ጥንዶች ትኩረት ሊያደርጉባቸው የሚገቡ ጉዳዮች

                                                        

የፍቅር ግንኙነት ሰጥቶ መቀበልን መሰረት ያደረገና በአንድ ወገን የላይነት ሳይሆን በትብብር መንፈስ የተቃኘ ሲሆን ረጅም ጊዜ የመቆየትና ጠንካራ የመሆን አቅም አለው።

በጣም ቀላልና ትልቅ ቦታ የማይሰጣቸው ለሽርሽር ሲወጣ የሚያዙ እቃዎችን መምረጥና ማደራጀትን ጨምሮ ሌሎች ቀላል ተግባራትም ለዘለቄታዊ የፍቅር ግንኙነት የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ይነገራል።

ዘወትር በፍቅር ህይዎት ውስጥ በሰከነ መንፈስ ነገሮችን መመልከትና በመወያየት ልዩነቶችን መፍታት ፍቅርን ለማጠንከርና ለማዝለቅ ይረዳል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ጭቅጭቅ የበዛበትና መነጋገር የሌለበት የፍቅር ህይዎት ቆይታው አጭርና አሰልች ይሆናል።

የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደግሞ ጥንዶች በፍቅር ህይዎታቸው ውስጥ ልብ ሊሏቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ያነሳሉ።

ከዚህ በታች የተጠቀሱትም ለፍቅር ህይዎት መሰናከል መንስኤና በፍቅር ህይዎት ውስጥ የደስታ ስሜት እንዲጠፋ የሚያደርጉ ናቸው።

መሰረታዊ ባህሪንና ማንነትን መደበቅ፦ አንዳንድ ጊዜ በእርስዎ ስብዕና፣ ድርጊትና ጓደኞች ምክንያት የፍቅር አጋርዎ በጣም እንደተጎዳ፣ እንደተገለለና ምናልባት እንደተበሳጨ ሊጨነቁና ሊያስቡ ይችላሉ።

ከዚህ አንጻርም አዋዋልዎን፣ ጓደኞችዎንና የሚያደርጉትን ድርጊትና መሰረታዊ ማንነትዎን ሊደብቁና ምናልባት ሊቀንሷቸው ይችሉም ይሆናል።

ግን ይህን በማድረግዎ የእርስዎ የሆነን ነገር ከማሳነስና ዋጋ ከማሳጣት ውጭ የተለየ ትርፍ እንደማይገኝ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከዚህ አንጻርም መሰል አካሄድ አፍራሽ ጎኖቹ ይበዛሉና በተቻለ መጠን ከአጋርዎ ጋር በመወያየት ማሳዎቅ።

ምናልባት የእኔ የሚሏቸው መገለጫዎችና ወዳጅ ዘመድም ሆነ ጓደኞችዎ ለእርስዎ ምን ያክል አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆኑ ማሳየትና ማስረዳትም ይኖርብዎታል።

ከዚህ ባለፈም የፍቅር ህይዎታችሁ በመሰል አጋጣሚዎች እና ድባብ ታጅቦ መዝለቁ ያለውን ጠቀሜታ በማስረዳትም ድብብቆሹን ማቆም ይገባዎታል።

አለመፈለግን ከልክ በላይ መታገስ፦ ያለመፈለግና የመገለል ስሜት የፍቅር ህይዎት በአጭሩ እንዲቋጭ ከሚያደርጉ አጋጣሚዎች መካከል ከቀዳሚዎቹ ይጠቀሳል።

በአንድ ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለፍቅር አጋርዎ ክብር አለማሳየትና እንደማይፈልጉት/እንደማይፈልጓት ማሳየትና ማግለል ከልክ በላይ ስሜትን ይጎዳል።

በዚህ ወቅት እምነት እንደሌለዎት ማሳየት የበዛ ማግለልና ቸል ማለት ማሳየትን መታገስም ዋጋ ያስከፍላል።

በዚህ ወቅት ታዲያ በግልጽ ተነጋግሮ በመወያየት የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር።

ችግር ሲፈጠር መሰል ባህሪን ከማሳየት ይልቅ ችግር መፍቻ መንገዶችን መለየትና በዚያ አግባብ ልዩነቶችን መፍታት ቀዳሚው ሊሆን ይገባል።

በነገሮች ላይ የሚስተዋል የበዛ ልዩነት፦ ምናልባት ቤት ውስጥ ከእቃዎች አቀማመጥ ጀምሮ በነገሮች ላይ የተለያዩ አይነት ፍላጎቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ተገናኝታችሁ ስትዝናኑም ሆነ አንድ ነገር ስትከውኑ በይሉኝታ ተይዛችሁ መሆን አይኖርበትም።

ያላችሁን ልዩነት ለማስወገድና ወደ አንድ ለመምጣትም በአግባቡ መነጋገርና መወያየትን መልመድና ልዩነቶችን በዚያ አግባብ መፍታት።

በዚህ መልኩ ከአለባበስ የሚጀምር ልዩነትን ተነጋግሮ መፍታት ከፍ ወዳለው ደረጃ ለመድረስ የመጀመሪያው እርምጃ ነውና ይጠቀሙበት።

ከዚህ በተጨማሪም በበዛ መልኩ በነገሮች ላይ ቀዝቀዝ ያለ ስሜት ማሳየት፣ ከእርሱ/እርሷ ስልክ እስከሚደዎል መጠበቅ እንዲሁም ምቾት በማይሰማዎት ጊዜ በይሉኝታ ታስሮ መገናኘት ከጠቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና ባይከውኑት ይመረጣል።

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement