በርካቶች ከደም ማነስ ይልቅ ስለ ደም ግፊት እና ደም ብዛት ማውራት ይቀናቸዋል።
ይሁን እንጅ ደም ማነስም ከደም ብዛት ያልተናነስ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።
አንዳንድ ጊዜ ለረጅም ጊዜ ተቀምጠው ቆይተው ሲነሱ አልያም ተመግበው ከመቀመጫዎ ሲነሱና ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆሙ የማዞር አጋጣሚ ይከሰታል።
መሰል አጋጣሚዎች ደግሞ ከደም ማነስ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የህክምና ባለሙያዎችም ሰዎች ለደም ግፊት የሚሰጡትን ትኩረት ያክል ለደም ማነስም ሊሰጡ እንደሚገባ ይመክራሉ።
እነዚህ ደግሞ የደም ማነስ መከሰቱን ማሳያ ምልክቶች ናቸው፤
የመፍዘዝና በአግባቡ ማስተዋል አለመቻል፦ ይህ ምልክት ከቀላል ራስ ምታት ጋር ከተከሰተ የደም ማነስ ችግር ሊሆን ይችላል።
የደም ማነስ ሲከሰት ወደ አዕምሮ የሚፈሰው የደም መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፥ ይህ ደግሞ ወደ አዕምሮ የሚሄደውን የኦክስጅን መጠን በማሳነስ የመፍዘዝ ስሜትና በአግባቡ እንዳያስተውሉ ያደርጋል።
ይህ አጋጣሚ በአብዛኛው ማለዳ ከእንቅልፍዎ እንደነቁ ከአልጋ ላይ ፈጥነው ሊወርዱ ሲሞክሩ ሊስተዋል ይችላል።
ከፍተኛ ድካም፦ ደም ማነስ ሃይልዎን በማሳጣት ለከፍተኛ ድካም ይዳርጋል፤ በሰውነት ውስጥ የሚኖር የደም ዝውውር ዑደት ሃይልና እና አቅም ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው።
በዚህ ችግር ከተጠቁ ተኝተውም ሊደክምዎት ይችላልና መሰል ሁኔታ ሲከሰትብዎት ወደ ሃኪም ቤት ቢያቀኑ መልካም ነው።
ፈጣን የልብ ምት፦ ይህም ደም ማነስ መከሰቱን ማሳያ አንደኛው ምልክት መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ወደ ልብ ዝቅተኛ የሆነ የደም ፍሰት ካለ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እንዲኮማተር ያደርገዋል፤ ይህን መሰሉ የደም እጥረት ሲከሰት ደግሞ ባልተለመደ መልኩ ፈጣን የልብ ምት እንዲከሰት ያደርገዋል።
ይህም ፈጣን አተነፋፈስ እንዲኖር በማድረግ ምናልባትም ያልተለመደ የሰውነት ሙቀት መቀያየር እንዲኖር ሊያደርግም ይችላል።
ከልብ ጋር የተያያዘ ነገር በሙሉ አደጋው የከፋ ሊሆን ስለሚችል፥ መሰል አጋጣሚ ሲከሰት በተቻለ መጠን ወደ ህክምና ተቋም ማምራት ተገቢ ይሆናል።
የእጅ መዳፍና ቆዳ መርጠብና መቀዝቀዝ፦ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ውጭ መሰል አጋጣሚ ከተከሰተ በደም ማነስ መጠቃትዎን ማሳያ ሊሆን ይችላል።
ሁኔታው በተለይም ከፈጣን የልብ ምት እና ጥልቅ አተነፋፈስ ጋር ጋር ከተዋሃደ ደግሞ መታየት ይኖርብዎታል።
ትኩረት ማጣት፦ በሚያስተውሉ ጊዜ ትኩረት የሚያጡ ከሆነ ደም ማነስ ተከስቶ ሊሆን ይችላልና መታየቱ አይከፋም።
በሰውነት ውስጥ ከተከሰተው የደም ማነስ ጋር ተያይዞ አዕምሮ በቂ የደም መጠን አይደርሰውም፤ ይህ ደግሞ በአዕምሮ ውስጥ የሚገኙ ህዋሳትን ኦክስጅን በማሳጣት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደርጋቸዋል።
በዚህ ጊዜም በአግባቡ ማስተዋልና መመልከት አለመቻል ስራን በትክክል አለመከወን ይከሰታል፥ መሰል ሁኔታዎች ሲከሰቱም ሃኪምን ማማከርና መታየቱ የተሻለ መሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ።
እንግዳ የሆነ የውሃ ጥም ስሜት፦ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሰውነት ፈሳሽ ያጠረው ያክል አሁንም አሁንም ውሃ የመጥማት ስሜትም ሌላው የዚህ ችግር ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ ስሜት ሰውነትዎ በርካታ መጠን ያለው ፈሳሽ ወደ ደም ውስጥ እንዲገባ መፈለጉን ማሳያና ደም ማነሱን ማመላከቻም ነው።
የተጋረደ እይታ፦ አንድን ነገር በትክክል ማስተዋልና መመልከት አለመቻልና ሲመለከቱ የተጋረደ ነገር ከተመለከቱ ይህም ምልክቱ ነውና መጠንቀቁ አይከፋም።
በሰውነት ውስጥ የደም ማነስና ያንን ተከትሎ የሚመጣው የኦክስጅን እጥረት አይን ትክክለኛውን ስራ በአግባቡ እንዳይሰራ ያደርገዋል፥ በዚህም የተጋረደ እይታና ብዥታ ይከሰታል።
ከዚህ ባለፈም ማስመለስ፣ ድብርትና መጫጫን፣ መፍዘዝ፣ ራስ ምታት፣ የአንገት አካባቢ እንደልብ አለመታዘ፣ ከበድ ያለ ሳል፣ በጀርባ የላይኛው ክፍል ላይ የሚሰማ ህመምና የስርዓተ ምግብ አለመፈጨትም የዚህ ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ።
ማለዳ እንደነቁ በፍጥነት ከአልጋ ወርዶ ለመቆም አለመሞከር፣ ውሃ በብዛት መጠጣት፣ ሲቀመጡ እግርን አለማጠላለፍ፣ በቫይታሚን ቢ12 እና ፎሊክ አሲድ የበለጸጉ ምግቦችን ማዘውተር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ በቂ እረፍትና መኝታ፣ ሲጋራና አልኮል ማስወገድ፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬን በብዛት መመገብ ደግሞ ለዚህ መፍትሄዎች ናቸው።
ምንጭ:- ጤናችን