በብዛት ለምግብ ማጣፈጫነት በጥቅም ላይ የሚውሉት ቅመሞች ከማጣፈጫነት በዘለለ ለጤናችን ጠቀሜታ እንዳላቸው በብዛት ይነገራል።
ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እንዲህ አቅርበናቸዋል፦
ቀረፋ
ቀረፋ ጥንታዊ የቅመም አይነት እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፥ ከ2 ሺህ 500 ዓመት በፊት በግብፃውያን በጥቅም ላይ መዋል እንደጀረ ይነገርላታል።
በሀገራችን በብዛት በሻይ ውስጥ እና አልፎ አልፎ ለአንዳንድ ምግቦችም ለማጣፈጫነት ይውላል።
ቀረፋ ከዚህ በዘለለ ጎጂ የኮሊስትሮል መጠንን በመቀነስ ከልብ እና አተነፋፈስ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመከላከል ያግዛል ተብሏል።
ስለዚህ የምንጠጣው ሻይ ውስጥ በማስገባት መጠጣት አሊያም በደንብ እንዲፈጭ በማድረግ ለምግብ ማጣፈጫነው ማዋል ይመከራል።
እርድ
በህንድ ለአንጀት ካንሰር የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፥ ምክንያቱ ደግሞ እርድ በሀገሪቱ በብዛት ጥቅም ላይ ስለሚውል ነው ተብሏል።
በቅርብ ጊዜ የተሰሩ ጥናቶችም እርድ በውስጡ የፀረ ባክቴሪያ፣ ፀረ ፈንገስ፣ ፀረ ቫይረስ እና ፀረ ካንሰር የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም እርድን በምግባችን ውስጥ መጨመር የደም ቧንቧዎቻችን ጤና ለመጠበቅ እና የደም መርጋትን ለመቀነስ ይረዳል ተብሏል።
ሚጥሚጣ
ሚጥሚጣ በውስጡ የቫይታሚን ሲ ንጥረ ነገር ያለው ሲሆን፥ ይህም በ100 ግራም ሚጥሚጣ ውስጥ 80 ነጥብ 6 ሚሊግራም ቪታሚን ሲ ማግኘት እንችላለን።
ይህም በእለት ከሚያስፈልገን የቫይታሚን ሲ መጠን 97 በመቶ ነው ሲሉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
ሚጥሚጣ ከቫይታሚን ሲ በተጨማሪ፥ ቫይታሚን ኬ፣ ቢ6 እና ኢ እንዲሁም ፖታሲየም፣ ፎሌት ማግኒዥየም፣ አልፋ እና ቤታ ካሮቲን፣ ሉቴዪን እና ሌሎች ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይዟል።
ዝንጅብል
ዝንጅብል ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ከሚመከሩ የስራስር አይነቶች አንዱ ነው።
ይህ ስራስር ከምግብ ማጣፈጫ እና መቀመሚያነት ባለፈም በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል።
የጤና ባለሙያዎችም ለምግብ ማጣፈጫ የሚሆነው ዝንጅብል በርካታ የጤና ትሩፋቶች እንዳሉት ይገልጻሉ።
በዱቄት መልክም ሆነ በጥሬው ቢጠቀሙት መልካም ነው ይላሉ፤ ለዚህ ደግሞ በቀን 2 ግራም ዝንጅብልን መጠቀምን ይመክራሉ።
ይህም የተወቀጠ 1 የሾርባ ማንኪያ ወይም ከአንድ የሻይ ማንኪያ ጎደል ያለ የዝንጅብል ዱቄት ይሆናል።
ምንጭ:- ዶክተር አለ (Doctor Alle)