ቢንቢዎች የሚነክሱን ለምንድነው? በጣም የሚሳክከንስ? መፍትሔ አለው?

                                            

የዝናብ ጊዜን ተከትሎ ቢንቢዎች በብዛት ይፈላሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ ቢንቢዎች ሲነክሱን ቆዳችን ላይ አለርጂክ ይገጥመናል፤ ቆዳ ላይ የመቅላትና የማበጥ ሁኔታም ይከሰታል፤ ነገር ግን የማበጥና የመቅላት ሁኔታን ብዙውን ጊዜ ችግር የማይፈጥርና የምንቋቋመው ነው፤ ይሁን እንጂ በቀጣይ የሚከሰተው የማሳከክ ሁኔታ ግን እረፍት የሚነሳ ነው፤ ከቢንቢዎች

ንክሻ በኋላ በጣም የሚያሳክከን ለምንድነው?
ቢንቢዎች የሚነክሱን ልክ እንደ ንብ በኛ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወይም የህልውናቸው ጉዳይ ሆኖባቸው ምግባቸውን ከኛ ለማግኘት አይደለም፤ ምክንያቱም ወንዱም ሆነ ሴቷ ቢንቢ ምግባቸውን የሚያገኙት ከአበባዎች ዱቄት( nectar) ነው፤ ከደም አይደለም፡፡ በቢንቢዎች ህይወት ውስጥ ደም የሚያስፈልጋት ሴቷ ስትሆን ይህ ደም የሚያስፈልጋት ደግሞ እንቁላሏን በምታጎለምስበት ወቅት ነው፡፡ ደም ፕሮቲን አለው፤ ይህ ፕሮቲን እናት ቢንቢ ለምታዘጋጀው እንቁላል ጤናማነት አስፈላጊ ነው፡፡


ቢንቢ ደም ለማግኘት ቀረብ ያለና ጥሩ የደም ግፊት ያለበት ሰፈር በቆዳችን ላይ ያስፈልጋታል፤ ዙሪያችንን የምታስሰን ለዚያ ነው፤ ይህንን ቦታ ካገኘች በፍጥነት ከርሷን ሞልታ አደጋ ሳይገጥማት ከኛ ማምለጥ አለባት፡፡ ይዘን የገደልናቸው ቢንቢዎች በሙሉ ይህንን ያላሳኩ ናቸው፡፡

የቢንቢ ንክሻ ለምን በጣም ያሳክከናል?
ምንም እንኳን ንክሻ ብለን ብንጠራውም፣ ሁኔታውን ቀረብ ብለን ስንገመግመው ግን እየተካሄደ ያለው ነገር እንዲያ አይደለም፤ በአፏ ትክል ብላ የቆዳችንን የላይኛውን ንጣፍ በመብሳት እንደስትሮው ረዘም ያለውን መምጠጫ አካሏን ታስገባለች፤ ደም በደንብ እየተዘዋወረ በሚገኝበት ቦታ ላይ መምጠጫ አካሏን( proboscis) ካስገባች በኋላ ምራቋን መልቀቅ ትጀምራለች፤ ይህንን የምታደርግበት ምክንያት ምራቋ ደም እንዳይረጋ የሚያደርግ በመሆኑ የሚበቃትን ያክል እስክትመጥ ችግር እንዳይገጥማት ነው፡፡


ሰውነታችን እንዲህ ያለ እንግዳ ነገር ሲገጥመው አንዳች ጥቃት እየተሰነዘረበት መሆኑን ስለሚረዳ ምላሽ ይሰጣል፤ በመሆኑም የፕላስማ ሕዋሳት ሁኔታው ወደ ተፈጠረበት ቦታ ኢሚዩኖግሎቡሊንስ (immunoglobulins) የተባለ ፀረ እንግዳ አካል በማዘጋጀት ወደ ተነከስንበት ስፍራ ይልካሉ፡፡ ይህ የተዘጋጀ ፀረ እንግዳ አካል ማስት( mast cells) የተባሉ ህዋሳትን በማነቃቃት ሂሰታሚን( histamine) የተባለውን ልይ ውህድ እንዲለቁ በማድረግ የመጣውን አካል እንዲፋለሙ ያደርጋሉ፤ ሂስታሚን ጥቃቱ ያለበት ቦታ ሲደርስ በአካባቢው ያሉ የደም ቧንቧዎች እንዲያብጡ ያደርጋል፤ በመሆኑም አብጠቱ የመጣው በሂስታሚኑ የተነሳ እንጂ በቢንቢ ንክሻ የመጣ አይደለም፡፡ የአለርጂክ ሁኔታ የሚፈጥርብን ይህ ሂሰታሚን( histamine) ነው፡፡

ማሳከኩስ ከየት መጣ?
የደም ቧንቧ አብጦ ሲስፋፋ እብጠቱ በአካባቢው ያሉ ነርቮችን ያስቆጣል፤ እነኝህ የነርቭ መቆጣቶች ናቸው ማሳከክ የሚፈጥሩብን፡፡
በቢንቢ ንክሻ አለርጂክ ሆኖ የሚያሳክከንን እንዴት ማስቆም እንችላለን?
ከቢንቢ ንክሻና አለርጂክ ነፃ ለመሆን የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ያለበት አለመነከስ ነው፤ ይህውም ቢንቢዎች በብዛት ባሉበት አካባቢ ስንሆን አጎበርም ሆነ መሉ አካላችንን የሚሸፍን አለባበስ መጠቀም ነው፤ ወይም ደግሞ ኢንሴክቶችን የሚያርቁ ወይም የሚገድሉ መድኃኒቶችን መጠቀም ነው፡፡ ነገር ግን አንዴ ከተነከስንና አላርጂክ ሆኖ እያሳከከ እረፍት ከነሳን ሁነኛ መፍትሔ የሚሆነው ፀረ ሂስታሚን(antihistamine) የሆኑ መድኃኒቶችን መጠቀም ነው፡፡ እነኝህ መድኃኒቶች ሂስታሚንን ስለሚያረክሱ የእብጠት ሁኔታ አይኖርም፤ የእብጠት ሁኔታ ከሌለ ደግሞ አደብድቦ ማሳከክ አይፈጠርም፡፡
ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement