ጎግል የሞባይል ስልክ የመረጃ መፈለጊያ መተግበሪያውን አሻሻለ::

                                               

ጎግል የሞባይል ስልክ የመረጃ መፈለጊያ መተግበሪያው ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን አዳዲስ መረጃ በቀላሉ በሚያገኙበት መልኩ ማሻሻሉን ገልጿል፡፡

በማሻሻያውም በሞባይል ስልክ ውስጥ የሚገኘው የመፈለጊያ መተግበሪያ ስለ መዝናኛዎች፣ የጉዞ መረጃ፣ የስፖርት ሁነት እና ሌሎችንም ርዕሰ ጉዳዮችን ጠቋሚ ስርዓት አካቷል፡፡

በዚህም ከፌስቡክ የአዳዲስ የመረጃ መጠቆሚያ ስርዓት ጋር እንደሚፎካከር ነው ኩባንያው የገለጸው፡፡

ዛሬ በአሜሪካ ተግባራዊ የሆነው የመረጃ ማሳወቂያ የመፈለጊያ ስርዓት በቀጣይ ሳምንታት በሌሎችም ሀገራት ወደ ተግባር እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

አዲሱ ማሻሻያ “Google Feed,” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን ከፌስቡክ “News Feed,” ጋር እንዲመሳሰል እና በተግባርም ተቀራራቢ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ሆኖም የፌስቡክ ኩባንያን ፈጠራ ለመቅዳት ሳይሆን በጎግል መረጃ ለሚያፈላልጉ ሰዎች ስለሚፈልጉት ጉዳይ አዳዲስ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

የጎግል የምህንድስና ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ቤን ጎሜስ እንደተናገሩት፥ አዲሱ የመረጃ መጋቢ የማሻሻያ ስራ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ያማከለ ነው፡፡

በተለይም በአዲሱ ሞባይል ስልክ የመፈለጊያ ስርዓት ውስጥ ስለሚፈለገው ወቅታዊ መረጃ፣ ሁነቶች እና ሌሎችም ጉዳዮች ዋነኛውን የመረጃ ምንጭ የሚገኝበትን የድረ ገፅ ማስተሳሰሪያ ያካትታል፡

የምህድስና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጎግል በመረጃ የመፈለጊያ ስርዓቱ ላይ ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍ የቅርብ ጊዜ እቅድ የለውም ብለዋል፡፡

ጎግል ፊድ ተጠቃሚዎች የፈለጉትን የመረጃ ትውስታ፣ እንዲሁም ከሌሎች የጎግል መረቦች ማለትም በዩቲዩብ፣ በጂ ሜይል እና በጎግል ካሌንደር የሚመጡ አዳዲስ መረጃዎች መግባታቸውን ጥቆማ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ

Advertisement