ጡት የማጥባት ተግዳሮቶች

ጡት የማጥባት ተግዳሮቶች

 

ሦስቱን ልጆቻቸውን ጤናማና ጠንካራ በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው አሥር ሲሆን፣ ሁለተኛው ስድስት፣ ሦስተኛው ደግሞ አራት ዓመቱ ነው፡፡ ልጆቹ በሆነው ባልሆነው እየታመሙባቸው በየጤና ተቋማት ተመላልሰው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ያደረጉት የተለየ ነገር ኖሮ ወይም ሕፃናቱ በተፈጥሯቸው የተለየ ጥንካሬ ኖሯቸው ሳይሆን በሽታን የመከላከል አቅሙን ያዳበሩት እስከ ስድስት ወራቸው ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ ሳያቋርጡ በማጥባታቸው እንደሆነ እናታቸው ወ/ሮ እምነቴ ድልነሳው ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ እምነቴ በአንድ ግብረሠናይ ድርጅት ውስጥ ሠራተኛ ናቸው፡፡ ጡት ማጥባት ለእናትየው በተለይም ደግሞ ለሕፃናት ልዩ ጥቅም እንዳለውና ልጆቻቸውን እስከ ስድስት ወራት ድረስ በጡት ወተት ብቻ እንዲያቆዩ ትጎተጉታቸው የነበረችው እህታቸው እንደበረች ያስታውሳሉ፡፡ ጡት ብቻ በቂ ነው ብሎ ለማመን ጊዜ ቢወስድባቸውም፣ አለው ከተባለው ጥቅም አንፃር ሦስቱንም ልጆቻቸውን እስከ ስድስት ወር ድረስ ጡታቸውን ብቻ በማጥባታቸው ልጆቻቸው ጤናማ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡   

ይህንን ሲያደርጉ ግን ነገሮች አልጋባልጋ ሆነውላቸው አልነበረም፡፡ የስራ ፀባያቸው ልጅ ለማሳደግ የተመቸ አይደለም፡፡ ጡት ለማጥባት ደግሞ ስድስት ወራት ያስፈልጓቸው ነበር፡፡ የሚሰሩበት ድርጅት የሚሰጣቸው የወሊድ እረፍት ሕጉ በሚያዘው መሰረት ከወሊድ በፊት አንድ ወር፣ ከወሊድ በኋላ ደግሞ ሁለት ወር ነው፡፡ ስለዚህም በተገቢው መንገድ ልጃቸውን ጡት ለማጥባት ሌላ ተጨማሪ አራት ወራት ያስፈልጓቸው ነበር፡፡

‹‹የምሠራበት ድርጅት ጥሩ ነበር›› የሚሉት ወ/ሮ እምነቴ፣ ከቅርብ አለቃቸው ጋር በመነጋገር የዓመት ፈቃዳቸው እንዲመቻችላቸው አደረጉ፡፡ በቂ  ግን አልነበረም፡፡ በመሆኑም የእረፍት ጊዜያቸውን ጨርሰው  ወደ ሥራ ገበታቸው ከተመለሱ በኋላ ልጁ 6 ወር እስኪሞላው ድረስ በየቀኑ ምሳ ሰዓት ላይ ቤት ገብተው ልጃቸውን እንዲያጠቡ ሁኔታዎች ተመቻቹላቸው፡፡ ‹‹ስድስት ወራት ሙሉ በጡት ያድጋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል›› ያሉት ወይዘሮዋ፣ በእምነታቸው ፀንተው የመጀመርያ ልጃቸውን እስከ ስድስት ወሩ ድረስ በጡት ብቻ እንዲቆይ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

ከስራ እስኪመለሱ ድረስ ባለው ክፍተት ልጃቸው እንዳይራብ ጡታቸውን አልበው ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ ልምዳቸው ነበር፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ ከሚሰሩበት ቦታ ወደ ቤት መመላለሱም ሌላው አሰልቺና አድካሚ ነበር፡፡ ስድስት ወሩን እንዲህ ከቆዩ በኋላ ከተጨማሪ ምግብ ጎን ለጎን ሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስኪሞላው ድረስ ጡት ያጠቡት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

 ተከታይ ሁለቱን ልጆቻቸውንም በዚህ መልኩ አጥብተው ማሳደጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጥቅሙን ስላወቅኩኝ ነው የተጋሁት›› በማለት ልፋታቸው በልጆቻቸው ዕድገትና ጤና ላይ በመንፀባረቁ ደስተኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በእናት ጡት ወተት ብቻ ሕፃንን ለስድስት ወራት ማቆየት ይቻል ይሆን? የሚል ጥርጣሬ እንደነበራቸው በማስታወስም፣ ‹‹ሌላ ልምዷን የምታካፍለኝ እናት ብትኖር ኖሮ ቀላል ይሆንልኝ ነበር›› የሚሉት ወ/ሮ እምነቴ፣ ልምዳቸውን ለሌሎች እናቶች እንደሚያካፍሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጡቴ ወተት አላወጣ አለኝ፤›› በሚል ልጆቻቸውን ሌላ አማራጭ ምግብ የሚመግቡ እናቶችን በተመለከተ የእናት ጡት ወተት አንዷ ጠብታ ምን ያህል ዋጋ እንዳላት ቢያውቁ ጥርጣሬ አያድርባቸውም ነበር ይላሉ፡፡ ጡት የማጥባት ጥቅምን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጡበት የራሳቸው የፌስቡክ ገጽ ከፍተው መሥራት ከጀመሩም ቆይተዋል፡፡ መጽሐፍ ለማሳተምም ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን ይናገራሉ፡፡

የጡት ወተት የተለያዩ ፕሮቲኖች፣ ቫይታሚኖች፣ ስብና ካርቦሃይድሬቶች የሚይዝ በመሆኑ ለሕፃኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለሕፃኑ ጤንነት፣ አካላዊና አእምሯዊ እድገትም ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ በተገቢው መጠን የእናት ጡት ወተት ያገኘ ሕፃን  ለስኳር፣ ለአስም በሽታና ከመጠን ላለፈ ውፍረት የመጋለጥ ዕድሉ ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ጡት ማጥባት ለእናትየውም ጭምር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከወሊድ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ደም የመፍሰስና ሌሎችም ችግሮች በፍጥነት እንዲቆም ያደርጋል፡፡ የጡትና የማሕፀን ካንሰርንም እንደሚከላከል ይነገራል፡፡ ከልክ ያለፈ ውፍረት እንዳይከሰት እንደሚረዳም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ህፃኑ ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የእናቱን ጡት ብቻ እንዲጠባ ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ይሁንና አግባብነት ያለው ጡት የማጥባት ባህል ምን ያል ተለምዷል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ ህፃኑ ሲወለድ ጀምሮ ጡጦ እንዲጠባ የሚያደርጉ ወላጆች ያጋጥማሉ፡፡ ወተት በውኃ እየበረዙ፣ ተልባ እየቀቀሉ ማጠጣትም የተለመደ ነው፡፡ ሕፃናትን ለመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት በጡት ብቻ ማኖር እንደሚቻል ማሳመኑም ከባድ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት ስር ሚገኘው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበር ጤና ፎረም በጡት ማጥባት ዙሪያ የግማሽ ቀን ዓውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

በዕለቱ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ የተጋበዙት ወ/ሮ እምነቴ፣ አብዛኛዎቹ እናቶች ለጡት ማጥባት ያላቸው አመለካከት የተዛባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጡት ማጥባትን፣ ያጣችና ያልሠለጠነች ሴት የምታደርገው እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ እናቶች መኖራቸውን በመጥቀስም የአስተሳሰብ ችግር መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ማንኛውም ሕፃን በተወለደ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ቢጠባ፣ ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራትም በእናት ጡት ወተት ብቻ እንዲቆይ ቢደረግ፣ እስከ ሁለት ዓመቱ ደግሞ ከሌሎች ምግቦች ጎን ለጎን ጡት ቢጠባ፣ በየዓመቱ የ800,000 ሕፃናትን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2015 ያወጣው ጥናት ያሳያል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለስድስት ወራት ያህል የእናት ጡት ብቻ ጠብተው የሚያድጉ ሕፃናት ከ40 በመቶ ያልበለጡ መሆናቸውን የድርጅቱ ጥናት ያሳያል፡፡

በዕለቱ የተገኙት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥርዓተ ምግብ አስተባባሪው አቶ ቢራራ መለሰ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፣ 30 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በአመጋገብ ችግሮች ተጠቂ ነው፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2035 ወደ 50 በመቶ ከፍ ይላል፡፡ 7 ቢሊዮን ከሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች መካከል ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይጠቃሉ፡፡ አምስት ቢሊዮን ከሚሆኑ አዋቂዎት መካከልም ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑት ከአመጋገብ ችግር ጋር በተያያዘ ከመጠን ባለፈ ውፍረት ይጠቃሉ፡፡

 በአሁኑ ወቅት ትልቁ የጤና ሥጋትም ከአመጋገብ ችግር ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎች መሆናቸውን አቶ ቢራራ ይናገራሉ፡፡ በቂ ምግብ ባለማግኘትና በረሀብ  ምክንያት ከ1.4 እስከ 2.1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚሆን የዓለም ዓመታዊ የምርት ፍጆታ እንደሚጠፋ፣ በአገሪቱ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2009 አገሪቱ በረሃብ ምክንያት 55.5 ቢሊዮን ብር ወይም 16.5 ከመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የምርት ፍጆታ ማጣቷን አቶ ቢራራ ያቀረቡት ጥናት ያሳያል፡፡

ባለው የሥርዓተ ምግብ ችግር እ.ኤ.አ. በ2016፣ 67 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች እድገት እንዲቀጭጭ ሆኗል፡፡ በጥናቱ መሰረት፣ ከአምስት ዓመት እድሜ በታች በሆኑ ህፃናት የመቀንጨር ችግር በስፋት የሚታየው በአማራ ክልል ነው፡፡ በክልሉ የመቀንጨር ችግር 46.3 በመቶ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 42.7 በመቶ፣ በአፋር ክልል 41.1 በመቶ ችግሩ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የተሻሉ የተባሉት አዲስ አበባ 14.6 በመቶና ጋምቤላ ክልል 23.5 በመቶ መሆኑን ከጥናቱ መረዳት ተችሏል፡፡

ይህንን አገራዊ ችግር በ2022 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግም ለሕፃናቱ ዕድገት ትልቁን ድርሻ በሚይዙት በመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ውስጥ ብዙ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት ሕፃኑ ከተረገዘ ወይም ከተረገዘችበት ጊዜ እስከ ሁለት ዓመቷ ወይም ዓመቱ ድረስ ባሉት ቀናት የሚደረግ እንክብካቤ ነው፡፡ ይህም የሆነው በሕፃናት አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ላይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ትልቁን ሚና ስለሚጫወቱ ነው፡፡

ሕፃናቱ ከተወለዱበት ቅፅበት አንስቶ ስድስት ወር እስኪሞላቸው ድረስ በእናት ጡት ብቻ እንዲቆዩ ማድረግም ጤናማ ለሆነ የሕፃናቱ ዕድገት ቁልፍ ነው፡፡ 96 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን እናቶች ልጆቻቸውን ጡት የማጥባት ባህል ቢኖራቸውም፣ አግባብነት ባለው መንገድ የሚያጠቡት ግን ከ58 በመቶ ያልበለጡ እንደሆኑ አቶ ቢራራ ይናገራሉ፡፡ ይህም በብዙ ልፋት የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነፃፀርም ትልቅ መሻሻል ማሳየቱን አክለዋል፡፡

ለዚህም የግንዛቤ ችግር፣ በተቃራኒው ደግሞ ግንዛቤ ኖሯቸው ነገር ግን ከሥራ ጋር የማይመቻቸው ቢሮ የሚውሉ ሰራተኛ እናቶች ጉዳይ በዋናነት ይነሳሉ፡፡ ለአንዲት እናት ከመውለዷ በፊት አንድ ወር እንዲሁም ከወለደች በኋላ የሚሰጣት የሁለት ወራት የወሊድ ዕርፍት፣ ስድስት ወር ጡት ማጥባት ከሚለው መርህ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ወ/ሮ እምነቴ ያሉ መስሪያ ቤታቸው የሚተባበራቸው ለልጃቸው የሚጠበቅባቸውን ሲያደርጉ ይህ የማይሳካላቸውም አሉ፡፡

ከእነዚህ እናቶች መካከል የሥርዓተ ፆታ ባለሙያዋ ወ/ሮ ሰብለ ዳንኤል ይገኙበታል፡፡ ለአሥር ዓመታት ያህል በአንድ ግብረ ሠናይ ድርጅት በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ በማሪስቶፕ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ተቀጥረው መሥራት ከጀመሩ ገና ወራቸው ነው፡፡ አንድ ዓመት ከአሥር ወራት ዕድሜ ያላትን ልጃቸውን ሲወልዱ ጡት ለማጥባት በቂ ጊዜ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ልጃቸውን የወለዱት ጊዜዋ ሳይደርስ እንደሆነ ይነገራሉ፡፡ ይሠሩበት የነበረው ድርጅት ሕጉ በሚያዘው መሠረት ከመውለዳቸው በፊት አንድ ወር ከወለዱ በኋላ ደግሞ የሁለት ወራት የዕረፍት ጊዜ እንደሚሰጣቸው ያውቃሉ፡፡ በዚህ መሠረትም ከመውለዳቸው አስቀድሞ ያለውን የአንድ ወር ዕረፍት ለመጠቀም ከአለቃቸው ጋር በመነጋገር ላይ ሳሉ በድንገት ሕፃኗ አለጊዜዋ እንድትወለድ የሚያስገድዳቸው አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

‹‹ዘጠኝ ወር ገና አልሞላትም፡፡ ልዩ ክትትል ያስፈልጋት ነበር፡፡ ሁለት ወር ዕረፍቴን ጨርሼ ከወሊድ በፊት የነበረውን አንድ ወር ታሳቢ አድርገው ዕረፍት እንዲጨምሩልኝ ጠየኳቸው፡፡ ነገር ግን ‹‹ተቃጥሏል አይቻልም አሉኝ፡፡ የዓመት ፈቃድ ካለሽ እሱን ተጠቀሚ አለዚያ ግን ዕረፍት ያለ ክፍያ መውጣት ትችያለሽ፤›› አሉኝ፣ በማለት ለጉዳዩ የተሻለ ቅርበት እንዳላቸው የሚታመኑ ድርጅቶች እንኳን የወሊድ ፈቃድን በተመለከተ ተነጋግሮና ተግባብቶ ለመሥራት ፈቃደኛ የማይሆኑባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

51 በመቶ የሚሆኑት የዓለም አገሮች ለሴት ሠራተኞች ቢያንስ የ14 ሳምንት የወሊድ ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት አገሮች 18 ሳምንታትና ከዚያ በላይ የወሊድ ፈቃድ ይሰጣሉ፣ 35 በመቶ የሚሆኑ አገሮች ከ12 እስከ 13 ሳምንት፣ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ12 ሳምንታት ያነሰ የዓመት ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ የሚሰጡት የዕረፍት ጊዜ ከአገር አገር እንደሚለያየው ሁሉ እናቶቹ በወሊድ ፈቃድ ላይ ሳሉ የሚከፈላቸው ወርሃዊ ክፍያ ምጣኔም የተለያዩ ናቸው፡፡

በአለም ረጅሙን የወሊድ ፈቃድ በመስጠ የምትታወቀው ጀርመን አንዲት እናት ስትወልድ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ዕረፍት ከ65 በመቶ ወርሃዊ ደመወዝ ጋር እንዲሰጣት የአገሪቱ ህግ ያዛል፡፡ ጣልያን አምስት ወራት ከ80 በመቶ የወር ደመወዝ ጋር፣ ቼክ ሪፐብሊክ 28 ሳምንታት ከ60 በመቶ ክፍያ ጋር ነው፡፡ በአፍሪካ በሶማሊያ 14 ሳምንት ከ50 በመቶ ክፍያ ጋር፣ በስዋዚላንድ አለምንም ክፍያ 12 ሳምንት ዕረፍት እንደሚሰጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ አንዲት እናት ምን ያህል ጊዜ የወሊድ ፈቃድ መውሰድ እንዳለባትና የወሊድ ፈቃድ መውሰድ የምትችለውም በድርጅቱ ለተወሰነ ጊዜ ከሰራች በኋላ ነው የሚል ሕግ ያላቸው አንዳንድ አገሮችም አሉ፡፡

የኢትዮጵያ የወሊድ ፈቃድ ሕግ ከብዙዎቹ አገሮች የተሻለ እንደሆነ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ደጀኔ ግርማ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/2003 እና የፌዴራል ሲቪል ሠርቫንት አዋጅ ቁጥር 515/2007 የወሊድ ፈቃድን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጧቸው ድንጋጌዎች አሉ፡፡

አዋጆቹ በአንድ ደርጅት ተቀጥራ የምትሰራ አንዲት እናት ስትወልድ የምትሰራበት ድርጅት አንድ ወር የቅድመ ወሊድና ሁለት ወር ከወሊድ በኋላ እረፍት ከሙሉ ደመወዝ ጋር ክፍያ እንዲፈፀምላት ያስገድዳሉ፡፡ ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረ የቅድመ ወሊድ ዕረፍት በሚኖርበት አጋጣሚም፣ ከወሊድ በኋላ ጨምሮ መጠቀም እንደሚቻልም የሚደነግግ በሲቪል ሠርቫንት አዋጁ የተካተተ አንቀፅ አለ፡፡

ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያቅማሙ ድርጅቶች መኖራቸውን ከወይዘሮ ሰብለ ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ መብት (ከመውለድ በፊት ያለው አንድ ወር ከወሊድ በኋላ መታሰብ እንደሚችል) እንዳላቸው የሚያውቁም እምብዛም አይደሉም፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች አንድ ሕፃን አለተጨማሪ ምግብ ለስድስት ወራት ጡት መጥባት አለበት የሚለውን መርህ ከዳር ለማድረስ እያዳገቱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ጤናማና ብሩህ አእምሮ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ጡት ማጥባት ግድ ነውና ‹‹አንዲት እናት ስትወልድ አንድ ወር የቅድመ ወሊድና ስድስት ወር ከወሊድ በኋላ ፈቃድ ሊሰጣት ይገባል›› ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡

እሳቸው ይህንን ቢሉም የእረፍት ጊዜው እንዲጨምር ማድረጉ ሌላ አደጋ ያስከትላል በሚል የሚከራከሩ አሉ፡፡ አሠሪዎች ሴትን ለመቅጠር ያላቸው ፍላጎት ይቀንሳል፣ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሥራ ሥምሪቱ ለወንዶች ብቻ እንዲያደላ ያደርጋሉ በማለት ሌላ አማራጭ በተለይም በሥራ ቦታዎች ለሕፃናቱ የሚሆን ማቆያ ማዘጋጀትና ከእናትየው እንዳይርቅ ማድረግ የተሻለ መሆኑን አንዳንድ የዐውደርዕዩ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችን ተሞክሮም በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ደጀኔ በበኩላቸው፣ ከተነሱት አማራጮች በተጨማሪ ለወሊድ የሚሠጠውን የዕረፍት ጊዜ መጨመር የቀጣሪ ድርጅቶችን የመክፈል አቅም እንዳይፈታተነው ‹‹የተወሰነውን የደመወዝ መጠን ድርጅቱ፣ ሌላውን ደግሞ ሶሻል ሴኩዩሪቲ ኤጀንቶች የሚከፍሉበት አሠራር ቢዘረጋ ጥሩ ነው፡፡ በሌላው ዓለምም የተለመደ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

 

Advertisement