የብረት (Iron) እጥረት Anemia ካለብን ምን ማድረግ አለብን? መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቼው?

  

 

 

 

ምን ማድረግ አለብን? መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቼው?

– አመጋገባችንን በተመለከተ

1. በብረት (Iron) የበለፀጉ ምግቦች መመገብ

ከዓለም ህዝብ 30% የሚሆነው በደም ማነስ ተጠቅቷል፡፡ ከዚሁ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የብረት እጥረት ነው የተጫወተበት፡፡ ከላይ እንደተገለፀው ሔሞግሎቢን የተሰኘው የቀይ ደም ህዋሳት ክፍል የተሰራበት ንጥረ ነገር አንዱ ብረት ነው፡፡ ደማችን በዚህ ምክንያት ቀይ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ኮፕር(መዳብ) ይህን ቦታ በሚሸፍንላቸው እንደነሎብስተር አይነት አሳዎች ደማቸው ሰማያዊ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የብረት ማዕድን የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ ደምን ቀይ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸውንም ደህና አድርጎ ይሰቅልልናል፡፡ እነማናቸው ካላችሁ ቀይ ሥጋ፣ ጉበት፣ የዕንቁላል አስኳል፣ ሽንብራ፣ ባቄላ መብላት ይችላሉ፡፡

2. በፎሊክ አሲድና በቫይታሚን B12 የከበሩ ምግቦች መመገብ

ለሰውነታችን በቀን የሚያስፈልገው የፎሊክ አሲድ መጠን ከ0.4 ሚ.ግ አይበልጥም፡፡ ታዲያ 100 ግራ የሚመዝን ቅጠላ ቅጠል የተመገበ ሰው ከ1 ሚ.ግ የበለጠ ፎሊክ አሲድ ማግኘት ይችላል፡፡ ጠቅላላ የሰውነታችን የፎሊክ አሲድ ጎተራ 5 ሚ.ግ ነው፡፡ ታዲያ አነስተኛ የሆነ ፎሊክ አሲድ በየቀኑ የሚመገብ ሰው ካለ በ4 ወር ውስጥ የደም ማነስ ተጠቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ለምን ጠላት ደስ ይበለው? ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ባቄላ፣ ሎሚ፣ ብርቱካን፣ ሃብሃብ፣ ጉበት፣ ኩላሊት፣ እንጉዳይ እንክት አድርገው ቢበሉ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስን አስቀሩ ማለት ነው፡፡

ቫይታሚን B12ን ቢሆን ሰውነታችን እንዲሁ ይፈልገዋል፡፡ ከፎሊክ አሲድ የሚለየው የሚያስፈልገን የቀን ቀለብ ከፎሌት የሚያንስ በመሆኑ ብዙ እንኳን ባንመገብ ደም ማነሱ ሊከሰትብን የሚችለው ከ3-5 ዓመታት ባሉት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ቁም ነገር ደግሞ ቫይታሚን B12 ከእፅዋት እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ ከስጋ ተዋፅኦዎች ከዓሣና ከወተት ውጤቶች ላይ መፈለግ ግድ ነው፡፡

– ስር ለሰደዱ በሽታዎች መፍትሄ መፈለግ

ለምሳሌ የቲቢ በሽታ ከሆነ ቶሎ መታከም፡፡ የደም ካንሰርም ከሆነ በተለይ ልጆች ላይ አመርቂ የሆነ ውጤት ስላለው በጊዜው መፍትሄ መፈለግ ደም ማነሱንም ሆነ ዋናውን በሽታ ቶሎ ማስወገድ ይቻላል፡፡

– የሚሰጠንን የደም ማነስ መድሃኒቶች በአግባቡ መውሰድ

በተለይ ከፍተኛ የሆነ የብረት፣ የፎሊክ አሲድና ቫይታሚን B12 ፍላጎት የሚንርበት የእርግዝና ወቅት ላይ የሚሰጥ መድሃኒት አለ፡፡ መድሃኒቱ ትንሽ ጨጓራን የመንካት ጠባይ ስላለው፣ በተጨማሪም ዘለግ ላለ ጊዜ ስለሚወሰድ ለምሳሌ ለሶስት ወር ያህል ተጠቃሚው መድሃኒቱን የማቋረጥ ነገር ይታይበታል፡፡ ነገር ግን ለጨጓራው ከሐኪም ሌላ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል እንጂ መድሃኒቱን ባያቋርጡት መልካም ነው፡፡

ደም

ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው እንደሚባለው ሁሉ ለደም ማነስም መድሃኒቱ ደም የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ ብዙ ደም ፈሶት ሔሞግሎቢኑ በጣም የወረደ ሰው ጉበት ብላና ዳን ማለት እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ ላሜ የምትወልደው ለፍልሰታ እንዳለችው ሴት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የፈሰሰ ደም ቶሎ መተካት ስላለበት ጉበቱን ለጊዜው ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ ይሻላል፡፡ ይልቁንም የሚመሳሰለውን ደም ፈልጎ መለገስ ህመምተኛውን ከሞት በእጅጉ ይታደገዋል፡፡

– ከኢንፌክሽንና ከአንዳንድ ጥገኛ ራስን መጠበቅ

ለምሳሌ ወባ ደምን ከማሳነስ ጀምሮ እስከ መግደል ታደርሳለች፡፡ ስለዚህ ራስን ከወባ ትንኝ መጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ የራስን የግል ንፅህና መጠበቅም ቅድም መግቢያችን ላይ እንዳየነው ህመምተኛ በጥገኛ ህዋሳት ከመጠቃት ያርቃል፡፡

መቅንን መተካት

ይህ አይነቱ ህክምና የመቅን ስንፈተ ስጋ ጠማቸው ህመምተኞች የሚከናወንና እጅግ ውስብስብ ቴክኖሎጂን የሚፈልግ ነው፡፡

ምንጭ: የጤና ሞግዚት

Advertisement