በመካከለኛ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ፍጥነት የታከለበት የእግር ጉዞ ማድረግ አለባቸው::

                                           

መካከለኛ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍጥነት የታከለበት የእግር ጉዞ ቢያደርጉ ለጤናቸው ጠቃሚ መሆኑን አዲስ የወጣ ጥናት አመልክቷል።

ጥናቱ ሰዎች እድሜያቸው እየጨመረ በመጣ ቁጥር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየቀነሰ መምጣቱ የፈጠረው ስጋት ላይ ተመስርቶ ነው የተሰራው።

ጥናቱን ያካሄዱት የእንግሊዝ የጤና ባለሙያዎች፥ ሰዎች እድሜያቸው 40 ሲያልፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ እንደሚመጣ ይናገራሉ።

እድሜያቸው ከ40 እስከ 60 መካከል ያሉ ሰዎች በየእለቱ ቢያንስ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ መጀመር አለባቸው ሲሉም ባለሙያዎቹ ምክራቸወን ይለግሳሉ።

በቀን ውስጥ በትንሹ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ ከፍተኛ የጤና ጥቅም ያስገኛል የሚሉት ባለሙያዎቹ፥ ያለ እድሜ የሚከሰት ሞትንም በ15 በመቶ እንደሚቀንስ ይናገራሉ።

ሆኖም ግን የጤና ባለሙያዎቹ ግምት እንደሚያሳየው ከሆነ እድሜያቸው ከ40 እስከ 60 መካከል ካሉ 10 ሰዎች የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ የሚያደርጉት ቢበዛ በወር አንዴ ነው።

ሰዎች በተቻላቸው አቅም ወደ ሱቅ ወይም ገበያ ሲሄዱ ተሽከርካሪ አሊያም ታክሲ ከመጠቀም ይልቅ እንደ ቦታው ቅርበት የእግር ጉዞ ቢያደርጉ መልካም ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።

እንዲሁም አብዛኛውን ስራቸውን ወንበር ላይ ቁጭ በማለት የሚሰሩ ሰዎችም በምሳ ሰዓታቸው አሊያም ከስራ ሲወጡ በትንሹ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ቢያደርጉ የሚያገኙት ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑም ተነግሯል።

ጥናቱ እድሜያቸው መካከለኛ የሚባሉት ላይ ያተኮረው፤ በተለይም ሰዎች እድሜያቸው ከ40 በሚያልፍበት ጊዜ የሚያደርጉት የአካላዊ እንቅስቃሴ መጠን በጣም ስለሚቀንስ ነው ተብሏል።

አንድ ሰው በሳምንት ውስጥ በአማካኝ የ150 ደቂቃ የአካል ብቃት መስራት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው መስፈርት ያመለክታል።

ሆኖም ግን እድሜያቸው ከ40 እስከ 60 መካከል ካሉት ሰዎች ውስጥ ግማሽ ያክሉ ይህንን ማሳካት እንደማይችሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 5 ሰዎች አንዱ ደግሞ በሳምንት ውስጥ ከ30 ደቂቃ ያነሰ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ይሰራል።

ምንም እንኳ በቀን ውስጥ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት ባያስችልም በሰዎች ጤና ላይ ግን ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።

በተለይም እንደ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ጭንቀት እና የመሳሰሉ ህመሞችን በመከላከሉ ረገድ የእግር ጉዞ ማድረግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው ባለሙያዎቹ የሚያነሱት።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement