ዋ…..ተማሪ መሆን

 

                                    

          ኣንደኛ ክፍል ትምርት ስጀምር፤ የመማርያ ክፍላችን ተሠርቶ ኣልተጠናቀቀም ነበር፡፡ እና ከክፍሉ በር ተነስተን መቀመጫ ወንበራችን ላይ እስክንደርስ ድረስ ጉቶ ያደናቅፈን፣ ሰርዶም ይጠልፈን ነበር፡፡

መምህሩ ከታች እያስተማረ ከሰሌዳው ራስጌ፤ ኣንድ ቀጫጫ ኣናጢ መሠላል ላይ ቆሞ ጣራውን መመዶሻ ሲወቅር ኣይቸዋለሁ፡፡

መምህራችን ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ካፍሪካ ኣንደኛ መሆኗን ሲተርክልን ከላይ ያለው ኣናጢ”ምነው ዲስኩሩን ትተህ ተጠመኔው ኣጠገብ ያለችትን ቢስማር ብታቀብለኝ“ እያለ ያናጥበዋል፡፡

ተማሪ ቤትን ሳስብ ትዝ የሚለኝ ዩኒፎርም ነው፡፡ የዩኒፎርም ዓላማ በደሃና በሃብታም ተማሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ነው፡፡ግን ሃብታሞች ሁሌም ብልጫቸውን ኣስጠብቀው መቆየት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም በረቂቅ መንገድ ይፋለማሉ፡፡

ትምርት ቤቱ ሁላችንም ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ያለው ዩኒፎርም እንድለብስ ያስገድድ ነበር፡፡ ሃብታሞች በቀለሙ ተስማምተው ለልጆቻቸው ኣንደኛ ደረጃ ጨርቅ ይመርጡላቸዋል፡፡ በሚይዙት የደብተር ቦርሳ በሚጫሟት ጫማ ለየት ብለው እንዲታዩ ያደርጓቸዋል፡፡

እኛ የድሃ ልጆች ዩኒፎርማችን ለትምርት ቀሰማ ብቻ ሳይሆን ለእንጨት ለቀማም ስለምንጠቀምበት ከሁለት ወር በኋላ ቀለሙን ይቀይራል፡፡ ቁልፉ ረግፎ በድዱ ብቻ ይቀራል፡፡ እነ መርፌ ቁልፍ የረገፈውን ቁልፍ ተክተው ኣገልግሎት ለመስጠት ይታገላሉ፡፡

በጊዜው ተሽከርካሪ ወንበር ስላልነበረ በሰለቸን ቁጥር እኛው ራሳችን ወንበራችን ላይ ከመሽከርከር ውጭ ኣማራጭ ኣልነበረንም፡፡ ኣሁን ሳስበው ፤ ክፍል ውስጥ እንጎለትበት የነበረው ነገር ኣግዳሚ ወንበር የሚል ስም ይበዛበታል፡፡ ሁለት እግር ያለው የወደቀ የብሳና ግንድ ተብሎ ቢጠራ ያምርበታል፡፡ ግማሽ ቀን ተቀምጨበት ስነሳ መሃረብ የሚያክል ጨርቅ ከሱሪዬ ላይ ቆርሶ ያስቀራል፡፡ የፊዚክስ መምህር ሰለ ሰበቃ friction ባሰተማረ ቁጥር ለምሳሌነት የሚጠቅሰው የኔን ሱሪ ነበር፡፡ የሰፈራችን እውቅ ልብስ ሰፊ የተለያየ ቀለምና የጥራት ደረጃ ባላቸው ትርፍራፊ ጨርቆች በመጣጣፍ በነተበው ሱሪዬ ላይ ነፍስ ለመዝራት ሞከሩ፡፡ ሙከራው መቀመጫዬ ኣካባቢ የጥንቱን ያለም ካርታ የሚመስል የጨርቅ ምስል በመሳል ተጠናቀቀ፡፡

ተማሪ ቤት ሲነሣ ጋሽ ዮሴፍ ያቆብን ሳላነሣ ማለፍ ኣይሆንልኝም፡፡ጋሽ ዮሴፍ ወፍራም ነበሩ፡፡ ቦርጭን ወደ ደብረማርቆስ ለመጀመርያ ጊዜ ያስገቡት ጋሽ ዮሴፍ ይመስሉኛል፡፡ ተዝያ በፊት ቦርጭ ምን እንደሆነ ያየነው መስከረም በተባለው መጽሄት ላይ በሚሳለው የኢምፔሪያሊዝም ካርቱን ስእል ላይ ነው፡፡ በመጽሄቱ የመጨረሻ ገጽ ላይ ኢምፒየሪያሊዝም ከትንሽ ህጻን ልጅ ኣፍ ጡጦ ቀምቶ ሲጠባ ይታያል፡፡ ደርግ፤ ቦርጭ ካድሃሪው ስርኣት የተወረሰ ኣካል ነው ብሎ ስለሚያምን ቦርጭ ማውጣትን በህገመንግስቱ ከልክሎ ነበር፡፡ጋሽ ዮሴፍ ከሶስት መቶ ብር ደመወዝተኛ የማይጠበቅ ቀፈት በማውጣታቸው ኣቃቤህግ ከሰሳቸው፡፡ ክቡር ፍርድቤቱ የግራና የቀኙን ክርክር ኣዳምጦ የኣምስት ወር ጂምናስቲክ ፈረደባቸው፡፡

ጋሽ ዮሴፍ ሁሌም በግራ ብብታቸው ስር የተጣጠፈ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ይይዛሉ፡፡ በዚያች ጋዜጣ ኣምስተኛ ገጽ ላይ ታላቅ ልጃቸው ፤ ወላጅን ስለማክበር የጻፈው ግጥም ታትሟል፡፡ የትምርት ምኒስትር የመደባቸው ጂኦግራፊ እንዲያስተምሩ ነበር፡፡ ልጃቸው ግጥም ካወጣ በኋላ በራሳቸው ጊዜ የስነግጥም መምህር ሆኑ፡፡ ፈርዶብን የሳቸውን ልጅ ግጥም በቃል ስንወጣ ውለን ወደ ቤታችን እንሄዳለን፡፡ ያንን የቸከ ግጥም ስሸመድድ ኖሬ ግጥም ኣለመጥላቴን ሳስብ ይገርመኛል፡፡

ጋሽ ዮሴፍ “መኣድን” የተባለ ትንሽ ልጅ ነበራቸው፡፡ መኣድን የተባለው ወድቆ ስለተገኝ ነው፡፡ ክፍል ሲመጡ እንደ ቡችላ ተከትሏቸው ይመጣል፡፡ ከኛጋ ትንሽ ሲማር ከቆየ በኋላ ይሰለቸዋል፡፡ ከዚያ ብድግ ይልና ከተማሪዎች መካከል ትንሽ ኣናት ያለውን ተማሪ መርጦ በቴስታ በመምታት ይዝናናል፡፡ ኣልፎ ኣልፎ ኣባቱ እያስተማሩ እሱ ድምጡን ከፍ ኣድርጎ ይዘምራል፡፡ መዝሙሪቱ…
“ሰባትና ሰባት ሲደመር ኣስራ ኣራት
መንግስቷይለማርያም የጨለማ መብራት”
የምትል፤የሂሳብ ስሌትን እና የግለሰብ ኣምልኮን ኣስተባብራ የያዘች መዝሙር ነበረች፡፡

እስከ ሶስተኛ ክፍል በሂሳብ ጎበዝ ተማሪ ነበርሁ፡፡ ሶስተኛ ክፍል ስደርስ እትየ ስለናት የተባለች መምህር ገጠመችኝና በሂሳብ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ካለኝ እምነት ጋር ኣቆራረጠችኝ፡፡ የሆነ ብዜት ትጠይቀኝና ስሳሳት ና ወዲህ ውጣ ትለኛለች ፡፡ ገና እንደወጣሁ ከስጋና ከጅማት የተሰራ መንሽ በሚያክል መዳፏ በጥፊ ትከድንብኛለች፡፡ ኪራላይሶ ! የሰው ልጅ ሳይወልድ ኣይኑን ባይኑ ማየት እንደሚችል የተረዳሁት ለመጀመርያ ጊዜ የትየ ስለናት ጥፊ ፊቴ ላይ ሲያርፍ ነው፡፡

እትየ ስለናት ከማስተማር ውጭ ያለውን ጊዜዋን የምታሳልፈው ሻረው የተባለውን ጓደኛየን በመግረፍ ነበር፡፡ ”የምትገረፍበትን ለበቅ ቆርጠህ ኣምጣ “ ትለዋለች፡፡ ሻረው ከክፍል ይወጣና ጓሮ በበቀለው ጫካ ውስጥ ገብቶ ይንጎራደዳል፡፡ እጁን ወገቡ ላይ ኣድርጎ እያንዳንዱን ቅርንጫፍና ቅጠል በጽሞና ሲቃኝ በእጽዋት ላይ ምርምር የሚሰራ እንጂ ኣርጩሜ የሚቆርጥ ኣይመስልም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመስኮቱ ብቅ ብሎ እጩ ኣርጩሜውን እያሳየ ”ይቺ ትሁን እትየ?“እያለ ያማርጣታል፡፡ እሷም እንደ ሸማች “ትንሽ ጨምርበት” ምናምን ብላ ተከራክራ ስትጨርስ ኣንበርክካ ታበራየዋለች፡፡ ኣሁን ሳስበው፤ ትምርት ቤታችን በትምህርት ሚኒስትር ስር የሚተዳደደር ራሱን የቻለ የቶርች ካምፕ ኑሯል፡፡ የወህኒ ቤት ገራፊዎች ስርኣት ሲለወጥ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ የትምርት ቤት ገራፊዎች ግን መምህር በሚል የክብር ልብስ ተሸፍነው ተከብረው ይኖራሉ፡፡

ኣረጋ ተሰማ የተባለ ቀውላላ ላይበራሪያን ያደረገኝን እንዴት ረሳዋለሁ፡፡ ጋሽ ኣረጋ በላይበራሪያንነት የተመደበው ከትልቅ መደርደርያ ላይ መጽሃፍ ለማውረድ የሚያስችል ቁመት ስላለው መሆን ኣለበት፡፡ ኣብማ ትምርትቤት ስማር በሳምንት ኣንድ ቀን የንባብ ክፍለጊዜ ነበረን፡፡ ወይ ንባብ! ክፍለጊዜው ኣርባ ደቂቃ ብቻ ቢሆንም ከሰላሳ ደቂቃ በላይ ያለውን ጊዜ የምናጠፋው ያረጋ ተሰማን ኣሰልቺ መመሪያ በመስማት ነው፡፡

“መመሪያ ኣንድ ! ጸጥታ! ማንኛውም የላይበራሪው ተጠቃሚ ማውራትም ሆነ ማንሾካሾክ ኣይጠበቅበትም፡፡ እደግመዋለሁ ማውራትም ሆነ ማንሾካሾክ ኣይጠበቅበትም”

“መመርያ ሁለት ጽሞና፡፡ ማንኛውም ተማሪ ጽሞና ማሳየት ይጠበቅበታል”

ትዛዙ ስድሳ ድረስ ይዘልቃል፡፡ መመሪያውን ተጠናቆ የመጀመርያውን ገጽ ስንገልጥ ክፍለጊዜው ማለቁን የሚያረዳው ደወል ይደወላል፡፡

ኣንድ ቀን ኣላስችለኝ ስላለ ጋሽ ኣረጋ ሲዘበዝብ እኔ ከፊቴ የተቀመጠውን ”ለምለምና ጎሹ” የተባለ መጽሃፍ ገለጥ ኣርጌ ማንበብ ጀመርሁ፡፡

“ውጣና ተንበርከክ“ የሚል ድምጽ ኣናጠበኝ፡፡ ኣረጋ ተሰማ ወለሉ ላይ በጥንቃቄ ኣንበርክኮ ያገጨን ኣቅጣጫ ሲያስተካክል ሊሥለኝ ለሞዴልነት እያመቻቸኝ እንጂ ለግርፍያ የሚያሰናዳኝ ኣይመስልም፡፡ በኋላ ወድያ ወዲህ እየተንጎራደደ ትእዛዛቱን ማዝነብ ቀጠለ፡፡ድንገት ግን ዞር ሲል እና እግሩ ሲወናጨፍ ትዝ ይለኛል፡፡ ከዝያ ወድያ ትዝ የሚለኝ ነገር ቢኖር መለስተኛ ኣውሎ ነፋስ ያነሳው ኣቧራ ክፍሉን መሙላቱ ነው፡፡ በዚያ መጅ እግር የግድያ ሙከራ ተደርጎብኝ መትረፌ ተርፌም ይችን መጻፌ ይገርመኛል፡፡ የድመት ነፍስ እና የተርምኔተርን ኣካል የሰጠኝ የወንቃው ጊዮርጊስ የተመሰገነ ይሁን፡፡ በኤክስሬይ ቢታይ ጋሽ ኣረጋ የጫማ ምልክት ጉበቴ ላይ ሳይኖር ኣይቀርም፡፡

ከእለታት ኣንድ ቀን ይመር የተባለ ጓደኛችን ወለላ ለተባለች ልጅ ኣፍቅሮ ደብዳቤ ጻፈላት፡፡ ደብዳቤው በደብተር ውስጥ ተሸሽጎ ከእጅ ወደ እጅ ሲዘል ቆይቶ ለተፈቃሪዋ ሳይደርስ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

ኣንድ ቀን ማለዳ ላይ ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ይመርና ወለላ ወደ መድረኩ እንዲወጡ ተደረገና ደብዳቤው ለተማሪው ሁላ ተነበበ፡፡ ርእሰ-መምህራችን ደብዳቤውን ይዞት ወደ መደረኩ ሲወጣ ኣቤት ፊቱ ላይ ይታይ የነበረው ኩራት! የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ያከሸፈ እንጂ የሁለት ምስኪኖችን የፍቅር ደብዳቤ የዘረፈ ኣይመስልም፡፡ ከደብዳቤው ውስጥ ኣንድ ሃረግ በተነበበ ቁጥር ተማሪው ሲያወካ ከውካታው እኔም ያቅሜን ኣዋጥቻለሁ፡፡ በጊዜው በይመርና ወለላ “ብልግና” ተቆጥቸ በውርደታቸውም ረክቼ ነበር፡፡ የሁለቱ ፍቅረኛሞችን ግላዊነት ከደፈሩት ጋር መተባበሬ ፤ህሊናን ቶርች ከሚያደርጉት ጋር ማበሬ የገባኝ ኣሁን ነው፡፡

ይህ በእውነተኛ ገጠመኝ ላይ የተመሰረተ ኩሸት ነው፡፡ 
ግን ብዙዎቻችሁ ያሳለፋችሁት ልጅነት ከዚህ መንፈስ እንደማይወጣ እገምታለሁ፡፡

በተማሪ ቤት ያስተዋልነው የጉልበተኛ መምህሮችና ያቅመቢስ ተማሪዎች ግኑኝነት ከትምርት ቤት ስንወጣ የቀረ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡

ባለቃና በምንዝር መካከል ያለው ግኑኝነት፤
በኣከራይና በተከራይ መካከል ያለው ግኑኝነት፤ 
በመንግስትና በገባሩ መካክል ያለው ግኑኝነት፤ 
በዚህ ብሄርተኛና በዚያኛው ብሄርተኛ መካከል ያለው ግኑኝነት ፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግኑኝነት በትምርትቤታችን ኣምሳል የተዋቀረ ይመስለኛል፡፡
.
በ በዕውቀቱ ስዩም

Advertisement