ለጠነከረ እና መተማመን ለሰፈነበት ፍቅር

                                     

በጓደኝነት እና በፍቅር ህይዎት ውስጥ በሚኖር የአብሮነት ቆይታ ጥሩም ሆኑ መጥፎ አጋጣሚዎች ይከሰታሉ።

ዋናው ነገር የዚህ አይነት አጋጣሚዎች መምጣትና መሄድ ሳይሆን አብሮነትን መጠበቁና ማስቀጠሉ ላይ ነው፤ በሁለቱም የአብሮነት ቆይታ ወቅት የሚከሰቱ መጥፎ አጋጣሚዎችን ተራርሞና ተማምኖ ይቅር መባባል አንድነትን ያጠናክራልና።

አንድነት ሲኖር ደግሞ መተማመን ይበልጥ ይጎለብታል፤ ከዚህ በፊት የነበረን ቅራኔ ወይም መጥፎ ድርጊት፤ የአንድ ወቅት የህይዎት አጋጣሚ እና ክስተት አድርጎ በማሰብና አጠፋ የተባለውን ወገን ይቅር ማለትሲጀምሩ ያን ጊዜ መተማመን ይጎላል ይላሉ፥ በሬዲመር ዪኒቨርሲቲ የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ላውራ ሉቺ።

አክለውም ያንን ድርጊት ከመርሳት ይልቅ እያብሰለሰሉ የመጥፎ ባህሪ መገለጫና የዛ ግለሰብ ማንነት እንደሆነ ካሰቡ መቸም ወደ ይቅርታ አይመጡም፥ በሂደትም እምነት የለሽ እና ተጠራጣሪነትዎ እንደሚጎላም ይናገራሉ።

ከመዋደድ እና ሰላም ነን ብለው ከሚያስቡት የግንኙነት ሂደት በበለጠ መንገድም መተማመን በወንድማማችነት መሃል ባለ ጓደኝነትም ይሁን ለፍቅር ግንኙነት ወሳኙ ነገር እንደሆነ ያነሳሉ።

እምነት ማሳደር ጓደኛዎን ወይም የፍቅር አጋርዎን መጥፎ እና ደካማ ጎኖች ሳይሆን አብሮነትን እና መልካም ጎናቸውን እያዩ ቀና እና ደስ የሚል ግንኙነት እና የፍቅር ህይዎት እንዲኖርዎት ይረዳል፤ ፅኑ፣ አስደሳችና ሙሉ ጓደኝነትና የፍቅር ግንኙነት እንዲኖርም ያግዛል።

እናም በጓደኝነት እና በፍቅር ህይዎትዎ ይበልጥ ስኬታማ እና ዘለቄታው ያማረ እንዲሆን ከፈለጉ መተማመንን የሚያጎሉ መንገዶችን ይጠቀሙ፤

ምርጫውን ለአጋርዎ ይስጡ፥ እምነት እና መተማመን የሚማሩት እና የሚያገኙት እንደመሆኑ መጠን በሚሆነው ነገር ላይ ማመን ይኖርብወታል።

ለዚህም ከአጋርዎ ጋር ለሚኖርዎት ቀጠሮ የሚመርጡትን ቦታ ጨምሮ የሚጠቀሟቸውን ነገሮች ምርጫ መስጠትን ይልመዱ።

በዚህም በቀጠሮ ቀናችሁ እርሱ/ እርሷ/ በመረጡት ነገር እና ባሳለፉት ጊዜ ደስተኛ እና ምርጫው እንደተስማማችሁ እርግጠኛ መሆን ይኖርባችኋል፤ አጋርዎን እምነት ስለጣሉበት እና በመረጠው ነገር እንዳስደሰትዎ እንዲሰማው ማድረግም ይልመዱ።

ሁሉንም ነገር ማሳየት አለመደበቅ፥ ማታ ሲለያዩ እና ወደ ቤት ለመሄድ ስትሰነባበቱ የነበረ ገጽታ ጠዋት ከእንቅልፍዎ ሲነቁ ስለመበላሸቱ ሳይሆን እውነተኛ ማንነትዎን ማሳወቅ የመተማመኛ መንገድ ነው ይላሉ ላውራ ሉቺ።

በህይዎትዎ ያለውን ማንኛውንም ነገር ማሳወቅና አለመደበቅ በችግር ጊዜ ለሚፈጠር ቅራኔ ማስወገጃ መንገድም ይሆናል፤ ምክንያቱም የራስዎን ያክል ውስጥዎን አጋርዎ ስለሚያውቀው እና ባለዎት ነገር እምነቱ ስላለው ለይቅርታ ብዙ ጊዜ አይወስድም።

እናም መደባበቅና በአጋር ላይ እምነት ማጣት ለግንኙነት አይበጅምና እምነት ጥለውበት የራስዎ ያድርጉትና ውጤቱን ይመልከቱት።

እርግጠኛ ይሁኑበት፥ ምናልባትም ከስራ ቦታዎ ሲወጡ ተበሳጭተው በሰዎች ቂም ይዘው ከሆነ፥ የፍቅር ጓደኛዎን ወይም አጋርዎን ሲያገኙ ከመገናኘትዎ በፊት የነበረን ስሜት ከማንጸባረቅ ይቆጠቡ።

ሰዎች ቢሮ ውስጥ ያደረጉት እና ያበሳጭዎት ጉዳይ ከእርሱ ጋር እንደተገናኘ ማሰብና አንዳንድ ጊዜ በሚፈጠር ስሜታዊነት አንተም/ አንችም/ ያው ነህ ማለት እና የነበረን አመለካከት መቀየር ተገቢ አይደለም ይላሉ።

ይብዛም ይነስ በሰጡት ልክ ነውና የሚቀበሉት ጓደኛዎን ሲያገኙት እንደዛ ባይሆኑ ይመረጣል።

ለውሳኔ አለመቸኮል ወይም አለመፍረድ፥ አልፎ አልፎ ሰዎች ጓደኛዎ ያደርገዋል ብለው ወይም አድርጎት የሚያውቀው አይነት የሚመስል እና ተቀራራቢ ገጠመኝ ይነግሩዎት ይሆናል።

ያ ጊዜ ግን ከአጋርዎ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ዘለቄታዊ የሚያደርጉበት አልያም ነገሮችን ከማለፍ በዘለለ ተነጋግረው በማየትና በመፍታት የሚግባቡት ሊሆን እንደሚገባም ነው ያሰፈሩት።

ከዛ ይልቅ የሰሙት ነገር በአንድ አጋጣሚ ስለተመሳሰለ ያንን ስሜት አስበው ትችት እና ፍርድ ከሰጡ ግንኙነትዎን ሊያበላሹ የሚችሉ ነገሮች ይፈጠራሉ፤ የፍቅር አጋርዎ በቀጣይ በእርስዎ ላይ ያለው እምነት ይሸረሸራልና።

እናም በእርስዎ ተቀባይነት እንዳለውና አሁንም ተፈላጊ መሆኑን በማሳየት ጉዳዩን ጉዳየ በማለት እና በሰከነ መንፈስ በመወያየት፥ በእርስዎ ይበልጥ እምነት እንዲሰማው ያድርጉ።

ቃልን መጠበቅ እና ታማኝነት፥ እምነት በብዙ መንገዶች ይመጣል ይላሉ ሉቺ፥ እርስዎ ዘንድ የሌለን ነገር ከአጋርዎ መጠበቅ ግን ፍጹም ስህተት ነው።

በቅድሚያ ለግንኙነታችሁ ሃላፊነት የሚሰማዎትና ታማኝ ይሁኑ ያንን ሲያደርጉ ቃልን ለመጠበቅና ለዘለቄታዊ ግንኙነት አይቸገሩም።

ምናልባት እንኳን ማታ እደውላለሁ ብለው ሰአት ያሳለፉ መስሎ ከተሰማዎት ከወዲያኛው ጥሪ ሳይመጣ እርስዎ ቢያደርጉት ተመራጩና መንገድና መተማመንን የሚያመጣ ጉዳይ ነው።

ራስን መሆን፥ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ከአጋርዎ ወዳጆች ፊት እንኳን ቢሆን ማንነትዎን በተገቢ መንገድ መግለጽ እና ማሳየትም መተማመኛ መንገዱን ማምጫው ሌላው ዘዴ ነው።

ምናልባት እስከዛሬ ያላሳዩትን ባህሪና ማንነት ፍቅረኛዎን ለማስደመም እና ለማስደሰት ብለው ባላሰበው የቀጠሮ ቀን ከሰዎች ፊት ቢያሳዩ፥ እስከዛሬ የደበቁበትን መንገድ እና ሌላ ማንነትዎን እንጅ ለማስደመም እንዳሰቡት አይቆጥረውምና ያንን ያስወግዱ።

እንደ ላውራ ሉቺ በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን አንድም ነገር መደበቅና የተለየ ማንነት ማሳየት መተማመን ቀርቶ አብሮ መዋልንም አስቸጋሪ ያደርገዋልና እሱን ትተው ሁሌም ማንነትዎን ሳይደብቁ ማሳየት ይኖርብወታል።

እውነቱን መናገር አለመዋሸት፥ ትንሽም ይሁን ትልቅ ውሸት የትም ቦታ ቢሆን የግንኙነት መቋጫ እና ለአመታት የተገነባን ግንኙነት መናጃ እና ማፍረሻ መንገድ ነው።

አንድ ቀን በጥቂቱ የተጀመረ ውሸት እና ቅጥፈት በሂደት እያደገ እና በመሃል የነበረን መልካም ግንኙነትና መተማመን በመናድ የግንኙነትን መቋጫ እና መደምደሚያ ያበጃል።

እናም ከወራት በፊት ወይም የዛሬ አመት በዋሉበት ገበያ የገዙትን እቃ ዋጋ ማስታወስ ፈልጎ ፍቅረኛዎ ከጠየቀዎት ምንም ሳይዋሹ መናገሩ መተማመንን አጉልቶ ግንኙነትን ያጠነክራልና ሁሌም ቢሆን እውነቱን ይናገሩ።

ሰአት አክባሪነትም ቃልን ከመጠበቅ ያልተናሰ ጠቀሜታ ስላለው በመሃላችሁ ላለው መተማመን ይረዳል፤ ስለዚህም ሁሌም ባሉት ሰአት ለመገኘት ይሞክሩ።

ከሁለታችሁ የተደበቀን ሚስጥር ካለ ያስወግዱ፥

በግንኙነታችሁ መሃል አንዳችሁ የምታወቁት ሌላኛው ወገን ግን የማያወቀውና የተደበቀ ሚስጥር ካለ እርሱን ያስወግዱት፥ አንዳችሁ ያንዳችሁን ሚስጥር እና ገመና ማወቅ እና ያንን መረዳት ይኖርባችኋል።

ምናልባትም የፍቅር አጋርዎ ከዚህ በፊት የተከዳ / ከሌላ ሰው ጋር ባደረጉት ሚስጥራዊ ግንኙነትም ሊሆን ይችላል/ ከሆነ ያንን ጉዳይ ረጋ ባለ መንፈስ በይቅርታ ጀምረው ማስረዳትና የሆነውን መንገር ይበልጥ ለመተማመን ይረዳል፤ ያ ሲባል ግን ይቅር ስላለዎት መድገም እንዳለብዎ በጭራሽ አያስቡት።

ሌላው ቀርቶ ከማን ጋር እንደሚደዋወሉና ለማን የሞባይል መልዕክት እንደሚልኩ ማሳወቁና የተወሰኑ ቁጥሮችን ማገድ / ብሎክ/ ማድረግዎን ቢያቆሙ መልካም ነው።

እርስዎ የሚያደርጉትን ነገር ለአጋርዎ ደበቁ ማለት ራስ ወዳድነት ነው ያ ደግሞ መተማመንን ያስወግዳልና ሚስጥርዎን ያካፍሉት።

አጋርነትዎን ያሳዩት፥ አንዳንድ ጊዜ ለፍቅር አጋር አጋዥ መሆንዎን ማሳየት በሚኖራችሁ የፍቅር ግንኙነት ከሚያደርጉት ቀጥተኛ እና ትክክለኛ ባህሪ ይልቅ ተመራጭ እና አዋጭ ነው።

ሌላው ቀርቶ ከጥብቅ ወዳጁ ጋር በሚኖር አለመግባባት እርስዎ አጠገቡ ከሆኑ፥ ሳይበዛ ለእርሱ አጋርነትን ማሳየትና ምናልባት የእርሱ ስህተት ከበዛ፥ ሁለቱም ልክ እንደሆኑ በመንገር ለየብቻ ማወያየት ይመረጣል።

ይህም በእርስዎ ላይ ያለውን እምነት ማሳደጊያው መንገድ ይሆናል፤ ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች በፍቅር ህይዎት ውስጥ በሚኖር ሂደት መተማመንን ይበልጥ ለማምጣት እና ፍቅርን ለማጠንከር የሚረዱ ናቸውና ይጠቀሙባቸው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement