10 የብረት (አይረን) እጥረት ምልክቶች – 10 Sign or Symptoms of Iron Deficiency

                                                         

(በዳንኤል አማረ)

ብረት በተለያዩ የሰውነት ሥራዎች ላይ የሚሳተፍ በጣም ጠቃሚ የሆነ ሜኔራል ነው፡፡ ቀይ የደም ሴሎች ወደተለያየ የሰውነት ክፍል ኦክስጂንን እንዲያደርሱ የሚረዳውን ሄሞግሎቢን እንዲመረት በማድረግ የሚታወቅ ነው፡፡

በተጨማሪም ኤሌክትሮን በሴሎቻችን ውስጥ እንዲጓዙ የትራንስፖርት መንገድ በመሆን ያገለግላል፡፡ የተለያዩ ኢንዛይሞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ይህ የብረት ማዕድን እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ጤናማ የሆነ የብረት መጠን በሰውነታችን ውስጥ እንዲኖር ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በአለማችን ላይ ከሚያጋጥሙ የምግብ እጥረቶች ውስጥ በጣም የተለመደው ይህ የብረት እጥረት ነው፡፡ በጊዜ ካልተቆጣጠርነው በብረት ምክንያት ወደሚመጣ የደም ማነስ ያመራል፡፡
የሚከተሉት ዋና የሚባሉ 10 የደም ማነስ ምልክቶች ናቸው፦

1. ድካም!
የብረት መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ላይ ድካም የተለመደ ምልክት ነው፡፡ ሰውነታችን ውስጥ የተመጣጠነ ሄሞግሎቢን እንዲኖር ብረት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሄሞግሎቢን በደማችን ውስጥ ኦክስጂንን የሚሸከም ኬሚካል ነው፡፡ ኦክስጂን በሰውነታችን ውስጥ በሚያንስበት ጊዜ የድካም ስሜት ይሰማናል፡፡

2. የትንፋሽ ማጠር!
ዝቅተኛ ብረት በመኖሩ ምክንያት ለተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ዝቅተኛ ኦክስጂን ይደርሳቸዋል፡፡ የሰውነታችን ኦክስጂን መጠን ዝቅተኛ ሲሆን ደግሞ ምንም ያህል በጥልቀት ቢተነፍሱም የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል፡፡

3. የቆዳ መንጣት!
የብረት መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ሰውነታችን በቂ የሆነ ሄሞግሎቢን ማምረት አይችልም፡፡ ደማችን ቀይ ቀለም እና ቆዳችን ሮዛማ ቀለም እንዲኖረው ያደረገው ሄሞግሎቢን ነው፡፡

4. በቀላሉ የሚሰበር ጥፍር!
ጥፍርዎ በቀላሉ የሚሰበርና አመድማ ዓይነት ቀለም ካለው ይህ የብረት እጥረት ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከጥፍር መሠበር በተጨማሪ የኮንኬይቭ ወይም የማንኪያ ቅርጽ መሰርጎድ በጥፍራችን ላይ ካለ በሰውነታችን ውስጥ በቂ ያልሆነ የብረት መጠን በሰውነታችን ውስጥ እንዳለ ያመላክታል፡፡

5. የፀጉር መሳሳት!
ለፀጉር መሳሳት በጣም በርካታ ምክንያቶች አሉ ከነዚህም መካከል አንድ የብረት እጥረት ነው፡፡

6. የምግብነት ይዘት የሌላቸውን ነገሮች መውደድ!
በህክምና ቋንቋ ፒካ (Pica) ይባላል የምግብነት ይዘት የሌላቸውን ምግቦች ሰዎች ለመመገብ ሲፈልጉ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የጤና ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይህ ሁኔታ በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ የብረት ወይም የሌሎች ማዕድናት እጥረት እንዳለ ያሳየናል፡፡

7. ለብርድ የአየር ሁኔታ በቶሎ መጋለጥ!
በተስማሚ የአየር ሁኔታ ራስዎን በፎጣ ወይም ብርድ ልብስ ጠቅልለው ካገኙት ሊወቅሱት የሚገባዎ ጉዳይ ቢኖር ዝቅተኛ የብረት መጠንዎን ነው፡፡

8. በተደጋጋሚ የራስ ህመም!
በተደጋጋሚ የራስ ህመም የሚያጋጥመዎት ከሆነ በብረት ማዕድን እጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የብረት እጥረት ያለበት ሰውነት በቂ ኦክስጂን ወደ አእምሮ እንዳይደረስ ያግዳል፡፡ ይህም በአእምሮ ደም ቅዳ ላይ እብጠት ስለሚያስከትል የራስ ህመም ይከሰታል፡፡

9. ድብርት!
ጤናማ የሆነ የብረት መጠን በሰውነታችን ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ለሥነ አእምሮ ጤንነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ጤናማ የብረት መጠን ለአጠቃላይ ግንዛቤ፣ ርህራሄን ለማዳበርና ከማህበረሰብ ጋር ያለንን ቅርበት ለማዳበር ይረዳል፡፡

10. እረፍት የለሽ እግሮች!
ለመተኛት በሚሞክሩበት ወቅት እግርዎን ማፋተግ የማያቆሙ ከሆነና እንቅልፍዎን የሚያሰናክል ከሆነ የእረፍት የለሽ እግሮች በሽታ ተጠቂ ነዎት ማለት ነው፡፡ በሴሎቻቸው ውስጥ የብረት እጥረት ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው፡፡

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement