የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የምንለው ከኩላሊት እስከ የውሃ ሽንት ማስወገጃ ጫፍ ድረስ የሚከሰተውን የኢንፌክሽን ዓይነት ነው፡፡
በአብዛኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚያጠቃው የውሃ ሽንት የሚከማችበት እና ፊኛ በመባል የሚታወቀውን የአካላችን ክፍል ነው፡፡
በሴቶች ተፈጥሮአዊ የሆነ የሽንት ቧንቧ ጫፍ ማጠር ምክንያት ከወንዶች ይልቅ ተጠቂነታቸው እንደሚጨምር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሕመምን የመከላከል አቅማቸው የቀነሰ እንደ የስኳር ሕመምተኞችና እርጉዝ ሴቶች ላይም በብዛት ይከሰታል፡፡
► የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዴት ሊከሰት ይችላል?
ባክቴሪያ ከሽንት ማስወገጃ ጫፍ ወደላይኛው የሽንት ቧንቧ አካል ይገባል፡፡ ይህም ሊከሰት የሚችለው በአካባቢው የሚገኘው የሠገራ ማስወጫ በባክቴሪያ የተበከለ ስለሆነ ነው፡፡
በመሆኑም
በምንፀዳዳበት ጊዜ የግል ንጽህናን ባለመጠበቅ (ባለመታጠብ)
በግብረሥጋ ግንኙነት ጊዜ
በተለያየ ምክንያት ሽንትን ለማስወገድ የሽንት ቱቦ በሚገባበት ወቅት ሊከሰት ይችላል፡፡
የኩላሊት ጠጠር እና የፕሮስቴት እጢ ያሉት ሕመሞች ደግሞ ተፈጥሮአዊ የሆነውን የውሃ ሽንት አወጋገድን በማስተጓጎል ለኢንፌክሽን ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ በደም ውስጥ የሚገኝ ባክቴሪያም ይህንን ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል፡፡
► የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የውሃ ሽንት በምንሳወግድበት ጊዜ የማቃጠል ስሜት መሰማት
የሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት
ከእንብርት በታች የሕመም ስሜት መሰማት
ደም የቀላቀለ ወይንም መጥፎ ጠረን ያለው ሽንት መኖር
ትኩሳትና ብርድ ብርድ የማለት ስሜት መሰማት
የማቅለሽለሽ ስሜትና ማስመለስ ናቸው
እነዚህ ምልክቶች በተለይ የስኳር ሕመምተኛ፤እርጉዝ ሴት፤የኩላሊት ሕመም ተጠቂ የሆኑ እና በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ከተከሰቱ ጊዜ ሳይሳጡ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ቦታ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
► የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን እንዴት መከላከል ይቻላል?
በብዛት ፈሳሽ መውሰድ ባክቴሪያ በሽንት ቧንቧ ውስጥ እንዳይቀመጥ በማድረግ ይከላከላል፡፡
ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ እና ከተፀዳዱ በኋላ የግል ንጽሕናን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡
ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)