የዛሬ 86 ዓመት በፊት በ1921 ዓ.ም. በዘመነ ንግስት ዘውዲቱ እና በተፈራ መኰንን አልጋወራሽነት ዘመን ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ የተዘረጋውን የባቡር ሐዲድ ቁልቁል እያነጣጠረ እና የባቡሩን የሀዲድ ፈለግ እየተከተለ ወደ አዲስ አበባ እየበረረ ይመጣ የነበረው አነስተኛ አውሮኘላን ቢሾፍቱ አካባቢ ሲደርስ በደመና በመጋረዱ ከቢሾፍቱ ከተማ 1ዐ ኪ.ሜትር እርቀት በምትገኘው ደሎ ቀበሌ አካባቢ በግዳጅ ለማረፍ ተገደደ፡፡ የአካባቢው ሰው በዚህ ታይቶ ለማይታወቅ የሰማይ ላይ ክስተት የተገመተው ከአምላክ መስቀል ወረደ ብለው /የአውሮኘላኑ የመስቀል ቅርፅ ስላለው/ ዙሪያ ገባው ህብረተሰብ በፈረሰና በእግሩ ጢያራው ወደ አረፈበት ቦታ ተመሙ፡፡ ከዚያ ሁሉ ማህበረሰብ ውስጥም የዘጠኝ ወር ልጃቸውን እተኛበት መደብ ላይ በተነጠፈ አጎዛ ላይ ጥለውት የሄዱ ቤተሰቦችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ቤተሰቦች ግን ይሄ የዘጠኝ ወር ህፃን እነሱን አሯሩጦ ካስኬዳቸው የሰማዩ ባቡር ጋርና ጥለውት ከሄደበት መደብ ላይ ከተነጠፈው ሌጦ ጋር ቁርኝት ይገጥመዋል ብለው እንዴት ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ ግን ሆነ ጠንካራው ገበሬ አቶ ጉያ ገመዳና የሸክላ ጠበብቷ ወ/ሮ ማሬ ጎበና መስቀል ሳይሆን በሆዱ ሰው ይዞ እንደ አሞራ በሰማይ የሚበር ጉድ መሆኑን ለዘጠኝ ወሩ ልጃቸው የነገሩበት አጫሪ መንፈስ ይኑርም አይኑርም ባይታወቅም ህፃኑ አድጎ በ23 ዓመቱ በዚህ ጉድ በተባለው የሰማዩ ባቡር ዋና ተዋናይ ሆኖ የእንጀራው ገመዱ የአንደኛውን አጣ ፈንታ ግጥምጥሞሽ ‘ሀ’ እንዲል አድርጓል፡፡ ይህንን ታሪክ የምንዘክረው ሰው ሻምበል ለማ ጉያ ይባላል፡፡ ሻምበል ለማ ጉያ ከአባቱ ከአቶ ጉያ ገመዳ ከእናቱ ከወ/ሮ ማሬ ጎበና በ1921 በቢሾፍቱ ደሎ ቀበሌ ተወለደ፡፡ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ እጣ ፈንታው የቆየው እንደ ሌሎቹ የአካባቢው ተመሳሳይ ልጆች ተለምዶአዊው የአባታዊ የስራ ፈለግ ውርስ ሳይሆን ያልተለምዷዊውን የወ/ሮ ማሬ ጎበናን የእደ ጥበብ ብቃት ነቅሶ በመያዝ ከእቃ ዕቃ ጨዋታው በላይና ከሚያየው የመገልገያ መሳሪያ የሸክላ ውጤቶች ውጪ ከእድሜው በላይ ወደ ሰራቸው የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች ነበር፡፡ ታዳጊ ወጣት ለማ የአካባቢውን ሰው ያስደመመው በሸክላ የሚሰራቸው የእንስሳት’ የሰው’ የመሳሪያና የቁሳቁስ ቅርፆችን ህብረሰበቡ ቤተሰቦችን ጫና በመፍጠር ወደ ዘመናዊ ትምህርት እንዲገባ አመቺ አጋጣሚ ሆነውለታል፡፡ ወ/ሮ ማሬ ሸክላ ሰሪ ብቻ ሳይሆኑ በቤተሰባቸው ግርግዳ ላይ በተለያዩ ቀለማት ባላቸው አፈሮች የሰዎችንና የእንስሳት ስዕሎችን ስለሚስሉ ቤታቸውን የተለየ እይታን ነበረው፡፡ አቶ ጉያ ገመዳ ወንድ ልጃቸው በእሳቸውን ተክቶ ህይወት በእሳቸው አይነት ክር ይሳሳባልና ቢያልሙት አልሆነም፡ ፡ በእናቱ የገባው የኪነጥበቡ ዘውግ በልጦ የተዋጣላቸው የጥበብ ሰው መሆናቸው አግራሞቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከእያንዳዱ ለስኬት ከታጨ ህፃን ጀርባ የመጀመሪያዋ አስተማሪ የሆነችው ታላቋ እናት አለች እንዲሉ፡- ለማ ጉያ ገመዳ በአሳየው የሸክላ የቅርፅ ስራዎችና በማህበረሰቡ ከፍተኛ ጫና በአስራ አምስት አመቱ ከቀበሌው በአስር ኪሎ ሜትር በሚገኘው በቀድሞው አጠራር አፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት የአስኳላ ትምህርቱን ጀመረ፡፡ እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ይሰጥ የነበረው ትምህርት ካጠናቀቀ በኃላ ቶሎ ስራ ይዞ ቤተሰቡን በመርዳት በነበረው ጉጉት ወደ መምህራን ተቋም ቢገባም አቋርጦ ወደ ቤተሰቦቹ ቀዬ ተመለሰ፡፡ ነገር ግን የስነ-ጥበብና ቴክኖሎጂ ቀመስ ዕድል የሚያገኝበትን ሁኔታ ሲያሰላስል አንድ ዘዴ መጣለት፡፡ ይኸውም በየሳምንቱ መጨረሻ ወደ ቢሾፍቱ የሚመጡትን ንጉስ ሃይለስላሴ የሚያማልል የጥበብ ስራ ሰርቶ የአጃቢዎችንና የኘሮቶኮል ሹሞችን ክልከላ በዘዴ በመወጣት የሰራውን የአውሮኘላን ሞዴል ማሳየት ነበርና፡፡ የሰራው ቅርፅ ጥበብ በንጉሱ አይን በመሙላቱ ምን እንደሚፈልግ ሲጠይቁት #አየር ሃይል ገብቶ መማር$ እንደሆነ ስለገለፀላቸው ትዕዛዝ ተላለፈለት፡፡ ያ በዘጠነኛው ወር እድሜው ቤተሰቦቹ ተገዶ ያረፈን አውሮኘላን ለማየት በድብዳብ በተነጠፈ መደብ ላይ ተጥሎ የነበረው ብላቴና እነሆ የአውሮኘላኑን ሆድዕቃ የሚመረምርና በአርሜንት ኮርስ በካዴትነት ስልጠና ጀምሮና ተመርቆ ወደ አስመራ ከተማ በአየር ሃይል መምህርት ማገልገሉን ጀመረ፡፡ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀው ወጣቱ የአየር ሃይል ቴክኒሻን ለማ ጉያ በእለቱ ከንጉሱ የተበረከተለት ስጦታ የስዕል መሳሪያዎች ነበር፡፡ ለማ ጉያ ከሰለጠነበት የአየር ሃይል ሙያ በተጓዳኝ ለዚህ ሙያና ስራ መግባት በር የከፈተለትን የስነ-ጥበብ ሙያ ሳይዘነጋው በአስመራ የኢጣሊያኖች የስዕል ት/ቤት ከደሞዙ እየቈረጠ በክፍያ በመማር የሙያ ማዳበር ስራውን ጀመረ፡፡ በተለይም በፖርትሬት በመልክአምድር በቁሳቁስ (StillLife) ስራዎች በመጠቀም በመማር በተፈጥሮ የታደለውን እውቀት ሊያዳብር ችሏል፡፡ በተለይም በወታደር ቤት እምብዛም የሲቪል ጉዳዮችን ባልተለመደበት ሁኔታ የስዕል ኤግዚቪሽኖችን በማቅረብ በአንድ በኩል በወታደራዊ ትምህርቱ የተሰጠውን ግዳጅ እየተወጣ በሌላ በኩል የኪነ-ጥበብ ፍቅሩን ለወገኖቹ ሠርቶ በማሳየትና ለጥበብ ቀናኢነቱን አሳይቷል፡፡ ለአስራአንድ አመት የአየር ኃይል ዘመኑን አጠናቆ ወደ እናት ምድቡ ደብረ ዘይት ቢመለስም በኢትዮጵያ ነበረው የፖለቲካ ትኩሳት በተለይም ከ1955ቱ የታህሳስ ግርግርና የሠራዊቱ መከፋፈል ጋር ተነስቶ እንደሻንበል ለማ ጉያ ላለ እና በወቅቱ ከነበሩት ወታደራዊ አባሎች አንፃር የተጨማሪ ክህሎት ባለቤት መሆንና በሚስላቸው ስዕሎች ትርጉም እየተለበሰበት ጎሸም የመደረ/ እጣው ወቅት እየጠበቀ የሚመጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተለያየ የውጭ ሃገራት ዜጐች ከሚበረከቱለት የስዕል መፅሐፎች ለኢትዮጵያውያን በሚስማማ መልኩ በሃገራችን ታሪክ በስዕሉ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነችው የስዕል ያለስተማሪ መፅሐፍ ትርጉም በትምህርት ሚኒስቴር ወጪ ታትሞ በመላው ሃገር ባሉ ት/ቤቶች እንዲሰራጭ በማድረግ በዚህ ዲሲኘሊን ላይ ተሰማርተው ያሉት ምሁራን እንኳን ያላረጉት ለወገኑ አስቦ በማድረጉ ታሪክ ምንግዚም ሊያስታውሰው የሚችል አሻራ አስቀምጧል፡፡ አርቲስት ሻምበል ለማ ጉያ በሃገራችን የፖስተርና የህትመት ቴክኖሎጂዎች ባልደበሩበት ወቅት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰብ የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤን የሚገልፁ በተለይም የኦሮሞን ህዝብ ትውፊትን የሚያጎሉ ስዕሎችን በመሳልና በማተም በመላው ሃገሪቱ እንዲደርስ የከፈለው መስዋዕትነት ያኮራል፡፡ ከአካባቢው ጀምሮ ያሉት መልክአ ምድሮች የህዝብ አኗኗርና የባህል እንቅስቃሴዎችን በታላላቅ ሸራዎች ላይ አስፍሮ ለህዝብ እንዲታይ ከማድረግ በላይ የውስጥ ስማቱንና ቁጭቱን የሚገልፁ ግን እርሱን ለእስርና ለእንግልት የሚደርጉ የስዕል ስራዎች በድፍረት ያሳይም ነበር፡፡ በተለይ በህዝብ ዘንድ ትልቅ አድናቆትን የሰጠውና በሹማምንት ልዩ ትርጉምና አቃቂር በማውጣት ከየወቅቱ አዛዦች ጋር እንዲላተም ካስደረጉት የበኩር ስራዎች ሳትጠቀስ የማታልፈው #ቋንጣ$ የምትባለው ስዕል ነች፡፡ ቋንጣ ስዕል የአፍሪካን የሃብት ምዝበራ ወይም ሙስናን ፍንትው አድርጋ ታሳያለች፡፡ በአንድ ቤት ጓዳ ውስጥ ቋንጣ በàማና በቀይ መልኩ ተዘልዝው ይታያል፡፡ ቋንጣውን መዥርጠው ለመብላት ይታገላሉ፡፡ ጠፍሩ አልጋ ላይ በድምሩ አራት ድመቶች ወጥተዋል፡፡ አንደኛው ግድግዳው በጥፍሩ ቧጥጦ ያወርዳል፡፡ አንዱ ቁመቱ አልደርስ ብሎታል፡፡ አንደኛው ደግሞ በእጁ የገባለትን እንደያዘ ሌላ ለማግኘት አንጋጧል፡፡ በእነርሱ ግፊያና ግርግር ጮጮ ሙሉ ወተት ተደፍቷል፡፡ የወተቱ አወራረድ የአባይ ፋፏቴን ተመስሎ ቀርቧል፡፡ የመጨረሻው ድመት የሸረሪት ድር የወረሰውን ድብኝት አፍጦ በሸረፋት ድር የተያዘውን ነፍሳት ለመያዝ ያስባል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ ግን ከአልጋው ስር አይጥ እሸት በቆሎ ትቀረጥፋለች፡፡ ይህንን ስዕል ስትመለከቱት የራሳችሁ ፍርድ ትሰጣላችሁ፡፡ የዛሬ አመት ግንቦት 18/2ዐ14 በኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ ‘An eagle eyed Artist’ በሚል ርዕስ በቋንጣ ላይ ድንቅ ትንታኔ ተሰጥቷል፡፡ ለማ ጉያ ከአስመራ መልስ በአካባቢው በሚገኙት በጎዲና በኮታ በደሉ በኡዴ በፈቃና በሃረር ሜዳ ከአስር የሚበልጡ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም መስቀል አደባባይ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በማሰራት ከጥበብ ስራው በተጨማሪ ለወገኑ ታላቅ ስራ በመስራት በአካባቢው ተከባሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በግዳጅ በጡረታ እንዲገለል የተደረገው አርቲስት ለማ ጉያ ቀሪ ህይወቱን ለስነ-ጥበብ ማዋሉን ተያያዘው፡፡ በተለይም በሃገራችን የስነ- ጥበብ ማሳያ ጋለሪዎችን በስፋት አለመስፋፋትን ተከትሎ በተለይም በሶቪየት ህብረት በተደረገለት ግብዣ ሩስያውያን እና መንግስታቸው ለጥበቡ የሚሰጠውን ታላቅ ድጋፍ ቁጭት ውስጥ ስለከተተው በሃገሩ ምድር የጥበብ ጋለሪ ማሳያ የማቋቋም ግፊቱን ቀጥሎበት ከ3ዐ በላይ የውጭ ሃገራት ዲኘሎማቶችን በመጋበዝ ድንኳን በመጣልና ስራዎቹን በማሳየት ማዕከል እንዲመሰረት አድርጓል፡፡ አርቲስት ለማ ጉያ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አርት ጋለሪ ባለቤት ሲሆን የጋለሪውን መታሰቢያ በኒልስን ማንዴላ ሃውልት በማጀብ አራት የጋለሪ ቤቶችን በመገንባት ለህዝብ ምንግዜም ክፍት ሆነው ስራዎቹን ወጣቱ ትውልድ እንዲማርበት በማድረግ ላይ የገኛል፡፡ ከአርማሜንት መሃንዲስነት የራሱን የአርት ቤት መሪነት ከአርትለሪ ናዛዥነት የአርት ጋላሪ አዛዣነቱን ከነቤተሰቡ በደስታና በፍቅር ይዞታል፡፡ ዛሬ ለማ ጉያ በኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ ፈለግ ለየት ያለ አሻራ አስቀምጧል፡፡ የስነ-ጥበብ ውጤቱ #ለማዊነት$ የሚል ስም አሰጥቶታል፡፡ አርቲስት ለማ በተለይም በቆዳ ስራ ላይ የሚቀርፀው የፖርትሬት ምስል ስራዎች ከሃገር አልፎ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራትን ተማሪዎች እቤት ድረስ አምጥቶ እንዲያስተምር በር ከፍተውለታል፡፡ የቆዳ ስራ በሃገራችን እድሜ ጠገብ ቢሆንም የአርቲስት ለማ ስራ ግን በተለይ የፍየል ቆዳ ሙሉ በሙሉ ፀጉሩ ሳይነሳ ተፈጥሮአዊ ወዙንና መልኩን ይዞ የፊትን ገፅ ብቻ በቀለም በመስራት የሚሰራቸውን የቆዳ ላይ ስዕሎች ልዩ መገለጫው ከመሆኑም አልፎ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዲኘሎማቶች የራሳቸውን የቤተሰቦቻቸው ምስሎች ማሰራት ልምድ ሆኗል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ምስሎችን ለክልሎች በዚሁ በቆዳ ስራ በማሰራት የኢትዮጵያን ታዋቂ ሰዎች መሪዎች ዲኘሎማቶች በለማ ጉያ የቆዳ ስራ ያልተነሱ አሉ ቢባል በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በህይወት ዘመኑ ወደ 1ዐ ሺህ የሚጠጉ የስዕል ውጤቶችን ለሃገሩ ያበረከተው አርቲስት ለማ ጉያ በመሠረተው ጋለሪ ግቢ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመክፈትም የሃገር ግዴታው እየተወጣ ይገኛል፡፡ አርቲስት ለማ ጉያ በደቡብ አፍሪካው ኘሬዝዳንት ጀኮብ ዙማ በተደረገለት ጥሪ ለሶስተ ጊዜ በኢኢንሲ አመታዊ ስብሰባ ተሳትፋል፡፡ – ሶስት ትውልድ የተናገሩ የጥበብ ስራዎችን የሰራ በሚል በሰሜን አሜሪካ የውስጥ ቅርስ ማህበር ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ – በአፍሪካ ህብረት ህብረቱን ያገለገሉ ፀሐፊዎችን በኦሮሚያ የባህል ማዕከል በአዲሱ ህንፃ የኦሮሚያ ኘሬዝዳንቶችንና የኦሮሞ ባህልና ትውፊትን የሚያሳዩ የቆዳ ላይ ስዕሎችን አያበረከተ ይገኛል፡፡ የዛሬ 86 ዓመት ቤተሰቦቹ አውሮኘላን ለማየት መደብ ላይ ተነጥፋ ተኝቶበት የነበረው ሌጦ ዛሬ የአርቲስቱ የጥበብ አሻራ መገለጫ ሆኖ የወቅቱን የእጣ ፈንታው መወለድ ሽታ ሆኖ ቀርቶ ነበር፡፡ አርቲስቱ በማህበራዊ ኑሮውም ሆነ በስራው አሁንም ደከመኝ ሰለቸኝ አይልም፡፡አሁንም ፖሌቱንና ቡርሹን ይዞ ይሰራልየሚገርመው ነገር ከትዳር አጋሩ ጋር ለ5ዐ ዓመት የወርቅ ኢዩመልዩ የጋብቻ ስነ-ስርዓት እየደረሱ ነው፡ ፡ ከወ/ሮ ማሬ ጎበና የተጋባበት የጥበብ ውርስ እየቀጠለ ነው፡፡ የአርቲስት ለማ ጉያ ሶስት ሴቶች ልጆቻቸውና ሁለት ወንድ ልጆቻቸው አምስቱም የስነ-ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ዘ ጉያ ፋሚሊ አሁንም ይቀጥላል፡፡ አርቲስት ለማ ጉያ እድሜውን ሙሉ ለጥበብ የሰጠ- ሀገር ወዳድና ባህሉን ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው፡ ፡ ምንም አይነት መደበኛ ትምህርት ሳይኖረው የተፈጥሮ ጥበቡን በማዳበር የራሱን የጥበብ Icon እንዲሆን አድርጓል፡፡ በስነ-ጥበቡ ዘርፍ የማይረሳ ለዘላለም ሊቀጥል የሚችል ለሃገርና ለወገን አርአያ የሚያደርገውን ውለታ ፈፅሟል፡፡ አላማውን ከግብ ለማድረስ ቀናኢ ከመሆኑም በላይ ከቤተሰቡ እስከ ወገኑ ሊተር ፍ የሚችል የጥበብ ርስራሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተፈጥሮ የሚገኘውን የቆዳ ምርት የጥበብ እሴት ጨምሮና ከሸኖ ወደሚናገር አምድ ቀይሮታል፡፡ የባህል እሴቶቻችን ከሃገር አልፈው እንዲነበቡ አንዲታወቅ እንዲገለፁ ያደረገ የጥበብ ጀግና ነው፡፡ ለወጣቱም ሆነ በሙያው ለተሰማራ ሁሉ የጠንካራ የስራ ስኬት ሞዴል መሆን የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሰኔ 5/2ዐዐ7 ዓ.ም. በወሰነው መሠረት ለአርቲስት ለማ ጉያ ገመዲ የክብር ዶክትሬት በስነ-ጥበብ እንዲሰጥ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡ በመሆኑም፡- የተከበሩ ዶ/ር ፍቅሬ ለሜሳ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት የክብር እንግዳዎን ወ/ሮ አስቴር ማሞን ጋብዛው የተዘጋጀውን ሽልማት እንዲሰጥ እንዲያደርጉ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡