Impacts of Plants at Home and at Work | እፅዋትን በስራ እና በመኖሪያ ግቢ ውስጥ መትከል የሚያስገኛቸው የጤና ጥቅሞች

                    

ጥናቶች በመኖሪያ ቤት፣ በተቋማት አገልግሎት መስጫ ህንጻዎች ግቢዎች፣ በደረጃዎች ላይ እና በእያንዳንዱ ፎቅ ውስጥ ውሃ አዘል አረንጓዴ እፅዋትን በመትከል የሰዎችን ጤና መጠበቅ እንደሚቻል አሳይተዋል።

የግቢ ተክሎችን ለማልማት እና ቤትን በአረንጓዴ እፅዋት ለማስዋብ ቀላል ጉልበትን እና ወጪን ይጠይቃል።

በተለይም በውስጣቸው ብዙ የውሃ መጠን የሚይዙ እፅዋትን በቤት ግቢ ውስጥ አልያም በተቋማት አካባቢ ማብቀል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሚናቸው የጎላ መሆኑም ነው የተገለፀው።

ከዚህም ባሻገር እፅዋቱ  ከሚሰጧቸው በርካታ የጤና ጥቅሞች ውስጥ አምስቱን ዋና ዋና የጤና በረከቶች እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1.አተነፋፈስን ያሻሽላሉ

ቅጠለ ሰፋፊም ሆኑ ውሃ አዘል አረንጓዴ ተክሎች ምግብ በማምረት ሂደታቸው (photosynthesis) ጊዜ በምሽትም ጭምር ኦክሲጅንን ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ፡፡ 

በዚህም በስራ ሰዓትም ሆነ በእረፍት ሰዓት በአካባቢያችን ንፁህ አየር እንዲኖር በማድረግ የተሻለ የአተነፋፈስ ስርዓትን ያመጣሉ፡፡ ምክንያቱም የሚለቁት የኦክስጅን መጠን ለአተነፋፈሳችን ሚናው የጎላ ስለሆነ ነው፡፡

2.የአየር መበከልን ይከላከላሉ

እነዚህ እፅዋት በግቢ ወይም በቤት ውስጥ መተከላቸው የተበከለ አየር እንዳይኖር በማድረግ በተሻለ ከባቢዊ ሁኔታ እንድንኖር ይጠቅማሉ፡፡

ይህ ደግሞ በአየር ብክለት የሚመጡ በሽታዎች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ጥናት እንደሚያሳየው እነዚህ ውሃ አዘል የሆኑ ቅጠለ ሰፋፊ እጽዋቶች በአየር ላይ የሚገኝ የቮላታይል ኦርጋኒክ ኮምፓውንድ 87 በመቶውን ያስወግዳሉ፡፡

በተለይም በቤተ መጻህፍት፣ በሲጋራ ማጨሻ አካባቢዎች እና በግሮሰሪዎች አካባቢ ቢተከሉ እንደ ቤንዚን ያሉ በካይ ጋዞችን ያመቁ የቮላታይል ኦርጋኒክ ኮምፓውንድ መጠንን በእጅጉ ይቀንሱታል፡፡

3.የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም ይጨምራሉ

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለከባቢ አየር ርጥበታማነት 10 በመቶ ድርሻው ከእፅዋት የሚለቀቀው የውሃ መጠን ነው፡፡

ይህ ማለት እያንዳንዱ ሰው በግቢው ወይም በቤታቸው ውስጥ እፅዋትን ከተከሉ የአካባቢው የአየር ሁኔታ እና ቅዝቀዜ የተመጠነ እና ለጤና ምቹ ይሆናል፡፡

የኖርዌይ የግብርና ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናው የእፅዋቱ በአካባቢው መኖር የቆዳ መድረቅ፣ የጉንፋን፣ የደረቅ ሳል እና የጉሮሮ ህመሞችን እንዳይከሰቱ ይከላከላሉ፡፡

4.የአዕምሮ ትኩረት የማድረግ አቅምን ያዳብራሉ

በእጽዋት ዙሪያ መስራት ወይም መኖር የሰዎችን የአዕምሯዊ ትኩረት የማድረግ እና ነገሮችን በጥሩ ሁኔታ የማጤን አቅም ይጨምራል ይላሉ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ተማራማሪዎች፡፡

የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው እፅዋት በአካባቢያችን በኖሩ መጠን የአዕምሮ የማስታወስ እና መረጃዎችን የማደረጃት እና የመለየት ብቃት በ20 በመቶ ያድጋል፡፡

5.ለተወሰነ ጊዜ የሚከሰቱና የተለመዱ የህመም ስሜቶችን ይቀንሳሉ

እፅዋቱ በስራ እና በመኖሪያ አካባቢዎች መኖራቸው እንደ ራስ ምታት እና ሳል ያሉ ቀላል የህመም ስሜቶችን ለመቀነስ ያስችላሉ፡፡ 

እንደካንሳስ ዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ መረጃ እፅዋት በህሙማን አልጋ ውስጥ ካሉ፥ ሆስፒታሎች እንደ ራስ ምታት አይነት በቀላሉ የሚድኑ በሽታዎችን ለማከም ጊዜያቸውን አያጠፉም፤ ምክንያቱም እፅዋቱ በዚያ በመኖራቸው ብቻ የህመም ስሜቶቹ የመከሰት እድላቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡

በተጨማሪም ጭንቀት እና ውጥረት ፈፅሞ ወደ ሰዎች አዕምሮ አይመጡም የተባለ ሲሆን፥ የደም ግፊት እና የልብ ምት ምጣኔን ለመቀነስም የዕፅዋቱ በሰዎች የስራ፣ የመኖሪያ እና የህክምና ተቋማት አካባቢ መተከል ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Advertisement