ግላውኮማ የምንለው የአይን ህመም በአይናችን ነርቭ ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን በአይናችን ውስጥ የሚገኘው ግፊት መጨመር ምክንያት የሚከሰት ነው። የዚህ ግፊት መጨመር በአይናችን የምናያቸውን ምስሎች ወደ አንጎል የሚውስደውን የአይናችንን ነርቭ ይጎዳል ይህም በቀጣይነት ቋሚ ለሆነ የአይን ብርሃንን እጦት ይዳርጋል።
ግላውኮማ በሚጀምርበት ጊዜ የሚያሳየው ቀዳሚ ምልክት ወይንም የህመም ስሜት ስለሌለ ማንኛውም ሰው መደበኛ የሆነ የአይን ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው ይህም አይናችን ለከፋ ጉዳት ከመጋለጡ በፊት ህክምና እንድናደርግለት ይረዳናል። ከ 40 አመት እድሜ በላይ ያሉ ሰዎች በአመት አንድ ጊዜ ወደ ሃኪም በመሄድ ምርመራን ማድረግ አለባቸው።
የአይናችን ውስጥ ግፊት ለምን ይጨምራል?
ግላውኮማ የሚከሰተው በአይናችን ውስጥ የሚገኘው ግፊት ሲጨምር ነው ያልን ሲሆን ይህ ደግሞ በዘር ፣ በኢንፌክሽን፣በአይን በቀዶ ጥገና ምክንያት በፊተኛው የአይናችን ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ በጤናማ ሁኔታ መንሸራሸር ሲያዳግተው ነው።
ግላውኮማ በአብዛኛው ሁለቱንም አይነቶች የሚያጠቃ ሲሁን የህመሙ ክብደት ግን ሊለያይ ይችላል።
በግላውኮማ የሚጠቁ እነማን ናቸው?
* ከአርባ አመት እድሜ በላይ የሆኑ
*በግላውኮማ የተጠቃ ቤተሰብ ያላቸው
*የስኳር ህመምተኞች
*የአይን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች
የግላውኮማ ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በአብዛኛው ግላውኮማ በቅድሚያ የህመም ምልክት ላያሳይ ቢችልም ከጊዜ በሗላ ግን የመጀመሪያ ምልክት የሚሆነው በጥግ በኩል የሚጀምር የአይን ብርሃን ችግር ነው።
ከምልክቶቹ ውስጥ:-
*ድንገተኛ የሆነ የአይን ህመም
*ከፍተኛ የራስ ምታት
*የአይን ብዥታ
*ጥርት ያለ እይታ አለመኖር
*የአይን መቅላት
*የአይን ብርሃን ማጣት
*የአይን እይታ ጥበት ናቸው
እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥምዎ በአፋጣኝ ወደ አይን ሀኪም መሄድ ይጠበቅቦታል።
ግላውኮማን መከላከል ይቻላል?
ግላውኮማ እንዳይከሰት መከላከል የማንችል ሲሆን ነገር ግን በቶሎ የህመሙ መኖር ከታወቀ ለመቆጣጠርና እንዳይባባስ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በግላውኮማ ምክንያት የተከሰተ የአይን ብርሃን ጉዳት ተመልሶ ሊስተካከል የማይችል ሲሆን የነበረው ጉዳት እየተባባሰ እንዳይሄድ ግን የአይን ግፊት መጠኑን መቀነስ ይቻላል። ህክምናቸውን በሚገባ የሚከታተሉ ታካሚዎች የአይን ብርሃናቸውን ማዳን ይችላሉ።
ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)