ቡና በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ትልልቅ ጥናቶች እያመለከቱ ነው።
የአውሮፓ እና የአሜሪካ ተመራማሪዎች በጋራ ሆነን አጥንተናል ባሉት ምርምር ደግሞ፥ ቡና ቶሎ የመሞት እድልን እንደሚቀንስ የሚያሳይ ማስረጃ አግኝተናል ብለዋል።
የአውሮፓ ተመራማሪዎች ከ10 የአውሮፓ ሀገራት የተወጣጡ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ላይ ባካሄዱት ጥናት፥ በቀን ውስጥ በትንሹ ሶስት ሲኒ ቡና የሚጠጡ ወንዶች ቶሎ የመሞት እድላቸው በ18 በመቶ የቀነሰ መሆኑን የሚሳይ ውጤት አቅርበዋል።
ሴቶች ቡና ከመጠጣት የሚያገኙት ጥቅም የወንዶቹን ያክል ባይሆንም እንኳ፥ በቀን ውስጥ ሶስት ሲኒ ቡና የሚጠጡ ሴቶች ቶሎ የመሞት እድልም በ8 በመቶ የቀነሰ መሆኑን ተመራማሪዎቹ አስቀምጠዋል።
የአሜሪካ ተመራማሪዎችም የተለያዩ የዘር ግንድ ያላቸው 185 ሺህ ሰዎች ላይ አደረግን ባሉት ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ተመራማሪዎቹ አገኘን ያሉት የጥናት ውጤትም በቀን ውስጥ በአማካኝ ከሁለት እስከ ሶስት ሲኒ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ቶሎ የመሞት እድላቸው በ18 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል።
ቡና ረጅም እድሜን እንድንኖር የሚረዳን በውስጡ ባለው ካፌይን ይቅል በውስጡ በያዘው አንቲ ኦክሲዳንት ንጥረ ነገር አማካኝነት ነው በማለት ጥናቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች ያምናሉ።
የአውሮፓ ተመራማሪዎችን ቡድን የመሩት የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ዶክተር ማርክ ገንተር፥ “በጥናታችን ቡናን አብዝቶ መጠጣት በተለያዩ የህመም አይነቶች ቶሎ የመሞት እድለን እንደሚቀነስ ለይተናል” ብለዋል።
ጥናቱን ባካሄድንባቸው 10 የአውሮፓ ሀገራት ያገኘነው ውጤት ተመሳሳይ ነው ያሉት ዶክተር ማርክ ገንበር፥ “ጥናቱም ቡና ለሰው ልጅ ጤና ያለውን ጠቀሜታ ያሳየ ነው” ብለዋል።
የአሜሪካ ተመራማሪዎችን ቡድን የመሩት የደቡብ ካሎፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ቬሮኒካ ስቴይዋን፥ “ቡና መጠጣት ህይወትን ያረዝማል ብለን መደምደም አንችልም፤ ነገር ግን ቡና በመጠጣት እና ረጅም እድሜ መኖር ግንኙነት እንዳላቸው ለይተናል” ብለዋል።
ዶክተር ቬሮኒካ፥ “ቡና በውስጡ በርካታ አንቲ ኦክሲዳንት እና ፌኖሊክ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ ነው፤ ይህ ደግሞ ካንሰርን ለመካለክል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶች ቡናን አዘውትሮ መጠጣት የልብ ህመም፣ የስኳር በሽታ፣ የጉበት እና የተወሰኑ የካንሰር አይነቶች ተጋላጭነተን እንደሚቀንስ ያሳያሉ።
ቡና በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው ሲሆን፥ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በቀን ውስጥ በዓለም ዙሪያ 2 ነጥብ 25 ቢሊየን ሲኒ ቡና ይጠጣል።
ምንጭ፦ www.huffingtonpost.co.uk