በአሜሪካው ግዙፉ ‘ያም ብራንድስ’ ዓለም አቀፍ ኩባንያ እና በኢትዮጵያው ‘በላይ አብ ፉድስ’ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ፒዛ ሃት ዛሬ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ አዲስ አበባ ላይ ከፍቷል።
በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይም አንድ ተጨማሪ ቅርንጫፍ እንደሚከፈት ይጠበቃል። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 10 ለማድረስ ድርጅቶቹ ተስማምተዋል።
35 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት ይህ ስምምነት በሁለቱ ቅርንጫፎቹ 55 ሠራተኞች ያቀፈ ሲሆን ኢትዮጵያ በሰሃራ ክፍለ ግዛት ለፒዛ ሃት 12 መዳረሻ ሆናለች።
እውን ፒዛ ሃት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ንግድ ተቋማት ገበያውን ነጻ እያደረገ እንደሆነ ሊያሳየን ይቻላል? የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አብዱልመናን መሃመድ እንዲህ አይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ እንደሚከብድ ይናገራሉ።”እንዳዛ ማለት ይከብዳል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ የኢንቨስትመንት አዋጁን በብዙ መልኩ በማሻሻል የውጭ ሃገር ኢንቨስተሮች ሊሰማሩ የሚችሉበትን የንግድ ዘርፎች ብዛት እንዲጨምር አድርጓል” ይላሉ ባለሙያው።
አቶ አብዱልመናን ፒዛ ሃት ኢትዮጵያ ውስጥ የገባባበት መንገድ ለየት ባለ ሁኔታ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ፒዛ ሃት ፍራንቻይዝ (የንግድ ስም ሽያጭ) ነው። ኢትዮጵያውያን ናቸው የድርጅቱን ስም በመውሰድ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ምርቶችን ለተጠቃሚ የሚያቀርቡት”ብለዋል።
አንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ፒዛ ሃት ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያውያን የመግዛት አቅም እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ይያያዛል።
“በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የንግድ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ለሌሎች የንግድ ተቋማትም መማበረታቻ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።
የሚያዘጋጃቸውን ፒዛዎች ከ90 እስከ 350 ብር ለገበያ የሚያቀርበው ፒዛሃት ምግቡን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በጠቅላላ ከውጭ ሃገር እንደሚያስገባ አስታውቋል።
ይህ የድርጅቱ እርምጃ ጥሬ ግብዓቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎችን ሊጎዳ አይችልም ወይ ለሚለው ጥያቄ ባለሙያው ምላሽ ሲሰጡ “እንደ ፒዛ ሃት ያሉ ፍፈራንቻይዝ ተቋማት ለምርቶቻቸው ጥራት እጅጉን ይጠነቀቃሉ። ለዚህም ነው ግብዓቶቹ በሙሉ ከአንድ ቦታ እንዲሆኑ የሚመርጡት። በዚህ አካሄዳቸውም ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያን በመጠየቅ ትርፋማ ይሆናሉ” በማለት ሂደቱን ያስረዳሉ።
አብዱልመናን ድርጅቱ በገበያው ውስጥ ምን ያህል ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ሲችል እንደሆነ ይጠቁማሉ።
በሳምንት ወደ 2200 ሽያጭ ለማከናወን እቅድ እንዳለው ፒዛ ሃት ያሳወቀ ሲሆን አሁን የተተመነለት ዋጋ የተጋነነ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ።
“ዋጋ በሌሎች ሃገራት ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው። በኢትዮጵያም ከ3-12 የአሜሪካን ዶላር ለመሸጠት ነው ያሰቡት። ከፍተኛው 350 ብር አካባቢ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው” ይላሉ።
መቀመጫውን ኬንታኪ ግዛት ያደረገው ፒዛ ሃት በአፍሪካ ከ1 ሺህ በላይ ፒዛዎችን በመለያው የሚሸጡ ሱቆች ያሉት ሲሆን ኩባንያው በአህጉሪቱ 188 ፍቃድ ያላቸው ቅርንጫፎች እንዳሉትም ተዘግቧል፡፡
ምንጭ፦ ቢቢሲ