ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም እና ለመምራት የሚያስችሉ ነጥቦች – How To Manage Your Time Efficiently

                                             

ጊዜዎን እንዴት እና በምን መልኩ መጠቀም እንዳለብዎት አስበው ያውቃሉ?

በጣም የተጨናነቀ እና የተጣበበ ጊዜ ኖሮዎት የቱን ላስቀድም፣ እንዴትና በምን መልኩ ስራውን ላቃል በሚል ጥያቄም ራስዎን ያስጨንቁ ይሆናል።

ቢሆንም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ምናልባት ሳምንቱን ሙሉ ሌትም ሆነ ቀን በስራ ሊጠመዱ ይችላሉ።

ምናልባት አብስሎ ከመመገብ የደረሰ ነገር ገዝቶ መመገብና የመሳሰሉትን አማራጮች ይከተሉም ይሆናል።

እንዲህ ያለ የተጨናነቀ ነገር ሲያጋጥም ከመጣደፍ እና ከመጨነቅ ቆም ብሎ ማሰብ መልካም ስለመሆኑ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የመጀመሪያው ነገር ሁኔታውን መቆጣጠር መቻል ነው፤ ይህን ሲያደርጉ የተሻለውን መከወን ይችላሉ።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ደግሞ ጊዜዎን በአግባቡ ለመጠቀም እና ለመምራት የሚያስችሉ ነጥቦች ናቸው፤

ቅድሚያ የሚሰጠውን መለየትና ማቀድ፦ ሁልጊዜም ቢሆን መነሻዎ የህይዎቴ ግብ ብለው ያስቀመጡት ነገር ነውና ከየት ጀምረው እንዴት መሄድ እንዳለብዎት በዝርዝር ያስቀምጡ።

ግብ ብለው ካስቀመጡት መካከልም አስፈላጊ እና ወሳኝ የሚሉትን ይለዩ፤ የፍቅር ግንኙነት መጀመር፣ ስራ ላይ ማተኮርና ውጤታማ መሆን ብቻ፣ ቤተሰብን መርዳትና ማገዝ፣

ተሯሩጦ በመስራት ገንዘብ መያዝ ወይስ በሁሉም አቅጣጫ ተመጣጣኝ የሆነ ህይዎት መምራት።

በዚህ ደረጃ ግብዎን በዝርዝር ከለዩና መቅደም ያለበትን ካስቀደሙ በእቅድዎ መሰረት ህይዎትን መምራትና ማሳካት ይችላሉ።

በሚሰሩት ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን፦ አደርገዋለሁ ብለው የጀመሩት ነገር ከባድ እና አስቸጋሪ እንደሆነ ካሰቡ ብዙም ሳይሄዱ ሊሰናከሉ ይችላሉ።

በመሰል ሃሳቦች ተጠምዶ ነገሮችን ለመከወን መሯራጥ ትርፉ ድካም ስለሆነ አደርገዋለሁን ብቻ ይዘው እቅድዎን ወይም ስራዎን ይጀምሩ።

ይህ ሲሆን በማመንታት የሚያጠፉትን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ግብዎን መድረስ ይችላሉ።

የሚያውኩ ነገሮችን መቀነስ፦ ስራዎን እየሰሩና ያሰቡትን ለማሳከት ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት ከስራዎ የሚያስተጓጉሉ እና የሚያውኩ ነገሮችን መቀነስና ማስወገድንም አይርሱ።

ምናልባት ቤት ውስጥ የሚሰሩ ከሆነ ጎረቤትዎ አልያም ልጆችዎ ባሰቡት ሰዓት ስራዎን እንዳይሰሩ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ስለዚህም ቤት ውስጥ የመስራት ግዴታ ወስጥ ከገቡ ልጆች እርስዎን ሳይሆን ጨዋታን በሚፈለጉበት ሰዓትና የእርስዎን ስራ በማያውኩበት ወቅት ቢሆን ይመረጣል።

እነርሱን ደስተኛ የሚሆኑበትና የእርሰዎን አብሮ መሆን የማይፈልጉበት መንገድ ካለ ያንን አጋጣሚ በመጠቀም ስራዎን መከወን።

ቢሮ ውስጥ ከሆኑም ቢሮዎን ዘግተው መስራት፤ ይህን ሲያደርጉ የስራ ባልደረቦችዎ በአካባቢው በሚኖራቸው እንቅስቃሴ ትኩረትዎን አያጡም።

አስቸኳይ ስራ ከሆነ ሞባይልዎን ማጥፋት፣ ኢንተርኔት አለመክፈትና ስራዎ ላይ ብቻ ማተኮርን ይልመዱ።

እነዚህ መንገዶች በስራ ላይ እያሉ የሚያውኩ ነገሮችን በመቀነስ ጊዜዎን በአግባቡ ይጠቀሙ ዘንድ ይረዱዎታል።

ከህይዎትዎ ጋር የማይገናኙ ተጨማሪ ነገሮችን እቅድዎ ላይ አለመጨመር

ብዙዎቹ ሰዎኛ ባህሪ ሆኖ በአቅራቢያ ያሉ ሰዎች “ይህን ነገር አግዘኝ” ሲሉ፥ አልችለም ከማለት ይልቅ እሺ ማለትን ይመርጣሉ።

እሺታዎ መልካም ቢሆንም ግን የእርስዎን ጊዜ ከመጠቀም አንጻር እና ከግብዎ ባሰቡት ጊዜ እንዳይደርሱ በማድረግ በኩል የራሱ ተፅዕኖ አለው።

ከዚያ ይልቅ የእኔ በሚሏቸው ጉዳዮችና እቅዶች ላይ አተኩሮ መስራትን ይምረጡ፥ የእርስዎ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ተነሳሽነት ወስዶ መስራት የሚጨምረው ነገር እንደሌለም ያስቡ።

(ይህ ሃሳብ ግን በማህበራዊ ህይዎት ውስጥ በሚኖር መስተጋብር ከወዳጅ የሚመጡ ጥያቄዎችን የሚያካትት አለመሆኑን ባለሙያዎቹ ያሰምሩበታል።)

የእርሰዎ ትልቅ እቅድ እያለዎት የሆነ ነገር በተጨማሪነት እንዲሰሩ ሲጠየቁም፥ በቅድሚያ የጉዳዩን ክብደትና አስፈላጊነት ይመዝኑ።

ጉዳዩ ከትዳር ህይዎትዎና ከልጆችዎ ጋር፣ ከቤተሰብ እና ጎረቤትዎ ጋር እንዲሁም በህይዎትዎ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ከሆነ ምናልባት ጊዜ ሰውተው እንደሚሰሩት በማሰብ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን እቅድዎን በጊዜ ሳይከውኑ ማግኘት የሚገባዎን የራስዎንና የቤተሰብን ጊዜም ያጣሉና በሚመለከትዎት ላይ ብቻ ያተኩሩ።

ስራዎችን ለሌላ ጊዜ አለማስተላለፍ፦ በጣም ሰፊ ጊዜ እንዳለዎት በማሰብ “ይህን ስራ” ሌላ ጊዜ ብከውነው መልካም ነው በሚል እሳቤ ስራን ለሌላ ጊዜ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

በድካም፣ ወይም ጥሩ ስራ መስራት አልችልም በሚል ሰበብ አልያም ስራውን መስራት ስላልፈለጉና ምቾት ስለማይሰማዎት እንደዛ ሊወስኑ ይችላሉ።

ዛሬ መስራቱ የማያስደስት እና አድካሚ ነው ብለው ከማሰብ እርስዎ በመስራትዎ ለህይዎትዎና ለቤተሰብዎ ያለውን ጠቀሜታ ይመልከቱ።

ልብስ ማጠብ አሰልች እንደሆነ ቢያስቡም በጊዜ ሰሌዳ በመመራት ልምድና ስራውን ቀላል ማድረግ ይችላሉ።

ምናልባት ግን በጣም አንገብጋቢ ያልሆኑ ጉዳዮችን ልከውን አልከውን ከሚሉ የተዘነጋ ትልቅ ጉዳይ ካለ ትኩረትዎን አድርገው ወደዚያ መሰማራትንም ይልመዱ።

ከዚህ ባለፈ በጣም ደክሞኛል ብለው የሚያስቡ ከሆነም አረፍ ብለው ራስዎን የሚያነቃቁባቸውን መንገዶች በመጠቀም ወደ ስራ መግባት።

ዛሬ የማልሰራው ስራየ ይበላሻል አልያም ጥሩ ስራ መስራት ስለማልችል ብለው ካሰቡ ደግሞ፥ እስኪ ሃሳብዎን ይመዝኑት እና ወደ ተግባር ይግቡ።

ስራ ላይ ብሰማራ ስራው ይበላሻል የሚለው እሳቤ ምናልባትም የእርስዎ በራስ መተማመን ስሜት መውረዱን ማሳያ እንጅ እውነታ ሊሆን አይችልም።

ያ ከሆነ ደግሞ ሁልጊዜም ቢሆን እችላላሁ ይበሉና ወደ ስራ ይግቡ፥ የክህሎት ችግር ከሆነ ደግሞ ከሰው መጠየቅና መማርንም ይልመዱ።

ዘወትር ጊዜ የለኝም ብለው የሚያስቡ ከሆነ ራስዎን መቆጣጠርና ወደ እውነታው በመምጣት አቅዶ መንቀሳቀስ የሚበጀው እርምጃ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።

በዚህ ልክ ከሰሩ ትልቅ ስኬት፣ ጊዜዎን በመጠቀምዎም ጭንቀትን ያስወግዳሉ ከዚህ ባለፈም ለአዕምሮዎ ሰላምን ይሰጡታል።

ምንጭ፦ psychologytoday.com

Advertisement