ስለኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ምን ያክል እናውቃለን?

                                        

መርዛማ ንጥረነገሮችን ለጥቃት ጥቅም ላይ ማዋል የጀመሩት በጥንት ጊዜ አማዞን ደን ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ድርጊቱን ይፈፅሙ የነበሩትም መርዞችን በቀስቶቻቸው ጫፎች ላይ በመቀባት ለጦርነት ወይም ለአደን በመውጣት ነው፡፡ መርዛማ ንጥረነገሮቹንም ያገኙ የነበሩት ከአደገኛ መርዛማ እንሳሳትና እፅዋት ነበር፡፡ ይህ ድርጊት የጥንቱ ዘመን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ሊያሰኘው ይችላል፡፡

ባሁን ዘመን የሚገኙትን የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ግን በሚያደርሱት ጉዳት በሁለት መንገዶች ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ አንደኛ፣ በቆዳ ንክኪም ቢሆን ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱት ሲሆኑ፤ ሁለተኛ ደግሞ በጋዝ መልክ ተዘጋጅተው በመተንፈሻ አካላት በቀጥታ በመግባት አጠቃላይ የነርቭ ስርዓትን የሚያጠቁ ናቸው፡፡ ከሰውነት አካላት ጋር በሚኖር ግንኙነት ለጉዳት ከሚዳርጉን ኤጀንቶች መካከል ፎስጂን(Phosgene)፣ ክሎሪን ጋዝ(Chlorine gas)፣ ሃድሮጅን ሳያናይድ(Hydrogen cyanide) እና የመስተርድ ጋዝ(Mustard gas) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የነዚህ ኬሚካል ኤጀንቶች ጉዳት ከፍተኛ የሚሆነው በመተንፈሻ አካሎቻችን በቀጥታ ሲገቡ ነው፡፡ የፎስጅን ጋዝ ዋና ተግባሩ መተንፈስን በመከልከል ሳንባችን በውኃ እንዲሞላ ማድረግ ነው፡፡ የክሎሪን ጋዝ ደግሞ በመተንፈሻ አካሎቻችን የሚገኙትን ሴሎች ይገድላል፡፡ ሃይድሮጅን ሲያናይድ ኦክስጅን ወደ ደማችን እንዳይደርስ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህልፈት ይዳርጋል፡፡ የመስታርድ ጋዝ ጥቃት፣ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ጋዝ መሰል ፈሳሽ ብናኞች በአየር ውስጥ መሰራጨት ነው፤ ይህ ጋዝ መሰል ፈሳሽ ብናኝ በመተንፈሻ አካላችን ከገባ፣ ከቆዳችን ጋር ንክኪ ከፈጠረ፣ አይናችን ውስጥ ከገባ ወይም ወደ ሳንባችን ከዘለቀ፤ ንክኪ የፈጠረባቸው ቦታዎች ላይ ውኃ እንዲቋጠር በማድረግ ለከፍተኛ ጉዳት ይዳርጋል፡፡ አተነፋፈሳችንን በማስተጓጎልም ለህልፈት ይዳርጋል፡፡
የነርቭ ኤጀንቶች፣ በነርቮች መካከል የሚደረግ የመልዕክት ልውውጥ በመዝጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት ይዳርጋሉ፡፡ ከእነዚህ ኤጀንቶች መካከል ሳሪን(Sarin)፣ ሶማን(Soman)፣ ታቡን(Tabun) እና ቪኤክስ(VX) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ኬሚካል ኤጀንቶች ወደ ሰውነት ሰርገው በገቡ የተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ ለሞት ይዳርጋሉ፡፡

የኬሚካል ኤጀንቶች ጥቃት በሰዎች ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- ኸርቢሳይድ ነው የሚባለው ኤጀንት ኦሬንጅ(Agent Orange) እፅዋቶችን ያወድማል፡፡ ኤጀንት ኦሬንጅ፣ በአሜሪካ-ቬትናም ጦርነት ወቅት(1959-1975) አሜሪካን በጫካ ውስጥ ተሸሽገው የሚገኙትን የቬትናም ወታደሮች ለይታ ለማየት ስለተቸገረች፣ የጫካውን ቅጠል በሙሉ ለማርገፍ እና ገላልጦ ለማየት ኤጀንት ኦሬንጅን ተጠቅማለች፡፡ ይህ በመሆኑም የቬትናም ወታደሮች እንደቀድሞ ከቅጠሎች ጋር ተመሳስለው መሰወር ስላልቻሉ ለጥቃት ተዳርገዋል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶች ኸርቢሳይድን እንደ ኬሚካል ጦር መሳሪያ መቁጠር የለብንም ቢሉም፣ እንደ ኤጀንት ኦሬንጅ ያሉት ግን ውጤታቸው ተፈጥሮን የሚፃረር በመሆኑ እንደ ጥፋት መሳሪያ ሊታዩ ይገባል፡፡ ሰወች እና እንስሳትን ኤጀንቱ አያጠቃም ቢባልም፣ በኤጀንቱ ሰዎች መጎዳታቸውን በወቅቱ የቬትናም መንግስት ክስ አቅርቦ ነበር፡፡

ምንጭ:- ሰርቫይቫል

Advertisement