SPORT: የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ከ16 ወደ 24 እንዲያድግ ተወሰነ::

                                             

በዳዊት በጋሻው

 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 በካሜሩን ከሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥር እንዲጨምር ተወሰነ።

የአፍርካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሞሮኮ ባደረገው ስብሰባም የአፍሪካ ዋንጫ ከቀጣዩ ውድድር ጀምሮ በ24 ቡድኖች መካከል እንዲደረግ ወስኗል።

በመሆኑም ካሜሩን ከምታዘጋጀው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ 24 የአፍሪካ አገራት ቡድኖች በአንድ የውድድር መድረክ ተሳታፊ ይሆናሉ።

ይሁንና ለአዘጋጇ ካሜሩን ተጨማሪ የቤት ስራ ይሆንባታል እየተባለ ነው። ምክንያቱም ዝግጅት የምታደርገገው ቀድሞ ለታሰበው 16 ቡድኖች በመሆኑ።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ፥ በዓለም ዋንጫና በአህጉራዊ ውድድሮች የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ይጨምራል የሚል ቃል ገብተው ነበር።

በዚህም መሰረት የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ከ32 ወደ 48 እንዲያድግ ባለፈው ጥር ወር መወሰኑም የሚታወስ ነው።

ካፍ የተሳታፊ አገራትን ቁጥር እንዲጨምር ከመወሰኑም በላይ ውድድሩ የሚካሄድበትን ወቅትም እንዲቀየር ወስኗል።

በዚህም መሰረት ጥርና የካቲት ላይ ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ከ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ ሰኔና ሃምሌ ላይ ይካሄዳል።

ውድድሩ በክረምት ወራት መካሄዱ በተለይም ክለቦች ተጫዋቾቻው ለብሔራዊ ቡድኖቻቸው ጨዋታ ሲጠሩ ለመልቀቅ ለሚቸገሩ የአውሮፓ ክለቦች አስደሳች መሆኑ እየተነገረ ነው።

አስተያየታቸውን የሰጡ የአፍሪካ ተጫዋቾች ወኪሎች ውድድሩ በክረምት እንዲካሄድ መወሰኑ ትክክል መሆኑን አንስተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የካሜሩንን ዝግጅት በተመለከተ በቀጣዩ መስከረም ገምጋሚ ቡድን ይልካል ተብሏል።

የሀገሪቱ ስፖርት ሚኒስትር ካሜሩን ከደህንነትና ከጸጥታ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከፍትኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement