እድል እንደሚኖራቸው ነው የተገለፀው።

ከፍተኛ የደም ግፊት እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ደግም 65 በመቶ ሊያጋጥሟቸው ይችላል።

በአሜሪካ ከሚኖሩ ቤተሰቦች መካከል 27 በመቶዎቹ ብቻቸውን የሚኖሩ ወይም አንድ ሰው ብቻውን እንደሚኖር ተጠቁሟል።

ከፈረንጆቹ 1920 ወዲህም ብቻቸውን የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ መሆኑን ነው ጥናቱ ያሳየው።

ተመራማሪዎች ጥናቱን ያካሄዱበት ዋና ምክንያት በዓለም ላይ ብቻቸውን የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው ተብሏል።

የሰዎች ብቻቸውን መኖር ደግሞ ለተለያዩ ማህራዊ ችግሮች የሚያጋልጣቸው ሲሆን፥ በተለይም ብቻቸውን የሚመገቡ ሰዎች ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን ተከትሎ ነው ጥናቱ ይፋ የሆነው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement