መኖሪያዋን ዱባይ ያደረገችው የ12 ዓመቷ ህንዳዊት ታጋዲ ለ6 ሰዓት ገደማ የቆየ የሙዚቃ ድግስ ላይ በ102 የተለያዩ ቋንቋዎች በመዝፈን ሁለት አዳዲስ የዓለም ክብረ ወሰኖችን መያዝ ችላለች።
ሱቼታ ሳቲሽ የተባለችው ይህች ታዳጊ 6 ሰዓት ከ15 ደቂቃ በፈጀ የሙዚቃ ድግስ ላይ ነው በ102 የተለያዩ ቋንቋዎች በመዝፈን ስሟን በዓለም የክብረ ወሰኖች እና የድንቃ ድንቅ መዝገቦች ላይ ማስፈር የቻለችው።
ዱባይ በሚገኘው የህንድ ሁለተኛ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሱቼታ፥ በበርካታ ቋንቋዎች በመዝፈን ክብረ ወሰን ለመያዝ ዝግጅት የጀመረችው ከ1 ዓመት በፊት ነበር።
ሱቼታ ከዚህ ቀደም በህንድ ውስጥ የሚዘወተሩ እንደ ሂንዲ፣ ማላያላም እና ታሚል ያሉ ቋንቋዎችን ጨምሮ በእንግሊዝኛም ትዘፍን ነበር።
ሆኖም ግን በተለያዩ ሀገራት ቋንቋዎች መዝፈን መቻል የዘወትር ፍላጎቷ እንደነበረም የምትናገር ሲሆን፥ ይህም ሱቼታ በርካታ ቋንቋዎችን እንድትማር አድርጓታል ነው የተባለው።
ከውጭ ቋንቋ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘፈነችው ዘፈን በጃፓንኛ መሆኑን የምትናገረው ሱቼታ፥ በመቀጠልም አረብኛን ጨምሮ በሌሎች ቋንቋዎች መዝፈን መጀመሯን ተናግራለች።
የሱቼታ የመጀመሪያ እቅድ በሀገሯ ሰው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ማሻሻል እንደነበረ የተነገረ ሲሆን፥ ህንዳዊው ገሃዛል ሰሪቫንስ በ76 የተለያዩ ቋንቋዎች በመዝፈን ነበር ክብረ ወሰን የያዘው።
ታዳጊዋ ይህንን ክብረ ወሰን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ባሳለፍነው ታህሳስ ወር 2017 ላይ 85 ቋንቋዎችን በመዝፈን አሻሽላ የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ለ12 ዓመቷ ታዳጊ አጥጋቢ አልበረም።
ለዚህም ልምምዷን አጠናክራ የሰራችው ሱቼታ፤ በአውሮፓውያኑ በጥር 2018 በዱባይ የህንድ ቆንስላ በተዘጋጅ የሙዚቃ ድግስ ላይ በተመልካቾች ፊት በመቆም፥ በ6 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ውስጥ በ102 የተለያዩ ቋንቋዎች በመዝፈን በርካቶችን አስደመመች።
ታዳጊዋ ሱቼታ 102 የተለያዩ ቋንቅዎችን ተጠቅማ በመዝፈኗም አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ችላለች።
ሱቼታ ለመዝፈን ከተጠቀመቻቸው ቋንቋዎች ውስጥም፥ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዳኒሽ፣ ጀርመንኛ፣ ሶማሊኛ፣ ስዋህሊ፣ ቱርክኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ጃፓንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፑርቹጊዝ እና አረብኛ ተጠቃሽ ናቸው።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)