በውቀቱ ስዩም-ሲያትል በተደረገው የዲያስፖራ የግርኳስ ውድድር አስመልክቶ የከተባት ወግ

በውቀቱ ስዩም

©2017

To be honest with you ሲያትል በተደረገው የዲያስፖራ የግርኳስ ውድድር ወደ ሚደረበት ስቴዲየም የሄድኩት ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሳልነካካ መፅሃፌን ሸጬ አገሬ ለመግባት ነበር፤

(ከመፅሃፍ ሻጭ የሚገኘው ገቢ አስር በመቶ ለእኔ ሲሆን ፤ ቀሪው ለቤት አከራየ ለጋሽ ጣሰው መጦርያ ይሆናል)

እና እዚያ ስደርስ፡ ከመላው አሜሪካ የመጣ ህዝበ -ዲያስፖራ ወደ ስቴድየሙ በር ይንቆረቆራል፤

የስደት ወዳጁን ለማግኘት የመጣ! ያበሻ ፊት ናፍቆት የመጣ! የነገስታት ፊት የታተመበት ካናቴራ ሊቸበችብ የመጣ! የመጨረሻ የጠበሳ ሙከራ ለማድረግ የመጣ! የእግኳስ ፍቅር ነድቶት የመጣ::ዝምብሎ መሄጂያ አጥቶ የመጣ:: በየፍላጎቱ ተመርቶ የመጣ ያገርሰው -ስቴድየሙን ወረሰው::

ከሜዳው ራስጌ ላይ ባለው ስፍራ ላይ የሸቀጥ መሸጫ ድንኳኖች ተደርድረዋል፡፡

አንዱ ድንኳን አጠገብ ሄጄ ቆምኩ፡፡ ወደ ድንኳኑ በር ስመለከት”የኢሳት ቲሌቭዥን ጊዚያዊ ጣቢያ “የሚል ፅሁፍ ጋር ተገጣጠምሁ:: ፈጠን ብየ ስልታዊ ማፈግፈግ አረግሁ:: አፈግፍጌ የተጠለልኩበትን ድንኳን ቀና ብየ ሾፍ ሳረግ” ኢህአፓ” የሚል ተፅፎበታል:: አጥብቄ ሮጥሁ :: በመስኩ ላይ እንደቄጤማ የተነሰነሰ” ቦይኮት ጎሳየ ተስፋየ” የሚል ማሳደሚያ ፖስተር እየደቀደቅሁ ሮጥሁ:: ግን ብዙ አልሮጥኩም:: የብሬ ነጋ መልክ የታተመበት ቲሸርት የለበሰ ወጣት ጋር ተላተምኩ:: ወጣቱ ማጅር ግንዴን ይዞ ሰልፊ ሊነሳ ሲጥር አምልጨው ሸሸሁ:: በዚህ አይነት ሳፈገፍግ ከስቴድየሙ ልወጣ ትንሽ ነበር የቀረኝ::

በመጨረሻ “በውቄ ከፈለግህ ይህን ጠረጴዛ መጠቀም ትችላለህ” የሚል ድምፅ ሰማሁ፤

ዞር ስል የፌስቡክ ባለንጀራየ አዲስ ናት:: ከባለቤቷ ጋር ሆነው አንድ ጠረጴዛ አዋሱኝ:: ጠረጴዛው ላይ መፃህፎቼን ዘርግቼ ሸማች መጠባበቅ ጀመርሁ::

ብጠብቅ ብጠብቅ ብጠብቅ መጣፌን አደለም የሚገዛ ዞር ብሎ የሚያይ የለም::

ፒፕሉ ተጉዳይ ሳይጥፈኝ ተፊትለፊቴ እየተጋፋ ይነጉዳል:: በጋ ስለሆነ ወንዱም ሴቱም ባለቁምጣ ነው:: ለምን እንደሆን እንጃ ከሰሜ ባላገሩ በቀር ቁምጣ የሚያምርበት ያበሻ ወንድ ገጥሞኝ አያውቅም:: ሰሜ ባላገሩ ያን የመሰለ አርበ -ሰፊ ቅልጥም ይዞ ለምን ለብሄራዊ ቡድናችን እንደማይጫወት አይገባኝም:: ያብዛኞቻችን እግር በቁምጣ ማሃል ሲታይ የመፈክር እጀታ ይመስላል:: ቁምጣን ሴቶቻችን ይታጠቋት!! የተልባ ማሻው ሚካየል ያለህ! ያንዲቱ እግር ላይ አይኔን ተክየ ያለሁበትን ረሳሁ:: የድሃ አገር ተወላጅ መሆኔን ረሳሁ:: ከነጋ አንዲት መፃፍ እንኳን አለመሸጤን ረሳሁ:: ልጂቱ ይባስ ብሎ በታፋዋ ላይ የይሁዳ አንበሳን ተነቅሳዋለች:: ተራማጁ ሰውየ በሰኮንድ የድሮ ናፋቂ ሆንሁ:: ወያኔ ነፍስህ አይማርም! ስንት መንደፍያ እግር በቸርቺል ጎዳና እየተርመሰመሰ አሁን ይህን የመሰለ ታፋ መሰደድ ነበረበት?

ዞር ስል አንድ ጎረምሳ ሚጢጢ ባንዲራ በሁለት ሁለት ዶላር ሲቸበችብ ሾፍኩት:: ግዞተኛው እየተጋፋ ይሸምታል::

ባንዲራ ሻጩ በግራ እጁ የኪሱን ተርዚና በዶላር እየወጠረ በቀኝ እጁ በያዘው ማይክ ” እንዲህ ነው ኢትጵያዊነት !” እያለ ያሟሙቃል::

ከሁለት ሰአት ጥበቃ በኃላ አንዱ መጥቶ መፅሀፍ ገዛኝ:: ማመን አቃተኝ::

እጄን ትከሻው ላይ ጭኘ እንዲህ ስል መረቅሁት::

“እጅህን ከቁርጥማት -ጉሮሮህን ከቢራ ጥማት ይሰውረው:: ከይሉኝታ ቢስ ቀፋይ- ጠላ ጋብዞ ውስኪ ከሚያስከፍል ግብር አስከፋይ -ይሰውርህ!

ደስታህ ፍፃሜ አይኑረው:: ሞትህን ያስቀረው:: ካልሆነ አሟሟትህን ያሳምረው- እግርህን በቀይ ምንጣፍ ላይ ያውለው- ስንቅህን ያክብደው እዳህን ያቅለለው- አለባበስህን ፋሺን-ኪስህን ATM ማሺን ያርግልህ-ምቀኛህን ለዘብጥያ ይዳርግልህ..

ጠላቶችህ እንደባዘቶ ይዳመጡ-ሽንት ቤት ሲቀመጡ-ይበርታባቸው ምጡ-“

በመጨረሻ ያትላንታው ወዳጄ ፊደል -ኮስታሮ ከፊቴ መጥቶ ተገተረ::

“ይሄ ነገር ተዝፍዝፎ ቀረ እንዴ?” አለኝ ወደ መፃፌ ባገጩ እየጠቆመ::

እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል ?! በሚል አይነት እጄን ዘረጋሁ::

“ለመጣፍ ሽያጭ ማስታወቂያ ወሳኝ ነው!! አሁን ተመልከት እንዴት እንደምቀውጠው!” አለና ከመፃፌ መካከል ሁለት አንስቶ ያዘ:: ከዚያ በቀኝ እጁ ይዞት የነበረውን ጥሩንባ አውጥቶ ድብልቅልቅ አድርጎ ነፍቶ ” እንዳያመልጣችሁ” ብሎ ጮኸ::

የጥሩባውን ልፈፋ ተከትሎ ብዙ አጃቢ ከበበን:: ከከባቢዎች አንዱ ጠጋ አለና እንዲህ አለ::

“ነፍሴ! እሱን ጥሩንባ ስንት ትሸጥልኛለህ?”

 

Advertisement