ደም የሚጠሙት አልቅቶች፣ በሕክምናም ውስጥ እየተሳተፉ ነው – Leeches’ Healing Role.

                                           

አልቅቶች ድንቅ የሚባሉ ፍጡራን ናቸው፡፡ አልቅት በሕክምና ዘርፍ ጥቅም ይሰጣል፤ በአልቅት ሕክምና በተለይ በሰውነት ላይ ያተረ ደምን መጦ እንዲያወጣ ይደረጋል፤ በሰውነት ውስጥ የደም ዝውውር እንዲቀላጠፍ ያደርጋል፡፡ ለከፍተኛ ራስ ምታት(ማይግሬን)፣ በአንዳንድ የኦፕራሲዮን ሂደቶችም ላይ ግልጋሎት አለው፤ ለቆዳ ሕክምናም ይውላል፤ ለፀጉር መሳሳትና ለራሰ በረሃነት ሕክምናም ያገለግላል፡፡ በአልቅት የሚደረግ ሕክምና ራሱን የቻለ ዘርፍ ሲሆን ሕክምናው በዘመናዊ መልክ ብዙ በሽታዎችን በማከም ጥቅም እየሰጠ ይገኛል፡፡

አልቅት ልክ እንደ መዥገር ደም መጣጭ ነው፡፡ በወንዞችና በረጋ ውኃ ወይም ኩሬ ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡ በተለይ የመጠጥ ውኃ ከወንዝ የሚጠቀሙ እንስሳት በምላሳቸው ስርና በጉሮሮ አካባቢ ተጣብቆ ይገኛል፡፡ አልቅት ደም ለመምጠጥ የሚያስችሉ ሶስት ጥርስ መሰል ንጣፎች በአፉ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ቆዳችንን ያለምንም ህመም ሰንጥቆ በመግባት በሰውነታችን ላይ ተተክሎ መቆየት ይችላል፡፡ በምራቁ ውስጥ ደም እንዳይረጋ የሚያደርግ ንጥረነገር ስለሚገኝ አንዴ ከተጣበቀ ደም ሳይረጋበት ለረጅም ጊዜ ሊመጥ ይችላል፡፡

አልቅት እንደ ቁስለት ያሉ ክፍተቶችን ካገኘ ወደ ሰውነት ዘልቆ ይገባል፤ ጤናማ ቆዳም ቢሆን ሰንጥቆ መግባት ይችላል፡፡ በህክምና ከሚሰጠው ማደንዘዣ ጋር ተመሳሳይ ተግባር ያለው፣ ነገር ግን በንክሻ ቦታው ላይ ብቻ አደንዝዞ የሚወሰን ንጥረነገር ስለሚጠቀም፣ ወደ ሰውነታችን ሰርስሮ ሲገባ ምንም አይነት ህመም አይሰማንም፡፡ አልቅት በብዛት በሚገኝበት አካባቢ (ወንዞች፣ የተክል ብስባሽ ውስጥ እና ኩሬዎች) ውስጥ ብዙ ቆይታ የምናደርግ ከሆነ ሰውነታችንን በሰዓታት ልዩነት መፈተሽ ይገባናል፤ በተለይ እግራችንን፡፡ አልቅት ያልተጣራ ውኃ ተጠቅመን ወደ ሰውነታችን ከገባ ትልቅ ችግር ሊፈጥርብን ይችላል፡፡ ስለዚህ ውኃ ስንጠቀም አጣርተን፣ አፍልተን ወይም በመድሃኒት አክመን መሆን አለበት፡፡ አልቅት በብዛት ሰውነታችንን በመውረር ተሰክቶብን ከሆነ ለመንቀል መሞከር የለብንም፤ ጥርሶቹ ተነቅለው በሰውነት ላይ ሊቀሩ ወይም ሊበጠስ ይችላል፡፡ ከሰውነታችን ለማላቀቅ የሎሚ ወይም የቆምጣጤ ጭማቂ፣ እርድ፣ በእሳት መተኮስ፣ በዘይት ወይም ቅባት መቀባት(ኦክስጅን እንዳያገኝ ስለሚያደርገው)፣ ጨው መነስነስ ወይም አልኮል ማፍሰስ እንችላለን፡፡ ቁስለት ከፈጠረ እንደማንኛውም ቁስል እስከሚድን ድረስ በንፅህና መንከባከብ አለብን፡፡ 

ምንጭ:- መረጃ

Advertisement