የቡሄ በዓል…

                                                  buhe_1.jpg

በሙለታ መንገሻ

ቡሄመላው ሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን፥ በዓሉ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቶች አሉት።

በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታተቶች ዘንድ የደብረ ታቦር በዓል በሚል ነው በየዓመቱ ነሃሴ 13 የሚከበረው።

ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ላይ በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን የገለፀበት ዕለትን ለማስታወስ ነው የሚከበረው።

በዓሉ ባህላዊ ትውፊቶችም ያሉት ሲሆን፥ በዚህም ቡሄ በዓል የሚል መጠሪያ አለው።

ቡሄ ማለት መላጣ ወይም ገላጣ ማለት ሲሆን፥ በሀገራችን ክረምቱ ተገባዶ ብርሃን በሚታይበት ወቅት የሚከበር በዓል ስለሆነ ቡሄ የሚባል መጠሪያ እንደተሰጠው ይነገራል።

በቀደምት ጊዜያት የቡሄ በዓልን መዳረሻ ተከትሎ በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ፤ እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ እና ሲፈጩ ይሰነብታሉ።

በነሐሴ 13 ዋዜማ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ደጃፍ እጅብ ብለው የታሰሩት ችቦዎች የሚቀጣጠሉበት ቀንም ነው።

ችቦ የማቀጣጥሉን ሥርዓት የሚያዘጋጁትም ሆነ የሚመሩት እንደጨዋታው ልጆች ሳይሆኑ አዋቂዎች እና አባቶች ናቸው።

በቡሄ በዓል አከባባርም ከዋዜማው ጀምሮ ህፃናት በየቤቱ ደጃፍ “ቡሄ በሉ” እያሉ ግጥም እየደረደሩ በዜማ ይጨፍራሉ።

ቡሄ ጭፈራ በቡድን የሚጨፈር ሲሆን፥ እያንዳንዱ ቡድን የራሱ መሪ ይኖረዋል፣ ይሄ መሪ አውራጅ በመባል ይታወቃል።

አውራጁ ዋናው ዘፋኝ ነው፤ ግጥሞቹን በዜማ በማቀናጀት ያወርድላቸዋል፤ ጓደኞቹም በወግ ይቀበሉታል፣ ከልባቸው ላባቸው እስኪንጠፈጠፍ ያስነኩታል።

ሽልማታቸው ሙልሙል ዳቦ ነውና እሱን ሲያገኙ ምርቃት መርቀው ወደሚቀጥለው ቤት ያመራሉ።

ከቡሄ ጭፈራ ግጥም ውስጥ፦

ቡሄ በሉ፣ ልጆች ሁሉ

ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ

ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ…

በማለት በሚጨፍሩበት ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ ይሰጧቸውና እየገመጡ ጅራፋቸውን ሲያጮሁ ያመሻሉ።

የቡሄ በዓል አከባበር አሁን አሁን በከተሞች ባህላዊ ቀለሙን እየለቀቀ መምጣቱ የሚስተዋል ሲሆን፥ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ግን አሁንም ባህሉን ጠብቆ እንደሚከበር እሙን ነው።

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement